ፈልግ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሮም ከተማ ማዘጋጃ ቤት ጉብኝት፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሮም ከተማ ማዘጋጃ ቤት ጉብኝት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሮም ከተማ ነዋሪዎች በቸርነት ተግባር እንዲተባበሩ ጠየቁ።

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልብ ውስጥ፣ የክርስትና እምነትን ለማይጋሩትም ሳይቀር፣ ልዩ የፍቅር ሥፍራ እንዳለ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለነዋሪዎቿ በሙሉ መንፈሳዊ አንድነትን በማሳየት፣ ዘወትር ወንድማማችነትን እና ሕብረትን እንዲያሳዩ እገዛን እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል። “እንደ ሌላው የዓለማችን ሕዝቦች የሮም ከተማ ነዋሪዋችም ስለ ኑሮ፣ ልጆቻችሁን ስለ ማስተማር፣ የዓለማችን የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ ሳያስጨንቃችሁ አይቀርም። ነገር ግን ዛሬም ቢሆን ነገ እያንዳንዳችሁ እንደየ አቅማችሁ የተቸገረን መርዳት፣ እርስ በእርስ መተጋገዝ እንዳለባችሁ አደራ እላለሁ”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. የሮም ከተማ ማዘጋጃ ቤትን በመጎብኙበት ወቅት የከተማው ከንቲቫ ወይዘሮ ቨርጂኒያ ራጂ ከከፍተኛ የሥራ ባልደረቦቻቸው እና የማዘጋጃ ቤቱ ሠራተኞች ጋር ሆነው አቀባበል አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ከከተማው ከንቲቫ ከወይዘሮ ቨርጂኒያ ጋር ሃሳብ ከተለዋወጡ በኋላ በማዘጋጃ ቤቱ የሚገኙትን የተለያዩ ጽሕፈት ቤቶችን፣ ታሪካዊ በሆኑ ጥንታዊ ሕንጻዎች ውስጥ ተገኝተው ንግግሮችን አድምጠዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሮም ማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ባሰሙት ንግግር በከተማው ውስጥ በሚገኙ ትላልቅ ቤተክርስቲያኖች በቅዱስ ጴጥሮስ እና በቅዱስ ዮሐንስ ባዚሊካዎች እንዲሁም በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኙ ቁምስናዎች ሲገናኙ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ዛሬ ግን በሮም ከተማ ማዘጋጃ ቤት፣ የከተማው ሕዝባዊ አስተዳደር ከሚገኝበት ማዕከል መገኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው ማዘጋጃ ቤቱ ለቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ለሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሲያሳይ ለቆየው ፍቅር እና ድጋፍ ምስጋናችውን አቅርበዋል።

በሮም የምትገኝ ቤተክርስቲያን፣ እንደ አንጾኪያው ቅዱስ ኢግናሲዮስ አገላለጽ፣ በፍቅር እንደምትተዳደር እና ይህም የራሷ ጳጳስ የሥራ ድርሻ ቢሆንም ቅሉ ለቤተክርስቲያን የሚገባትን አገልግሎት ማበርከት እና መንከባከብ፣ ልብን የሚያድስ የኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር ብርሃን እንዲበራ ማድረግ የሁሉም ክርስቲያኖች የሥራ ድርሻ እንደሆነ አስረድተዋል።

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልብ ውስጥ፣ የክርስትና እምነትን ለማይጋሩትም ሳይቀር፣ ልዩ የፍቅር ሥፍራ እንዳለ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለነዋሪዎቿ በሙሉ መንፈሳዊ አንድነትን በማሳየት፣ ዘወትር ወንድማማችነትን እና ሕብረትን እንዲያሳዩ በማለት እገዛን እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል። እንደ ሌላው የዓለማችን ሕዝቦች የሮም ከተማ ነዋሪዋችም ስለ ኑሮ፣ ልጆቻችሁን ስለ ማስተማር፣ የዓለማችን የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ ሳያስጨንቃችሁ አይቀርም። ነገር ግን ዛሬም ቢሆን ነገ እያንዳንዳችሁ እንደየ አቅማችሁ የተቸገረን መርዳት፣ እርስ በእርስ መተጋገዝ እንዳለባችሁ አደራ እላለሁ። ይህን በማድረጋችሁ ይህች ከተማ ነዋሪዎቿ በአንድነት፣ በሰላም እና በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ የሚያደርግ እሴት በልባችሁ ውስጥ እንዲፈጠር ከማድረግ በተጨማሪ ለፍትህ ብቻ ሳይሆን የፍትሃዊነት መንፈስ እንዲሰፍን ታደርጋላችሁ ብለዋል።

ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የሠመረ እንዲሆን የተባበሩትን፣ የሮም ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሠራተኞችን በሙሉ አመስግነው እግዚአብሔር ጸጋውን እንዲያበዛላቸው እና እንዲባርካቸው በመጸለይ ወደ መንበረ ቅዱስ ጴጥሮስ ተመልሰዋል።              

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በሮም በሚገኘው ማዘጋጃ ቤት ከከተማው ከንቲባ ጋር በተገናኙበት ወቅት
26 March 2019, 17:32