ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ያልታረመ አንደበት ጦርነትን ሊያስከትል ይችላል”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሁድ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ. ም. በሮም ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ቁምስናዎች መካከል አንዱ የሆነውን የቅዱስ ክሪስፒኖ ዳ ቪተርቦ ቁምስናን ጎብኝተዋል። በመስዋዕተ ቅድሴው ጸሎት ለተገኙት ምእመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል ለክርስትና ሕይወት ድጋፍ ከሚሆኑን መንገዶች መካከል ሁለቱን ጠቅሰው እነርሱም ተስፋን ማድረግ እና ሐሜትን ማስወገድ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዋዜማው የጸሎት ስነ ስርዓት ለተገኙት ምእመናን የቤተክርስቲያኑ ቆሞስ የሆኑት ክቡር አባ ሉቺያኖ ካቻማኒ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ቁምስናቸው የሚያደርጉት ጉብኝት በምዕመናኑ መካከል ደስታን እንደጨመረ ተናግረው ቁምስናቸው በምዕመናን ብዛት ይህን ያህል የሚጠቀስ ባይሆንም የተለያዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማሕበራት የሚገኙበት፣ ከቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር ጋር በመተባበር የተለያዩ የፍቅር አገልግሎቶችን የሚያበረክት ቁምስና እንደሆነ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመስዋዕተ ቅድሴው ስነ ስርዓት አስቀድመው የቁምስናውን ሕጻናት፣ በቅርቡ ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበሉ ሕጻናትን እና ወላጆቻቸውን፣ ምስጢረ ሜሮንን የተቀበሉ ታዳጊዎችን፣ በቁምስናው ከሚታገዙ ደሃ ቤተሰቦችን እና ሕሙማንን ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴውን ስነ ስርዓት የመሩት ብጹዕ ካርዲናል ደ ዶናቲስ የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ጉዌሪኖ ዲ ቶራ፣ የሰሜናዊው ሮም ከተማ ጳጳስ፣ ክቡር አባ ሉቺያኖ ካቻማኒ፣ የቅዱስ ክርስፒኖ ቤተክርስቲያን ቆሞስ እና የቁምስናው ረዳት ካህን ክቡር አባ አንድሬያ ላሞናካ መሆናቸው ታውቋል።

ከሉቃስ ወንጌል በምዕ. 6፣ ከቁጥር 39-45 ተውስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ “በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ራስህ ሳታይ፥ እንዴት ወንድምህን፣ ወንድሜ ሆይ፥ በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ” በሚለው ጥቅስ አስተንትኖን ያደረጉት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ምሳሌ ሲያቀርብልን የሌላን ሰው ጉድለት ከመመልከት ወይም ከመናገር አስቀድሞ የራስን ጉድለት በሚገባ መመልከት እንዳለብን ሊያስተምረን መፈለጉን አስረድተዋል።  

“እኛ ሁላችንም የየራሳችን ድክመቶች አሉብን፣ ነገር ግን በልማድም ሆነ በራስ ወዳድነት የተነሳ የራሳችንን ጉድለቶች ከመመልከት ይልቅ የሌሎችን ጉድለቶች መመልከት እንመርጣለን። የሌሎችን ጉድለቶች በመመልከት ጎበዞች ነን፣ ምክንያቱም የሌሎችን ስህተት ወይም ድክመት ማውራት የሚያስደስተን ስለሚመስለን ነው። ምናልባት በቁምስናችሁ አልተለመደም ይሆናል። በሌሎች ቁምስናዎች ያጋጥማል”።

የሌሎችን ጉድለቶች ለመመልከት ጎበዞች ነን፣

አስቀድሞ የራስን ጉድለቶች ከመመልከት ይልቅ የሌሎችን ጉድለቶች በመመልከት ፍርድን መስጠት መጥፎ ልማድ እንደሆነ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የሚያደርጉትን በሙሉ ግብዞች ናቸው ማለቱን አስታውሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ መንገድ ተመልሰን የሌሎችን ጉድለት ከመመልከት ይልቅ የራሳችንን ጉድለቶች መመልከት እንደሚያስፈልግ ያስተምረናል ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊትም እንዳስገነዘቡት ሁሉ ሐሜት ወደ ጥፋት ሊመራ የሚችል አደገኛ ልማድ እንደሆነ አስረድተዋል።

“ሐሜት ከሐሜትነት አልፎ ንትርክን፣ ጥላቻን እና ክፋትን ይወልዳል። ማጋነኔ አይደለም፣ ጦርነት የሚጀምረው ከአንደበት ከሚወጣው ክፉ ንግግር ነው። ሌሎችን የሚያማ ሁሉ ጦርነትን ይቀሰቅሳል፣ ይህ ጦርነት ጥፋትን ያስከትላል። በሐሜት የሌሎችን ስም ማጥፋት እና በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጦርነት አንድ ናቸው። ይህን እኔ ሳልሆን ቅዱስ ወንጌልን ወስዳችሁ ያነበባችሁ ከሆነ ሐዋርያው ያዕቆብ በመልዕክቱ ተናግሮታል”።  

ሰው ሆኖ ጉድለት የሌለበት አይኖርም ያሉት ቅዱስነታቸው በዚህን ጊዜ ይህን ሰው በአካል ቀርቦ መምከር እና መገሰጽ እንጂ በሐሜት ስሙን ማጥፋት ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረው የሐሜት ፍሬ መቀያየም እንጂ ሌላ ፋይዳ የለውም ብለዋል። በጾም ወራት በምናደርገው የጸሎት እና የጾም ተጋድሎ በመታገዝ ከማይመቹ እና ከማይጠቅሙ ልማዶች መላቀቅ እንደሚያስፈልግ በምክራቸው አስታውሰዋል።

“የጾም ጊዜን ጀምረናል፣ በዚህ የጾም ወቅት እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት፣ ለሌሎች ሰዎች ያለኝ ፍቅር ምን ያህል ነው? ብሎ ቢያስብ መልካም ነው። ሐሜተኛ ነኝን? አስመሳይ ነኝን? እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ራሳችንን ብንጠይቅ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ በሕይወታችን ትልቅ ለውጥን የሚያመጣ እና ያማረ ይሆናል” ብለዋል።

እነዚህን ጥያቄዎች በማንሳት ራስን በመመርመር ወደ ለውጥ መድረስ ቀላል ጉዞ እንዳልሆነ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ውጤታማ ለመሆን የሚያግዙን ሁለት ነገሮች እንዳሉ፣ የመጀመሪያው ጸሎት ሲሆን ሁለተኛው ሐሜትን ማስወገድ እንደሆነ አስረድተዋል። በጸሎት ከእግዚአብሔር በሚገኝ ሃይል ከችግሮች መውጣት እንደሚቻል ገልጸው በአንደበታችን የሌሎችን ድክመት ከማውራት መቆጠብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ለቤተክርስቲያን መጸለይ ያስፈልጋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ክርስፒኖ ዳ ቪተርቦ ቁምስና ተገኝተው ካሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት በመቀጠል የቁምስናው ምዕመናን ላደረጉላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው፣ መልካም የጾም ወቅት እንዲሆንላቸው ተመኝተውላቸዋል። ምዕመናኑ መላዋን ቤተክርስቲያን እና እርሳቸውንም በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለው ከምዕመናኑ ጋር ሆነው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበዋል። መላው የቁምስናው ምእመናንም በቅዱስነታቸው ጉብኝት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 March 2019, 15:40