ፈልግ

የስጦታ ልውውጥ የስጦታ ልውውጥ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ፕሬዚዳንት ምስጋናን ተቀበሉ።

በቅድስት መንበር እና በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ መካከል ከዚህ በፊት የተደረሱት የጋራ ስምምነቶች መልካም ፍሬዎችን እያስገኙ መምጣታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ፋውስቲን አርካንጄ ቷዴራ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ምስጋና ማቅረባቸው ተገለጸ። በአገራቸው የሰላም ተስፋ ጭላንጭል፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማደግ እና በዋና ከተማ አዲስ ሆስፒታል መገንባቱ ያስደሰታቸው የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ፋውስቲን አርካንጄ በቫቲካን ተገኝተው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልባዊ ምስጋና ማቅረባቸውን የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ያደረገችው እገዛ፣

በቅድስት መንበር እና በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ መካከል ከዚህ በፊት የተደረሱት የጋራ ስምምነቶች መልካም ፍሬዎችን እያስገኙ መምጣታቸውን ከቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል የተሰራጨ ዘገባ አስታውቋል። ሃገሪቱ በምታካሂዳቸው የትምሕርት እና የጤና አገልግሎት፣ በጠቅላላው በአገሪቱ የልማት ዘርፍ ውስጥ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ እና መንፈሳዊ ተቋማት ያበረከቱት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዘግቧል። ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ የምታበረክተውን ማሕበራዊ እና መንፈሳዊ ድጋፍን እና በቅርቡ በዋና ከተማ በባንጊ ሥራው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን ሆስፒታል ያስታወሱት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ፋውስቲን አርካንጄ፣ በቫቲካን ተገኝተው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሰላም ማበረታቻ፣

ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ አሁን የደረሰችበትን የሰላም እና የመረጋጋት ሁኔታን አስመልክተው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ባደረጉት ውይይት በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ተገናኝተው ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የእርስ በእርስ ግጭቶች በማስወገድ ለሰላም እና ለእድገት የሚያበቃቸውን ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ፕሬዚዳንት ፋውስቲን ገልጸዋል። በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች በውይይታቸው ወቅት በሰላም አብሮ መኖርን፣ ብሔራዊ እርቅን፣ ከእንግዲህ ወዲህ አመጽ እንዳይከሰት ጥረት ማድረግን እና በአመጽና በጦርነት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን ወደ የአካባቢያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ፕሬዚዳንት ፋውስቲን አስታውቀዋል። 

የስጦታ ልውውጥ አድርገዋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ በበኩላቸው ዘንድሮ በተከበረው በዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ያስተላለፉትን የሰላም መልዕክት እትም ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ፕሬዚዳንት ለክቡር አቶ ፋውስቲን አርካንጄ በስጦታ መልክ ያበረከቱ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ በአረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በአቡ ዳቢ የተደረሰው እና “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል ርዕሥ የሚታወቀውን የስምምነት ሰነድ ማበርከታቸው ታውቋል። ክቡር ፕሬዚዳንት ፋውስቲን አርካንጄ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ካደረጉት ቆይታ መልስ ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ከብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ጋርም መገናኘታቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ያደረጉት ጉብኝት፣

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ፕሬዚዳንት ፋውስቲን አርካንጄ ቀጥለው በሮም ከተማ የሚገኘውን የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትን የጎበኙ ሲሆን በዚህ ጊዜ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ2007 ዓ. ም. ወደ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሕዝብ ልብ ውስጥ ታሪካዊ ትዝታን ፈጥሮ መቆየቱን ገልጸዋል።

ሃገራቸው ሰላምን እና እርቅን ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል ገልጸው ወደ ኢጣሊያ ያደረጉትን ጉብኝት ከመጀመራቸው ከጥቂት ቀናት በፊት በዋና ከተማ በባንጊ በአገሪቱ ብቸኛ የሆነውን የሕጻናት ሆስፒታል መርቀው ለአገልግሎት መክፈታቸውን ገልጸዋል። ይህም ሃገርቱ እድገትን ለማምጣት ብላ ለጀመረችው ጉዞ መነሻ ይሆናል ብለዋል። ከቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር ጋር በመሠረቱት ወዳጅነት በሃገሪቱ ሰላምን እና እርቅን ለማውረድ በጋራ እንደሚሰሩ አስረድተው በቅርቡ በአገሪቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጋር በሰላም አብሮ መኖርን፣ ብሔራዊ እርቅን ለማድረግ፣ አመጾች ተመልሰው እንዳይከሰቱ ጥረት ማድረግን እና በጦርነት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን ወደ የአካባቢያቸው ለመመለስ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 March 2019, 14:54