ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የዐብይ ጾም ወቅት ልባችንን ከክፉ ነገሮች የምናጸዳበት የጸጋ ወቅት ነው” አሉ

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በየካቲት 27/2011 ዓ.ም የዐብይ ጾም ወቅት መጀመሩ ይታወቃል። ይህ የዐብይ ጾም ወቅት የተጀመረው የሰው ልጆች ሁሉ ያለእግዚኣብሔር ድጋፍ እና ምሕረት ከንቱ መሆናችንን እንድናስታውስ እና ብሎም በዚህ በዐብይ ጾም ወቅት በሠራናቸው ኃጢአቶች መጸጸታችንን በመግለጸ መንፈሳዊ የሆነ ለውጥ በማምጣት የፋሲካን በዓል ተገቢ በሆነ መልኩ ለማክበር መንፈሳዊ ዝግጅት የምናደርግበት ወቅት መሆኑን በመግለጸ የዐብይ ጾም ወቅት በይፋ መጀመሩ ይታወቃል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ  ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የዐብይ ጾም ወቅት በየካቲት 27/2011 ዓ.ም በተጀመረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራነቸስኮስ በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኘው ሳንታ ሳቢና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “በእውነተኛ ልብ እግዚኣብሔርን እንዳናመልክ ለማድረግ፣ ልባችንን በመጥፎ ነገሮች በመሙላት፣ ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያበላሹብንን ጣዖታት፣ ገንዘብ እና ምድራዊ የሆኑ የማያቋርጡ ፍላጎቶቻችንን በማስወገድ በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት ልባችንን ከክፉ ነገሮች የምናጸዳበት የጸጋ ወቅት ሊሆን ይገባል” ማለታቸውን ከደረሰን መረጃ ለመረዳት ተችሉዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 27/2011 ዓ.ም የዐብይ ጾም በተጀመረበት ወቅት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የዛሬው የመጀመሪያ ምንባብ “በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ” (ት. ኢዩኤል 2፡15) ይለናል። ይህ የዐብይ ጾም ወቅት የሚጀመረው መለከት በሚነፋበት ወቅት በሚያወጣው ለጆሮ በሚሰቀጥጥ ድምጽ ሲሆን ነገር ግን ከዚያን በኋላ ወደ ደስታ በዓል ይለወጣል። ይህ የሕይወታችን ጉዞ እንዳይዘገይ ማድረግ የሚችል በጣም ፈጣን የሆነ ድምጽ ሲሆን ነገር ግን አቅጣጫ አልባ የሆነ ድምጽ ነው። በሚያስፈልጉን ነገሮች ላይ ብቻ ማተኮር እንችል ዘንድ የቀረቡ የመጥሪያ ድምጾች ናቸው፣ እኛን የሚረቡሹን የማያስፈልጉንን ነገሮች መጾም እንድንችል የቀረበልን የማንቂያ ድምጽ ነው።

ይህ የማንቂያ ጥሪ ጌታ በነቢዩ ከንፈር አማካይነት በተናገረው አጭር እና ከልብ የመነጨ “ወደ እኔ ተመለሱ” (ኢዩኤል 2፡12) ከሚለው መልእክት ጋር ተያይዞ የቀረበ ነው። ወደ እኔ ተመለሱ። መመለስ ካለብን እኛ ቀድመን ጠፍተናል ማለት ነው። የዐብይ ጾም ወቅት የህይወት አቅጣጫን ዳግም ለማግኘት እድል የሚሰጠን ወቅት ነው። ምክንያቱም በእያንዳንዱ ጉዞ ውስጥ፣ በእያንዳንዱ የጉዞ ሂደት ውስጥ  ዋናው ጉዳይ ግባችን ምን መሆኑን አለመዘንጋታችን ነው። ለመጓዝ የሚያስፈልገን ነገር ቢኖር በጉዞ ወቅት አከባቢያችንን በመቃኘት ምግብ መብላት ስላለብን በእዚያ አከባቢ ምግብ ቤት መኖሩን ወይም አለመኖሩን ካላረጋገጥን በስተቀር ርቀን ለመጓዝ አንችልም። ራሳችንን እንዲህ ብለን እንጠይቅ፣ ‘በሕይወት ጉዞዬ ውስጥ መንገዱ ቢርቅም እንኳን ወደ ፊት ለመጓዝ እፈልጋለሁ ወይ?’ ወይም የዛሬውን ጊዜ ቢቻ በመኖር ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ በማድረግ አንዳንድ ችግሮችን በመፍታት እና በመዝናናት ደስተኛ ሆኜ ለመኖር እፈልጋለሁ ወይ? ታዲያ ይህ መንገድ የተኛው ነው? በዛሬው ዘመን የሚገኙ ብዙዎች እንደሚናገሩት በቅድሚያ እኔን የሚያስፈልገኝ ነገር አላፊ የሆነው የጤና ጉዳይ ነው ወይ? ወይስ ደግሞ ሐብት መሰብሰብ እና ጥሩ የሆነ ኑሮ መኖር ነው ወይ? እኛ ክርስቲያኖች ግን በዚህ ዓይነት ዓለም ውስጥ መኖር አይገባንም። “ወደ እኔ ተመለሱ ይለናል” አምላካችን። ወደ እኔ ኑ ይለናል። በዚህ ዓለም ውስጥ የእኛ የክርስቲያኖች ግብ ጌታ አምላካችን ብቻ ነው። ሁሉም አቅጣጫ ወደ እርሱ ሊመራን ይገባል።

ዛሬ ትክክለኛውን መንገድ እንድናገኝ የሚረዳን ምልክት አግኝተናል፡ ይህም በዐመድ የተቀባው ግንባራችን ነው። ይህም በአእምሮዋችን ውስጥ የሚመላለሰው ሐሳብ ምን እንደ ሆነ እንድንገነዘብ የሚረዳን ምልክት ነው። ሐሳቦቻችን በአብዛኛው የሚያተኩሩት ጊዜያዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ነው፡  እነሱም ወደ እኛ ይመጣሉ ተመልሰውም ይሄዳሉ። ግንባራችንን በዐመድ የምንቀባው ትንሽዬ ምልክት አስተሳሰባችንን የሚቆጣጠሩትን ብዙ ነገሮች፣ በየቀኑ እነርሱን ለማግኘት የምናሳድዳቸው እና በእየቀኑ ስለእነርሱ የምንጨነቅባቸው ነገሮች ሁሉ አይኖሩም የሚል የማስታወሻ ምልክት ነው። ምንም ያህል ጠንክረን የምንሠራ ብንሆንም እንኳን  ከዚህ ምድራዊ ከሆነው ሕይወት ለሕይወታችን የሚሆን ምንም ዓይነት ሐብት አናገኝም። በምድር ላይ ያሉት እውነታዎች በንፋስ እንደ ሚወሰዱ አቧራዎች ናቸው። ንብረቶች ጊዜያዊ ናቸው፣ ስልጣን አላፊ ነው፣ ስኬቶች እየቀነሱ ይሄዳሉ። ዛሬ ጎልቶ ለመታየት የመቸኮላችን ባሕል፣ ዛሬ በሁሉም ስፍራ አንጸባራቂ ሆኖ ለመታየት ያለን ፍላጎት እጅግ በጣም አታላይ የሆነ ፍላጎት ነው። ይህ ፍላጎት ልክ እንደ እሳት ነው፣ እሳቱ አንዴ ነዶ ካለቀ የሚቀረው ዐመዱ ብቻ ነው። የዐብይ ጾም ወቅት እንደ አቧራ በነው የሚጠፉ ጊዜያዊ ነገሮችን ከማሳደድ እና ከከንቱነት እኛ ራሳችንን ነጻ የምናወጣበት ወቅት ነው። የዐብይ ጾም ወቅት እኛ የተፈጠርነው ወዲያው ነዶ ነዶ አልቆ ዐመድ የሚሆነውን እሳት ለመሆን ሳይሆን የማይጠፋውን እሳት እንድናነድ መፈጠራችንን የምንገነዘብበት ወቅት ነው፣ ይህን እሳት የምናነደው ለዓለም ሳይሆን ለእግዚኣብሔር ነው፣ አታላይ ለሆኑ ለምድራዊ ነገሮች ሳይሆን ለዘላለማዊ መንግሥት፣ የቁሳቁሶች ባሪያ ለመሆን ሳይሆን ለእግዚኣብሔር ልጆች ነጻነት ብለን የምናነደው እሳት ነው። “እኔ በየተኛው ጎራ ላይ ነው የቆምኩት”? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። የምኖረው እንደ እሳት ነው ወይስ እንደ ዐመድ?

በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት ጉዞ ላይ በጣም አስፈላጊ ወደ ሆኑ ነገሮች መመለስ እንችል ዘንድ፣ ከግብዝነት እና ትክክለኛ ካልሆኑ ነገሮች እንቆጠብ ዘንድ የሚረዱንን ሦስት እርምጃዎችን እንወስድ ዘንድ ቅዱስ ወንጌል ሐሳብ ያቀርብልናል፡ እነዚህም ምጽዋዕት መስጠት፣ ጸሎት እና ጾም ናቸው። ታዲያ እነዚህ ነገሮች ምንድናቸው? ምጽዋዕት መስጠት፣ መጸለይ እና መጾም በነው ሊጠፉ ወደ ማይችሉ ወደ ሦስት እውነቶች ይመልሱናል። ጸሎት ከእግዚኣብሔር ጋር፣ ምጽዋዕት ከባልንጀራዎቻችን ጋር እና ጾም ደግሞ ከራሳችን ጋር ተመልሰን  በአዲስ መልክ ሕብረት እንድንፈጥር ይረዱናል። እግዚኣብሔር፣ ባልነጀራ እና እኔው ራሴ፡ እነዚህ እንዲያው በከንቱ በነው የማይጠፉ እውነታዎች በመሆናቸው የተነሳ በእነዚህ ነገሮች ላይ አጥብቀን መሥራት ይኖርብናል። የዐብይ ጾም ወቅት በቅድሚያ በጸሎት አማካይነት ሁሉን በሚችል እግዚኣብሔር ላይ ትኩረት እንድናደርግ የሚጋብዘን ወቅት ሲሆን ይህም ለራሳችን የሚሆን ጊዜ እንድናገኝ በማድረግ እግዚአብሔርን እንድንረሳ ከሚያደርጉን ዓለማዊ ከሆነ ሕይወት ነፃ እንድንወጣ ያደረገናል። ምጽዋዕት መመጽወት ደግሞ በሌሎች ሰዎች ላይ እንድናተኩር የሚጋብዘን ሲሆን ይህም የልግስና ተግባር ከንቱ በሆነ መንገድ ቁሳቁሶችን ለራሳችን ጥቅም ብቻ ይሆን ዘንድ እንዳናጋብስ እና ለእኔ ጥሩ የሆኑ ነገሮች ብቻ ናቸው ጥሩ የሚባሉ ነገሮች ብለን እንዳናስብ ይረዳናል። በመጨረሻም የዐብይ ጾም ወቅት በጾም አማካይነት ወደ ራሳችን በመመለስ ልባችንን በጥልቀት እንድንመለከት ይህም ደግሞ ከነገሮች ጋር ተጣብቀን እንዳንቀር እና ልብን የሚያደነዝዝ ዓለማዊ የሆነ ሕይወት እንድናስወግድ ይረዳናል። ጸሎት፣ ምጽዋዕት እና ጾም እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ላይ የምናጠፍው ኃይል ዘለዓለም የሆነ ሐብት እንዲኖረን ያስችለናል።

ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፡ “ንብረትህ ባለበት ቦታ በዚያው ልብህ ይገኛል” (ማቴ 6፡21)። ልባችን ሁልጊዜ በተወሰኑ አቅጣጫዎች ላይ ይጠቁመናል: አንድ ውጤት ለማግኘት እንደ ሚፈልግ የአቅጣጫ መጠቆሚያ መሣሪያ ነው። እንዲሁም ልባችንን ሁሉንም ነገር ለራሱ ሰብስቦ ለመያዝ ከሚፈልገው ከማግኔት ጋር ማነጻጸር እንችላለን። ነገር ግን ልባችን ምዳርዊ የሆኑ ነገሮችን ብቻ ሰብስቦ ለመያዝ የሚሞክር ከሆነ ዛሬ ይሁን ወይም በቅርብ ጊዜ የእነዚያ ነገሮች ባሪያ መሆኑ አይቀርም። መልካም ገጽታችንን ብቻ ለመገንባት፣ ገንዘብ ለማግኘት፣ ስኬቶቻችንን እና ፍላጎቶቻችንን ብቻ ለማሳካት የምንጥር ከሆንን እነርሱ የእኛ ጣዖታት ይሆናሉ፣ ባሪያዎቻቸውም ያደርጉናል፣ እኛን በማማለል ወደ እነርሱ ውስጥ ገብተን እንድንሰምጥ ያደርጉናል። ነገር ግን ልባችን ከማያልፉ ነገሮች ጋር ተጣብቆ ወይም ተጣምሮ እንዲቆይ የምናደርግ ከሆንን ግን ራሳችንን እንደገና መልሰን እናገኛለን ነፃ እንሆናለንም። ዐብይ ጾም ልባችንን ከንቱ ከሆኑ ነገሮች ነጻ ማውጣት እንችል ዘንድ ጸጋውን የምናገኝበት ወቅት ነው። የዐብይ ጾም ወቅት እኛን ከሚያባብሉን ሱሶች ነጻ የምንሆንበት ወቅት ነው። አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ብቻ እይታችንን የምናደርግበት ወቅት ነው።

በዚህ በዐብይ ጾም ወቅት ትኩረት ሰጥተን እይታችንን ልናደርግበት የሚገባው ነገር ምንድነው? በተሰቀለው በኢየሱስ ላይ ሊሆን ይገባዋል። በመስቀል ላይ የተሰቀለው ኢየሱስ ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚመራን የሕይወት አቅጣጫ መጠቆሚያ መሳሪያችን ነው። የእንጨቱ (መስቀል የተሠራበት እንጨት) ምስኪንነት፣ የጌታ ዝምታ፣ በፍቅር ምክንያት ራሱን ያዋረደበት ሂደት ስለ ነገሮች ከመጨነቅ ይልቅ ቀለል ያለ ሕይወት መኖር አስፈላጊ መሆኑን ያሳየናል። በመስቀል ላይ ያለው ኢየሱስ ጊዜያዊ የሆኑ ነገሮችን እንድናስወግድ ታላቅ ብርታት ይሰጠናል። እኛ ከባድ የሆነ ሸክም ከተሸከምን ወደ ፊት መራመድ ይከብደናል። ቁሳቁሶችን የማግበስበስ ባሕሪያችንን በመተው፣ ራሳችንን ከስሜታዊነት እና በእራስ ወዳድነት መንፈስ በመነጨ መልኩ ከሚያስጨንቁን ነገሮች ራሳችንን ነጻ በማውጣት፣ ሁሉንም ነገር ለራሳችን ብቻ ከማግበስበስ ይልቅ ልባችንን ለድሆች ልንከፍት ይገባል። በፍቅር ከመንደዱ የተነሳ በእንጨት በተሰራ መስቀል ላይ ያለው ክርስቶስ፣ በዓለም ውስጥ እንዳለው አቧራ በነን እንዳንቀር ወደ ሕይወት መንገድ እንድንመለስ ይጋብዘናል። እርሱ እንደ ሚፈልገው መኖር ይከብደናል ወይ? አዎን በጣም ከባድ ሊሆን ይችል ይሆናል፣ ነገር ግን እርሱ ወደ ግባችን ይመራናል። የዐብይ ጾም ወቅት ይህንን መንገድ ያሳየናል። የዐብይ ጾም ወቅት ዐመድ በመቀባት መንፈሳዊ ሥነ-ሥረዓት ይጀምርና በፋሲካ ምሽት በሚለኮሰው ሻማ የሚጠናቀቅ ሲሆን ይህም በመቃብር ውስጥ የነበረው የኢየሱስ በድን ዐመድ ሆኖ እንዳልቀረ በማሳየት በክብር መነሳቱን በማብሰር ይጠናቀቃል። ይህ እኛም የሚገጥመን እውነታ ነው፣ አቧራ ሆነን አንቀርም። ከነድክመታችን ወደ ጌታ ከተመለስን፣ በፍቅር ጎዳና ላይ መራመድ ከጀመርን ማለቂያ የሌለውን የዘለዓለም ሕይወት እንወርሳለን። ሙሉ በሙሉ ደስተኞች እንሆናለን።

06 March 2019, 08:43