ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የሮም ከተማ ዛሬም ቢሆን ሰዎችን የሚያስተናግድ ይሁን”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. የሮም ከተማ ማዘጋጃ ቤትን በመጎብኙበት ወቅት ከከተማው አስተዳደር ጋር የተገናኙ ሲሆን፣ ለማዘጋጃ ቤቱ የአገልግሎት ዘርፍ የሥራ አመራሮች ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከንግግራቸው አስቀድሞ ለሮም ከተማ ከንቲቫ ለሆኑት ወይዘሮ ቨርጂኒያ ራጂ፣ ለአማካሪዎቻቸው እና የተለያዩ መምሪያ ሃላፊዎች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማከናወን እድል በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ለግብዣውም የማዘጋጃ ቤቱን አስተዳደር አመስግነዋል። በዚህ አጋጣሚ በቦታው ለተገኙት የመንግሥት ተወካዮችና ለመላው የሮም ከተማ ነዋሪዎች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

የሮም ከተማ ማዘጋጃ ቤትን ለመጎብኘት የረጅም ጊዜ ምኞት እንደነበራቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ማዘጋጃ ቤቱ ከቅድስት መንበር ጋር በመተባበር የምሕረት ዓመት ኢዮቤልዩ እና ሌሎችንም ታላላቅ በዓላት በሚያኮራ አኳኋን እንዲከበሩ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ላበረከቱት ክፍሎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በማከልም ሕዝባዊ እና የቤተክርስቲያን ተቋማት በመተባበር ያበረከቱት አገልግሎት መልካም ውጤቶችን እንዳስገኘ ገልጸው የሮም ከተማ ከዘመናት ወዲህ ክርስትናን በተለይም ካቶሊካዊ እምነትን በማስተናገድ የሚታወቅ ከተማ እንደሆነ አስረድተዋል።

የሮም ከተማ፣ ቀዳሚ የሕግ ንድፍ የወጣበት፣ የጠቢባን ሕዝቦች ተሳትፎ ያለበት፣ በውስጡም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኝበት፣ የፍልስፍና እና የስነ ጥበብ፣ የጥንታዊ ባሕል ማዕከል፣ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ደማቸውን በማፍሰስ ሰማዕትነትን የተቀዳጁበት እና የክርስትና እምነት እንዲያብብ የተደረገበት፣ የብራሃን እና የጨለማ ዘመናት ቢፈራረቁበትም ታሪክን በማቆየት የሚታወቁ ሕንጻዎች እና ቅርጻ ቅርጾች የሚገኙበት ከተማ መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ 2,800 ዓመት የሚጠጋ ዕድሜ ያለው የሮም ከተማ በረጅም ዕድሜው ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚመጡ፣ ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ልዩነት ያሏቸው ሕዝቦች ሲስተናገዱበት እንደቆየ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ከተማው የእነዚህን ሕዝቦች ማንነት በማክበር፣ እርስ በእርስ በመመካከር አንዱ ለሌላው ማድረጋ ያለበትን እገዛ በመጋራት እንደቆየ አስረድተዋል።

የሮም ከተማ ተማሪዎችን፣ መንፈሳዊ ተጓዦችን፣ ጎብኝዎችን እና ከኢጣሊያ እና ከተቀሩት የዓለማችን አካባቢዎች የሚመጡ ስደተኞች የሚገኝበት ከተማ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው የሮም ከተማ የብዙ ሕዝቦች መስህብ እና ዋና ምሰሶ ከመሆኑም በላይ የስልጣኔዎች መገናኛ ሆኗል ብለዋል። የወንጌል እሴቶችን በተግባር በመግለጽ፣ ለእርስ በእርስ መከባበር እና ለጋር ጥቅም በማለት የመንግሥት እና የቤተክርስቲያን ተቋማት የሚተጋገዙበት፣ ሰብዓዊ መብቶችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት የሚደረግበት፣ የሕዝቦች ነጻነት ተረጋግጦ በማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች የሚሳተፉበት ከተማ መሆኑን አስረድተዋል።

የሮም ከተማ የኢጣልያ ዋና ከተማ ከመሆኑም በላይ የካቶሊክ እምነት ማዕከል እነደሆነም የገለጹት ቅዱስነታቸው የካቶሊክ እምነት ማዕከል በመሆኑ በርካታ ሰማዕታት የሚታወሱበት፣ ትላልቅ ዓመታዊ በዓላት በድምቀት የሚከበሩበት፣ የኢዮቤልዩ ንግደቶች የሚደረጉበት ከፍተኛ የኢጣሊያ እና የቅድስት መንበር የትምህርት ተቋማት የሚገኙበት ከተማ እንደሆነ አስረድተዋል። በመሆኑም የሮም ከተማ የተለያዩ ማሕበራዊ እና መንፈሳዊ ተቋማት በጋራ ሆነው በየጊዜው የሚያጋጥሙ ማህበራዊ ችግሮችን በጋራ እንዲያስወግዱ የማድረግ ግዴታ አለበት ብለዋል።

ከ45 ዓመታት በፊት በከተማው የሚገኙት ክርስቲያናዊ እና መንግሥታዊ ተቋማትን በደረሳቸው ጥሪ መሠረት በሮም ሀገረ ስብከት አስተባባሪነት ፍትሃዊነትን የተላበሱ የእርዳታ መስጫ ማዕከላት መኖራቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዓመታት ወዲህ ከብዙ አገሮች የሚመጡ የእርዳታ ፈላጊ ቁጥር መበራከቱን ገልጸው ጦርነትን እና ድህነትን ሸሽተው ለሚመጡት ስደተኞች በሙሉ አስፈላጊው ቁሳዊ እና መንፈስዊ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ቅድስት መንበር ከከተማው አስተዳደር ጋር በመሆን  ከዚህ በፊት የምታደርገውን ድጋፍ ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠው የሮም ከተማ አስተዳር ለከተማው ዕድገት የሚያደርገውን መጠነ ሰፊ ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

በመጨረሻም የእመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥበቃ፣ የሮም ከተማ ባልደረባ የሆኑት ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ እንዲሁም የቅዱሳን ሁሉ እገዛን ተማጽነው የእግዚአብሔርን ቡራኬ ከሰጡ በኋላ በጸሎታቸውም እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠውላቸዋል።             

26 March 2019, 17:18