ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ።

መጸለይ፣ ቅዱሳት መጽሐፍትን ማንበብ፣ በየእሑዱ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ መስዋዕተ ቅዳሴን ማስቀደስ፣ የመቁጠሪያ ጸሎትን መድገም፣ እነዚህ በሙሉ የተለመዱ የአንድ ክርስቲያን ተግባራት ናቸው። ነገር ግን በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች እነዚህን ክርስቲያናዊ ተግባራት ለመፈጸም የሚነሱ ምዕመናን ለከፍተኛ አደጋ የትጋለጡ ይሆናሉ፣ በድንጋይ ተወግረው ይገደላሉ፣ ወይም ከባድ የሆኑ የጉልበት ሥራን እንዲሠሩ ይገደዳሉ።   

የዘንድሮ ጎርጎሮሳዊው አዲስ ዓመት የተጀመረው በፊሊፒን በሚገኝ አንድ ካቴድራል ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት በማድረስ ላይ በነበሩ ምእመናን ላይ መሣሪያ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው 23 ሰዎችን የመግደላቸውን ዜና በማሰማት ነው። ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ 40 ሚሲዮናዊያን መገደላቸው ሲታወስ ከእነዚህም መካከል 35ቱ ካህናት መሆናቸው ታውቋል። ሁለቱ የተገደሉት በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ነበር።

በማሕበራዊ ሚዲያዎች በስፋት የተነገረው በፓክስታን የአሲያ ቢቢ ጉዳይ ሲሆን ይህች እናት የተከሰሰችው የነብዩን መሐመድ ስም አጥፍታለች፣ የእስልምናን እምነት አንቋስሳለች ተብላ በሐሰት ክስ ለዘጠኝ ዓመታት በወይሂኒ ተወርውራ እንድትማቅቅ ተደርጋለች። በ2007 ዓ. ም. እስላማዊ ጽንፈኛ የአሸባሪ ቡድን በግብጽ በሃያ አንድ ሰዎች ላይ የወሰዱት የግድያ ተግባርም የሚታወስ ነው። በፓክስታንም እንደዚሁ በ2006 ዓ. ም. በ130 ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ የሚታወስ ነው። 

በብዙሃን መገናኛውዕጭ በኹል አልተነገሩም እንጂ እነዚህን የመሳሰሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የግድያ ተግባራትን መጥቀስ ይቻላል። ለእምነት ነጻነት የቆመ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ሪፖርት መሠረት በዓለም የክርስትና እምነት ከሁሉም እምነቶች ይልቅ የከፋ ስቃይ እና ስደት የደረሰበት መሆኑ ታውቋል። በዓለማችን በ38 አገሮች ውስጥ መሠረታዊው የሰዎች መብት ክፉኛ የተጣሰ መሆኑ ሲነገር ከእነዚህም መካከል 21 አገሮች በሰዎች ላይ ከፍተኛ ስቃይን የሚፈጽሙ መሆናቸው ታውቋል። “በብዙ የዓለማችን ክፍሎች ለእምነት ነጻነት ቅንጣት የሚያህል ትኩረት አልተሰጠውም። በዛም አነሰም ተመችቶኝ እኖራለሁ ብሎ ማሰብ ሳይሆን እምነቱን ለመግለጽ የሚነሳ ሁሉ በሕይወት የመቆየት ዕድሉ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው” በማለት የገለጹት፣ ለእምነት ነጻነት የቆመ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ሥራ አስኪያጅ ክቡር አቶ ቶማስ ሔይን ጄልደርን ተናግረዋል።                 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየወሩ የሚያቀርቡትን የጸሎት ሃሳባቸው ምዕመናን በያሉበት ሆነው በጸሎት እንዲተባበሩ በማለት ለመጋቢት ወር እንዲሆን ያሉትን የጸሎት ሃሳብ በቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል። የመጋቢት ወር የጸሎት ሃሳባቸውም፣ ከመጀመሪያዎቹ ዘመናት ይልቅ በዛሬው ዘመን የበለጠ የሰማዕትነት ገድል እየታየ መሆኑን ገልጸው በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰ መሆኑን አስታውሰዋል። ስቃይ የሚደርስባቸውም እውነትን ስለተናገሩ እና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰበኩ ነው ብለዋል። በብዙ የዓለማችን ክፍሎች በክርስቲያኖች ላይ ስቃይን እና መከራን የሚያደርሱ አገሮች የእምነት ነጻነትን በማያስከብሩ እና ዋስትናን በማይሰጡ አገሮች ውስጥ መሆኑ ታውቋል። በክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ ስቃይ ጎልቶ የሚታየው በእነዚህ አገሮች ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብቶችን እና ነጻነቶችን የማስከበር ሥራን ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ በወረቀት ብቻ ባሰፈሩት አገሮች ዘንድ መሆኑን አስታውቀዋል።

05 March 2019, 18:13