ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በራባት ቤተመንግሥት ውስጥ ተገኝተው የመጀመሪያ ንግግር ሲያደርጉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በራባት ቤተመንግሥት ውስጥ ተገኝተው የመጀመሪያ ንግግር ሲያደርጉ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የጋራ ግንኙነት ለሰላም እና ለሰብዓዊ ወንድማማችነት መሠረት ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በራባት ቤተመንግሥት ውስጥ ተገኝተው ለሞሮኮ ሱልጣን ሞሃመድ 6ኛ፣ የተለያዩ የሞሮኮ ሕዝብ ተወካዮች፣ ባለ ስልጣናት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ ለተለያዩ አገራት ዲፕሎማቲክ አካላት ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። የቅዱስነታቸውን ንግግር ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ንጉሥ ሆይ!   የተከበራችሁ የሞሮኮ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣    የተለያዩ አገራት ዲፕሎማሲ አካላት፣    ክቡራን እና ክቡራት ወዳጆቼ፣

ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን፣

በዚህች ታሪካዊ ምድር እግሬን በማሳረፍ፣ የተፈጥሮ ውበቷን ለመመልከት በመቻሌ፣ መልካም ፍሬን በማስገኘት ላይ የሚገኘውን ጥንታዊ ታሪኳን በክብር በማቆየታችሁ የተሰማኝ ደስታ ከፍተኛ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ። ከሁሉም አስቀድሜ አገራቸውን እንድጎበኛ ዕድል ለሰጡኝ ለንጉሥ ሞሐመድ 6ኛ ልባዊ ምስጋናዬን እያቀረብኩ በመላው የሞሮኮ ሕዝብ ስም ላደረጉልኝም ደማቅ አቀባበል አመሰግናለሁ።     

ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ የአገራችሁን ጸጋ፣ ሕዝብ እና ባሕላችሁንም እንድመልከት እድል ስለ ሰጠኝ የደስታ እና የምስጋና ጉብኝት እንደሆነ እረዳለሁ። በተጨማሪም ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረገውን የጋራ ውይይት ወደ ፊት ለማራመድ ትልቅ አጋጣሚን የሚከፍት በመሆኑ እና ከዛሬ 800 ዓመት በፊት ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና ሱልጣን አል ማሊክ አል ካሚል ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት ዓመት የሚታወስበት ወቅት በመሆኑ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እነዚህ ሁለቱ ወንድሞቻችን ያደረጉት ድፍረት የተሞላበት ትንቢታዊ ግንኙነት በሰው ልጆች መካከል የአንድነትን እና የሰላም መንገድ ለማበጀት የሚረዳን መሆኑን እንገነዘባለን። ይህ ባይሆን ኖሮ እስከ ዛሬ ድረስ አክራሪነት እና ጥላቻ ተስፋፍቶ መለያየትን እና ውድመትን እንደሚያስከትል እናውቃለን። ስለዚህ በመካከላችን ያለው መልካም የእርስ በእርስ ግንኙነት፣ መከባበር እና መረዳዳት እውነተኛ ወዳጅነትን በማሳደግ ማሕበረሰባችን ለመጭው ትውልድ መልካም ዕድሎችን እንዲያመቻች ያግዘዋል ብዬ ተስፋ አደራጋለሁ።

አውሮጳን እና አፍሪቃን ለማገናኘት የተፈጥሮ ድልድይ በሆነው በሞሮኮ ሆኜ አንድነታችንን ለማሳደግ የሚያስችሉ አዳዲስ ሃሳቦችን ለመስጠት፣ እርስ በእርስ በመተማመን በሕብረት የቆመ ዓለምን ለመገንባት፣ የእያንዳንዱን ሕዝብ የጋራ እና የግል ማንነትን ያከበሩ ሰላማዊ የጋራ ውይይቶችን ለማድረግ ያለኝን ከፍተኛ ፍላጎት አረጋግጣለሁ። በግጭቶች እና በጦርነቶች ምክንያት ልዩነቶች በተጋነኑበት፣ እርስ በእርስ ለመቀራረብ ያለን ፍላጎት አደጋ ላይ በወደቀበት ባሁኑ ወቅት እያንዳንዳችን ይህን ችግር ለማስወገድ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ማሕበረሰባችንን ለመገንባት፣ ወንድማማችነትን ለማሳደግ እና ልዩነታችንን ተቀብለን ለማክበር የምንፈልግ ከሆነ፣ ዘላቂ የውይይት ባሕል፣ መተጋገዝ እና አንዱ ሌላውን ማወቅ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እናውቃለን። በፍርሃት እና በልዩነት ምክንያት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን እና ውጥረቶችን ለማስወገድ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል እርስ በእርስ መተባበር ያስፈልጋል። ይህን የምናደርግ ከሆነ የእደገት እና የመከባበር መንፈስ እንዲፈጠር ማድረግ እንችላለን። በዚህ መንገድ በሰዎች መካከል በሚታዩ የአክራሪነት አቋምን በአንድነት እሴቶች እና በመልካም ተግባር በመታገዝ ልናስወግድ እንችላለን። ስለሆነም የሞሐመድ 6ኛ የእልምና እምነት መምህራን እና ኢማሞች ማሰልጠኛ ከፍተኛ ተቋምን ለመጎብኘት በመምጣቴ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል። በግርማዊነታቸው ፍላጎት የተቋቋመው ይህ ከፍተኛ የማሰልጠኛ ተቋም የአመጽ እና የአሸባሪነት አመል፣ በሃይማኖትም ሆነ በአምላክ ላይ በደልን ለመፈጸም የሚያደፋፍር የጽንፈኝነትን አቋም ለመዋጋት የሚያስችል በቂ እውቀት የሚገኝበት ማሰልጠኛ ማዕከል ነው። በመጭው ትውልድ ልብ ውስጥ ትክክለኛ የእምነት መንፈስን ለማስረጽ ብቃት ያላቸውን መምህራንን ማፍራት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን።

ግልጽ እና እውነተኛ የሆኑ የጋራ ውይይቶች ማድረግ የእምነትን ጠቃሚነት እንድናውቅ፣ የተለያዩ ሕዝቦች የሚገናኙበትን ድልድይ ለመገንባት እና በማሕበረሰብ መካከል የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቋቋም ያግዛል። ልዩነቶቻችንን አሜን ብሎ መቀበል እና እምነትን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ የእያንዳንዱን ሰው የማይሻር ሰብዓዊ መብትን እና ክብርን ለመጠበቅ ያግዛል። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የፈጠረው እኩል መብትን እና ክብርን በመስጠት በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት መንፈስ በሕብረት እንዲኖሩ፣ የመልካምነት መገለጫ የሆኑትን  ፍቅርን እና ሰላምን በመስጠት እንደሆነ እናምናለን። የህሊና እና የሃይማኖት ነጻነት በእምነት ነጻነት ብቻ የተገደበ ሳይሆን ምን ጊዜም ሊነጣጠል ከማይችል ከሰብዓዊ ክብር ጋር አንድ ሆኖ የሚታየው በዚህ ምክንያት ነው። ስለዚህ በእምነቶች መካከል የሚደረግ ውይይት እርስ በእርስ በመተዋወቅ ወዳጅነትን እና ወንድማማችነትን እንድናሳድግ ያሳስበናል።

የእስልምና እምነትን በሰፊው በሚያራምዱ አገሮች ውስጥ የሚገኙ በቁጥር ዝቅተኛ የሐይማኖቶት ወገኖች ጉዳይ ለመመልከት በታህሳስ ወር 2008 ዓ. ም. በሞሮኮ ማራከሽ ከተማ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በእነዚህ ዝቅተኛ ቁጥር ባላቸው የእምነት ተከታዮች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና እና ግፍ በሙሉ ድምጽ በማውገዙ ደስታ ተሰምቶኛል። ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በእነዚህ የእምነት ተከታዮች ላይ የሚደርሰውን ስደት እና መከራን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን የዜግነት መብታቸውን እና ሰብዓዊ ክብራቸውን እንዲያጡ መደረጋቸውን  ተቃውሟል።

በሞሮኮ ውስጥ በ2004 ዓ. ም. የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት በጋራ ሆነው ያቋቋሙት ማዕከል ትንቢታዊ ምልክት የተገለጠበት አድርጌ እቆጥረዋለሁ። ይህ ማዕከል የተመሠረተው በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች ተነሳሽነት የተቋቋመ ቢሆንም ከተቀሩት ሐይማኖት ተቋማት እና ባሕሎች ጋር አንድነትን ለመፍጠር እንዲያስችል ነው። ይህ በጎ ዓላማ በሙስሊም አገሮች የሚገኙ በቁጥር ዝቅተኛ የሆኑ የክርስትያን ወገኖች ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያስችላቸውን ድልድይ ለመገንባት ፍላጎት ስላደረባቸው ነው።  

እነዚህ ጥረቶች የሚደረጉበት ዋና ዓላማ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚከሰተውን የጥላቻ፣ የአመጽ፣ የጽንፈኛነት፣ የአክራሪነት፣ በእግዚአብሔር ስም የሚደረጉ የጦርነት፣ የስደት እና የአሸባሪነትን አቋም በመቃወም ነው።

እውነተኛ እና መተማመን ያለበት የጋራ ውይይት ያስፈለገበት ምክንያት የምንኖርበትን የጋራ መኖሪያችን የሆነውን ዓለማችንን በሚገባ እንድናውቅ የሚያግዝ በመሆኑ ነው። የከባቢ አየር ለውጥን በማስመልከት በሞሮኮ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በርካታ አገሮች ዓለማችንን ከውድመት ለማዳን የተስማሙበት እና እግዚአብሔርም በምድር እንድንኖር አድርጎ ሲፈጥረን ለምድራችን ጥንቃቄን በማድረግ እና በመንከባከብ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት እንድናውለው በማሰብ ነው። በዚህ ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ በማበርከት የተባበሩትን አገሮችን እና ግለ ሰቦችን በሙሉ እያመሰገንኩ አሁን ቢሆን ዘላቂ መፍትሄ እስከሚገኝ ድረስ ጥረቱ እንዲቀጥል አደራ እላለሁ።

ሌላው አሳስቢ የሆነው የዓለማችን ችግር ስደት ነው። ለበርካታ ሰዎች እና ቤተሰቦች መበታተን፣ መሰደድ እና ክብራቸውንም ለማጣት ዋና መነሻ የሆኑ ችግሮችን በጋራ መዋጋት ያስፈልጋል። ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ዘንድሮ በታሕሳስ ወር በሞሮኮ አንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል። በጉባኤው ወቅት ቃል እንደተገባው ሁሉ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ሂደት በተግባር የመተርጎም ሥራ ነው። በተለይም ዓለም በስደተኞች ላይ ያለውን አመለካከት እንዲቀይሩ ማድረግ ነው። ዓለም መመልከት ያለበት የስደተኞች ቁጥር ሳይሆን ሰብዓዊ ፍጥረት መሆናቸው በመገንዘብ ለሰው ልጅ ሊሰጥ የሚገባው መብት፣ ነጻነት እና ክብር እንዳይጓደል ማድረግ ነው። በዚህም ምክንያት ባሁኑ ጊዜ በርካታ ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ የምትገኝ ሞሮኮ በድጋሚ ለዓለም መንግሥታት መልካም ምሳሌ ሆና እንድትቀጥል አደራ እላለሁ። የሚሰደዱ ሰዎች በአገራቸው ሁኔታዎች የተመቻቹ ቢሆን ኖሮ ወደ አገራቸው በተመለሱ ነበር። የስደት ችግር ድንበሮቻችንን በመዝጋት፣ ፍርሃትን በማሳደግ እና ለተቸገሩት እርዳታን በመንፈግ የሚቃለል አይደለም።

ክቡር ንጉሥነትዎ፣ የተከበራችሁ ባለስልጣናት፣ ክቡራን እና ክቡራት ወዳጆቼ! በሞሮኮ የሚገኝ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ከሞሮኮ ሕዝብ ለተደረገለት መስተንግዶ እና እንክብካቤ አድናቆት በመስጠት ምስጋና ያቀርባል። ወንድማማችነትን ለማሳደግ እና በአገሪቱ ውስጥ እድገትንም ለማምጣት የበኩሉን አስተዋጽዖን ለማድረግ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ይገልጻል። ይህን በተመለከተ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በማበርከት ላይ ያለችውን ማህበራዊ አገልግሎት፣ በተለይም በትምህርት ዘርፍ የምትሰጠው ከፍተኛ አገልግሎት የሚጠቀስ ነው። እስካሁን ለተደረጉት ሥራዎች በሙሉ እግዚአብሔርን እያመሰገንኩ ካቶሊካዊ  ምዕመናን እና መላው የክርስቲያን ወገን በጋራ ሆነው ሰብዓዊ ወንድማማችነት በሞሮኮ ሕዝብ መካከል እንዲያሳድጉ ብራታትን እመኝላችኋለሁ።

ክቡር ንጉሥነትዎ፣ የተከበራችሁ ባለስልጣናት፣ ክቡራን እና ክቡራት እና የሞሮኮ ሕዝብ በሙሉ፣ ላደረጋችሁልኝ ደማቅ አቀባበል አሁንም በድጋሚ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር በጸጋው እና በምሕረቱ እናንተን እና የሞሮኮን ሕዝብ ይጠብቅ፤ አመሰግናለሁ”። 

30 March 2019, 17:39