ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢጣሊያ ውስጥ ወደ ሎሬቶ ከተማ ሄደው ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢጣሊያ ውስጥ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በመቀጠል ወደ ሎረቶ ከተማ መሄዳቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ዛሬ ጠዋት ወደ ቦታው ሲደርሱ በርካታ ምዕመናን ደማቅ አቀባበልን አድርገውላቸዋል። የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ዋና ዓላማ በላቲን የሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን ያበሰራት በሚታወስበት እለት በሎሬቶ በሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ተገኝተው መስዋዕተ ቅዳሴን ለማሳረግ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወጣቶችን አስመልክቶ በመስከረም ወር 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ከተማ ካደረገው 15ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ያወጣውን የድህረ ጉባኤ መልዕክት በፊርማቸው ሊያጸድቁት ወደ ሎሬቶ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የንግደት ስፍራ ከመጡት ሕሙማን እና ምዕመናን ጋር ለመገናኘት እንዲሁም የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አብሮአቸው ለመድገም መሆኑን የሐዋርያዊ ጉዞአቸው መርሃ ግብር ይገልጻል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሎረቶን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያቸው መሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በሎሬቶ ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ የወጣቶች ማዕከል የደረሱት ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ገደማ መሆኑ ታውቋል። ከዚያ በኋላ በተዘጋጀላቸው መጓጓዣ ተሳፍረው ወደ ሎሬቶ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ሲደርሱ የሎሬቶ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ዳል ቺን፣ የማርኬ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ቼሪሾሊ፣ የሎሬቶ ከተማ ከንቲቫ ክቡር አቶ ኒኮለቲ፣ የአንኮና ከተማ አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ዳ አኩንቶ በሕብረት ሆነው  አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው ከወጣቶች እና ከሕሙማን ጋር ይገናኛሉ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ. ም. ከኢጣሊያ ክፍላተ ሀገራት ከመጡ ወደ 800 ከሚጠጉ ወጣቶች ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። ወጣቶቹ በየዓመቱ ወደ ሎሬቶ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የሚደረገውን መንፈሳዊ ጉዞን የተካፈሉ መሆናቸው ታውቋል።      

ቅዱስነታቸው ለወጣቶች ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ በሥፍራው የተገኙትን ሕሙማን ጎብኝተው ሰላምታን ተለዋውጠዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዘንድሮ በቫቲካን ከተማ ወጣቶችን አስመልክቶ ካደረገው 15ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ያወጡትን የድህረ ስብሰባ መልዕክትን በፊርማቸው ማጽደቃቸው ታውቋል።

ከመስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን ከተማ የተካሄደው 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ለወጣቶች የጻፉትን መልዕክት በፊርማቸው አጽድቀው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን ለዓለም ወጣቶች ይፋ አድርገዋል። የሎሬቶ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፋቢዮ ዳል ቺን ለቅዱስነታቸው ምስጋናቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሥፍራው ከተሰበሰቡት በርካታ ምእመናን ጋር ሆነው የእኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ንግግር አድርገውላቸዋል። 

25 March 2019, 17:33