ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እናንተ ስደተኞች በቤተክርስቲያኗ ልብ ማዕከል ውስጥ ትገኛላችሁ” አሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከመጋቢት 21-22/2011 ዓ.ም 28ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በሞሮኮ በማድረግ ላይ እንደ ሆኑ መግለጻችን ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሞሮኮ ለሚያደርጉት 28ኛው ሐዋርያዊ ግጉብኝት የተመረጠው መሪ ቃል “የእግዚኣብሔር አገልጋዮች አገልጋይ”  የሚለው ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 21/2011 ዓ.ም በዚያው በሞሮኮ ዋና ከተማ በራባት በሚገኘው እና ካሪታስ በመባል በሚታወቀው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የእርዳታ መስጫ ድርጅት ተቋም ውስጥ የሚገኙትን ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ስደተኞችን መጎብኘታቸው የተገለጸ ሲሆን “እናንተ ስደተኞ የቤተ ክርስቲያን ልብ ማዕከል ውስጥ ትገኛላችሁ” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በሞሮኮ በራባት አገረ ስብከት ሥር በሚገኘው የካሪታስ የእርዳታ መስጫ ተቋም ውስጥ የሚገኙትን ከተለያዩ አገራት የተውጣጡትን ስደተኞች ቅዱስነታቸው በጎበኙበት ወቅት እንደ ገለጹት “የእናንተ ቁስል እና ስቃይ ወደ ሰማይ ይጮኸል” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን “በዚህ ጉብኝቴ አሁንም ቢሆን በድጋሚ ለእናንተ ያለኝን አጋርነት ለመግለጽ በማሰብ ያደረኩት ጉብኝት ነው፣ ለእናንተ ያለኝን ቅርበት ለመግለጽ እፈልጋለሁ፣ በእናተ ውስጥ የሚገኘውን ስቃይ እና ቁስል ለመጋራት እፈልጋለሁ፣ ይህ የእናንተ ስቃይ እና መከራ አሁን ባለንበት በ21ኛ ክፍለ ዘመን እየተከሰተ የሚገኝ ሁኔታ መሆኑ ደግሞ በጣም የሚያስገርም ነው፣ ለቅሶዋችሁ እንዲሁ በከንቱ አይቀርም ወደ ሰማይ ይጮኸል” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ለስደተኞቹ ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት “እናንተ አልተገለላችሁም፣ እናንተ አሁንም ቢሆን የቤተ ክርስቲያን ልብ ማዕከል ውስጥ ትገኛላችሁ” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪም “ውድ ስደተኞ በጉዞዋችሁ ውስጥ ያጋጠማችሁን መከራ እና ስቃይ ቤተ ክርስቲያን በሚገባ ትረዳልች፣ የእናንተንም ስቃይ ትጋራለች? ብለዋል። እያንዳንዱ ሰው የመኖር መብት እንዳለው፣ እያንዳንዱ ሰው ሕልም የማለም እና የጋራ መኖሪያ ቤታችን በሆነችው ዓለማችን ውስጥ ለራሱ የሚሆን ተገቢ ስፍራ የመምረጥ መብት እንዳለው ጨምረው የገለጹት ቅዱስነታቸው “እያንዳንዱ ሰው ስለ መጪው ጊዜ ሕይወቱ የመጨነቅ እና ይህንንም እውን ለማድረግ የመስራት መብት እንዳለው ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

31 March 2019, 12:24