ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅርብ የሥራ ተባባሪዎቻቸው ጋር ሆነው በዓመታዊ የሱባኤ እና የጸሎት ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅርብ የሥራ ተባባሪዎቻቸው ጋር ሆነው በዓመታዊ የሱባኤ እና የጸሎት ጊዜ 

የእግዚአብሔርን አለኝታነት መገንዘብ እንዲችል ልብን መንከባከብ ያስፈልጋል።

በሕይወት ወጣ ውረዶች ውስጥ የሚገኘውን፣ በሐጢአት ምክንያት የተበላሸውን ማንነታችንን በሞቱ እና በትንሳኤው ሃይል፣ በምሕረት ዓይኖቹ ተመልክቶን ወደ አዲስ ሕይወት የሚያሸጋግረንን ኢየሱስ ክርስቶስን መመልክከት ያስፈልጋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅርብ የሥራ ተባባሪዎቻቸው ከሆኑት ብጹዓን ጳጳሳት እና ቄሳውስት ጋር ሆነው ዓመታዊ የሱባኤ እና የጸሎት ጊዜን መጀመራቸው ታውቋል። ከ65 የቅርብ የሥራ ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን ካለፈው እሑድ ምሽት ጀምሮ ከሮም ወጣ ብሎ በሚገኝ አሪቻ በተባለ ከተማ ውስጥ ሱባኤን እና ጸሎት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። ከእሑድ መጋቢት 1 ቀን  እስከ ዓርብ መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ ሱባኤውን የሚመሩት የቅዱስ በነዲክቶስ ማህበር መነኩሴ የሆኑት ክቡር አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ ማርያ ጃኒ መሆናቸው ታውቋል። አበምኔቱ አስተንትኖአቸውን የጀመሩት ለሱባኤው ከተቀመጡበት ከአሪቻ ከተማ ላይ ሆነው የሚመለከቱትን የፍሎረንስ ከተማ በማሳየት ሲሆን፣ ብጹዕ ጆርጆ ላ ፒራ የተባሉት ሰው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከንቲባ ሆኖ በሠራበት ጊዜ የፍሎረንስ ከተማን “የጸጋ መልክዓ ምድር” ብሎ መናገሩ ይታወሳል። አበምኔቱ አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ ማርያ ጃኒ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ሌሎች የሱባኤው ተካፋዮች የፍሎረንስ ከተማን እንዲመለከቱ ጋብዘዋቸዋል።

ከከፍታ ስፍራ ሆኖ መመልከት፣

አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ ከከፍታ ስፍራ ሆኖ መመልከት ለምን እንዳስፈለገ ሲያስረዱ በዚህ ዓለም ሃብት በመታለል፣ የበላይንትንም አግኝተን እንድንቆጣጠረው በማለት ሰይጣን የሚያቀርብልንን ፈተና አጥርተን ተመልክተን በፈትና እንዳንወድቅ በትጋት መጸለይ እንደሚያስፈልግ ለማስረዳት ነው ብለዋል። በሌላ በኩልም፣ አበምኔቱ እንደገለጹት በመንፈስ ቅዱስ እና በእግዚአብሔር ቃል በመመራት፣ ምስጋናን ማቅረብ፣ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ በዙሪያችን የሚሆኑትን ነገሮች በጥንቃቄ ተመልክተን ትንቢት መናገር ያስፈልጋል ብለዋል። ይህ ከከፍታ ላይ ሆኖ ወደ ከተማው መመልከቱ ከተሞቻችን ምን ያህል ባዶ መሆናቸውንም በቀላሉ ለመረዳት ያግዛል ብለዋል።

በአረንጓዴ ስፍራ መካከል በረሃን ማግኘት፣

አብምኔት አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮስ ከከፍታ ስፍራ ሆኖ መመልከት ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከቅዱስ ቃሉ የሚገኘውን እውነተኛ ሕይወት በአዲስ መልክ ለመጀመር ያስችላል ብለዋል። ክቡር አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ ለሱባኤው ተካፋዮች በሙሉ ባቀረቡት ማሳሰቢያ ወደ ፍሎረንስ ከተማ የመመልከቱ ምስጢር የሰው ልጆችን እንዲያገለግሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸው የሐዋርያዊ አገልግሎት ጥሪ በአዲስ መልክ ተቀጣጥሎ በሕዝቦች መካከል የሚታየው የበረሃማነት ስሜት፣ ሕይወትን እንዲዘራ የሚያግዝ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

ሰላም፣ ፍትህ እና ወንድማማችነት፣

ፍቅር ባለበት እርስ በእርስ መተያየት አለ የሚለውን የመካከለኛው ዘመን ስኮትላንዳዊው፣ የሪቻርድ ሚስጥራዊ ቃል የጠቀሱት ክቡር አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮስ፣ አሁን በምንኖርበት ዘመን እግዚአብሔር ትቶልን የሚያልፋቸውን ምልክቶች መለየት ያስፈልጋል ብለዋል። ብጹዕ ላ ፒራ የፍሎረንስ ከተማን መመልከት የቻለው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ኢየሩሳሌምን እና በየመንገዱ ያገኛቸውን ሰዎች በሙሉ መመልከት የቻለው በፍቅር በመታገዝ መሆኑን አስረድተዋል። ይህ በፍቅር የታገዘ፣ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፋሲካ በዓል ለመድረስ የምናደርገው ጉዞ የተዳከመውን የወንድማማችነት ስሜት እንድንገነዘብ ያግዘናል ብለዋል። በወንድማማችነት የሚገኝ ጥንካሬ አዲሱ የክርስትና ወሰን ነው ብለዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ዓይን፣

የሰዎች ስብዕና ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚጀምር ያስታወሱት አበምኔት አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ፣ በሕይወት ወጣ ውረዶች ውስጥ የሚገኘውን፣ በሐጢአት ምክንያት የተበላሸውን ማንነታችንን በሞቱ እና በትንሳኤው ሃይል፣ በምሕረት ዓይኖቹ ተመልክቶን ወደ አዲስ ሕይወት የሚያሸጋግረውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲመለከቱ በማለት የሱባኤው ተካፋዮችን ጠይቀዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲጎበኘን እና እንዲመለከተን እድል እንስጠው ብለው ይህን በማድረጋችን፣ ሃብታሙን ወጣት እና ዘኬዎስን እንደተመለከተ ሁሉ እኛም ሌሎችን መመልከት ከእርሱ መማር እንችላለን ብለዋል። አባ ቤርናርዶ በማከልም የኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ዓይን፣ ልባችንን ወደ ቀየረልን ወደ እግዚአብሔር እንዳንመለከት የሚያደርገንን ፍርሃት ያስወግዳል ብለዋል። “ልባችንን በሚገባ ካልተመለከትን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚጎበኘን ማወቅ አንችልም” ያለውን የቅዱስ አጎስጢኖስ ንግግር ያስታወሱት አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ የልብ መለወጥ እንደሚያስፈልግ እና በዚህ በመታገዝ በዘመናችን ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጥበትን አዲስ ተስፋ ማወቅ እንችላለን ብለዋል።

አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮ መላ ሕይወታቸውን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት አሳልፈው የሰጡትን በሙሉ እግዚአብሔር የሚገለጥበት ቀላል እና ትንቢታዊ የሕይወት አካሄድ እንዲኖራቸው አሳስበዋል። የአገልግሎት ሕይወት የቤተክርስቲያን ትንቢታዊነት የሚገለጥበት እንደሆነ ያስረዱት አባ ቤርናርዶ የቤተክርስቲያንን ትንቢታዊነት ብዙዎች ባይረዱትም እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ መሆኑን የምትገልጥበት መንገድ ነው ብለዋል። የቅዱስ በነዲክቶስ ማህበር መነኩሴ የሆኑት አባ ቤርናርዶ ፍራንችስኮስ በመጨረሻም እግዚአብሔር ሕይወት፣ ተስፋ እና መመኪያችን ነው በማለት የዕለቱን አስተንትኖአቸውን አጠቃልለዋል።  

13 March 2019, 14:18