ፈልግ

ስለ ር. ሊ. ጳ. ፒዮስ 12ኛ የሚናገሩ ሰነዶች ከአንድ ዓመት በኋላ ይፋ እንደሚሆኑ ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሰኞ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቫቲካን ውስጥ በቅለመንጦስ አዳራሽ ለተቀበሏቸው የቫቲካን መዝገብ ቤት ሠራተኞች ባሰሙት ንግግር፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ስለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የሚናገሩ ሰነዶች ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ለመዝገብ ቤቱ ሠራተኞች እንደገለጹት ከዚህ በፊትም ስለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፒዮስ 12ኛ ብዙ የተነገረ እና የሚታወቅ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ሌላ ገጽታ ሲሰጥበት መቆየቱን አስታውሰው፣ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ዘመናቸው ችግሮች የበዙባቸው የጨለማ ጊዜ ነበር ብለዋል። በማከልም ከሌላው ዓለም ጋር ግልጽ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የነበረበት እና ልባዊ ወዳጅነት የታየበት እንደነበር አስረድተዋል።

ከ81 ዓመት በኋላ ማለትም በሚቀጥለው ዓመት የካቲት 23 ቀን 2012 ዓ. ም. ስለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ጊዜን በግልጽ የሚያስረዱ ሰነዶችን የያዘው የቫቲካን መዝገብ ቤት ክፍት እንደሚሆን ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቫቲካን መዝገብ ቤት ሰራተኞች፣ ጥንትዊ የሆኑ የቫቲካን መዝገቦች፣ ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ በአዲስ መልክ እንዲቀመጡ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ትዕዛዝ መሠረት፣ ከ1998 ዓ. ም. ጀምሮ ላበረከቱ ሰፊ ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመዝገብ ቤቱ ሠራተኞች ባቀረቡት የምስጋና ንግግራችው ከቫቲካን መዝገብ ቤት ሠራተኞች ጋር ሆነው እገዛን ላደረጉ የታሪክ ምሁራንን በሙሉ አመስግነው፣ ስለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እስከ እረፍታቸው ድረስ የተጻፉትን ሰነዶች ለታሪክ ተመራማሪዎች በሙሉ ክፍት እንዲሆን ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

አንዳንድ ግምታዊ ሃሳቦች እና ማጋነኖች፣

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነበሩ። በርካታ አገሮች በአመጾች እና በጦርነቶች ውስጥ በገቡበት አስቸጋሪ በነበረ ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በብቃት እና በታማኝነት አገልግለዋል። እነዚያ የጨለማ ዓመታትም ካለፉ በኋላ በጦርነት የወደሙትን እና የተጎሳቆሉ አገሮችን መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ጥረቶችን አድርገዋል” ብለዋል።  

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ አገልግሎትን አስመልክቶ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል፣ ብዙ ምርምሮች ተደርገዋል፣ ወቀሳዎችም ቀርበዋል። እነዚህ ጥያቄዎችም ማጋነን የታዩባቸው እና በግምታዊ ሃሳቦች ላይ የተመሠረቱ ናቸው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ዛሬ ላይ ስንደርስ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው፣ ስነ መለኮታዊ አስተምህሮ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ወደ ትክክለኛው ብርሃን የወጣበት እና እውነቱ የታየበት ሁኔታ አለ።

እውነተኛ ብርሃን፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ ስነ መለኮታዊ አስተምሕሮ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁለቱ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ጊዜ ማለትም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ፓውሎስ 6ኛ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የሐዋርያዊ አገልግሎት ዘመን በስፋት ጥናት መደረጉን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል።      

“የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በሚገባ ለመገንዘብ ዓላማዬ ብሎ የተነሳ ሁሉ ጥናቶችን እና ምርምሮችን በምካሄድ፣ ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ ፍሬያማ የሆኑ የሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ውጤቶች፣ ክርስቲያናዊ እና ሰብዓዊ ጥንቃቄ የታከለበት የአገልግሎት ጥበባቸውን፣ እንዲሁም ያጋጠሟቸውን እንቅፋቶችን እና እንቅፋቶችን ለማለፍ የወሰዷቸውን መንገዶች እና ተስፋ ያደረጉበትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን እና ያሳዩትን ልባዊ ፍቅራቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ታሪክን መውደድ ያስፈልጋል፣

ጥንታዊ ታሪኮችን የያዙ መዛግብትን በአግባቡ ማንበብ ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተክርስቲያን ታሪክን አትፈራም ብለው እግዚአብሔርም ታሪክን እንደወደደ ሁሉ ቤተክርስቲያንም ታሪክ ትወዳለች ብለዋል።

የቫቲካን መዝገብ ቤት ሠራተኞች ተግባር፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቫቲካን መዝገብ ቤት ሠራተኞችን፣ እና የግምጃ ቤቱ ተለያዩ ክፍሎች የሥራ ሃላፊዎችን በሙሉ ለአገልግሎታቸው ምስጋናቸውን አቅርበው መዝገብ ቤቱ ለታሪክ ተመራማሪዎቹ፣ ጥናታዊ ሥራቸውን ለሚያካሂዱ የታሪክ ባለሞያዎች አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
04 March 2019, 17:34