ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የእግዚአብሔርን ምህረት መፈታተን በፍጹም አይገባም” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት ባቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ በሚነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ተመርኩዘው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በትላንትናው እለት ማለትም በመጋቢት 15/2011 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ በተጀመረው ሦስተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት ላይ ከሉቃስ ወንጌል 13፡1-9 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና “ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ላይ መሰረቱን ያደርገ አስተንትኖ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን እኛ በመንፈሳዊ ድክመቶቻችን የተነሳ የእግዚአብሔርን ምሕረት መፈታተን አይኖርብንም ማለታቸውን መለረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በትላንትናው እለት በቫቲካና በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮሰ አደባባይ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ በተጀመረው ሦስተኛው የዐብይ ጾም ሰንበት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 13፡1-19) ስለእግዚኣብሔር ምሕረት እና እኛ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት እንዳለብን ይናገራል። ኢየሱስ ፍሬአላብ ስለሆነ አንድ የበለስ ዛፍ ምሳሌ ይናገራል። አንድ ሰው በየአመቱ በመኸር ወቅት ፍሬ እንደ ሚሰጠው በመተማመን እና ተስፋ በማድረግ በወይኑ አትክልት ስፍራ የበለስ ዛፍ ይተክላል። በተከታታይ ለሦስት አመታት ያህል በተደጋጋሚ ፍሬ ባለመስጠቱ የተነሳ አዝኖና ተስፋ ቆርጦ ዛፉን ለመቁረጥ ይወስናል። ከዚያም በኋላ በወይን እርሻ ውስጥ የሚሰራውን ገበሬ ጠርቶ በዚህ ዛፍ አለምደሰቱን በመግለጽ ይህ ዛፍ መሬቱን ያለአግባብ እየተጠቀመ በመሆኑ እንዲቆርጠው ይጠይቀዋል። ነገር ግን አትክልተኛው ሰው ባለቤቱ ይህንን ዛፍ እንዲታገሠው እና ለአንድ ዓመት ያህል እንዲመለከተው በመጠየቅ ለዚህች የበለስ ዛፍ የበለጠ እንክብካቤ የተሞላበት ጥበቃ እንደ ሚያደርግ እና ይህ ዛፍ ፍሬያማ ይሆን ዘንድ ለየት ያለ ጥንቃቄ እና እንክብካቤ እንደ ሚያደርግለት የገልጽለታል። ይህ ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ነበር። ይህ ምሳሌ ምን ያመለክታል? በዚህ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ማንን ይወክላሉ?

የአትክልቱ ቦታ ባለቤት እግዚኣብሔር ሲሆን አትክልተኛው ደግሞ ኢየሱስ ነው፣ የበለስ ዛፍ ደግሞ  ግድየለሽ እና ደረቅ የሆነው የሰብአዊነታችን መገለጫ ነው። ኢየሱስ በአባቱ ፊት ሰለሰዎች ያማልዳል፣-ሁሌም እንዲህ ያደርጋል- ሰዎች የፍቅርና የፍትህ ፍሬ ያፈሩ ዘንድ ጊዜ እንዲሰጣቸው ያማልዳል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው እና ባለቤቱ ሊቆርጠው ያሰበው የበለስ ዛፍ የሚወክለው ፍሬ አልባ የሆነ ሕይወት ሲሆን ይህም ምርት መስጠት የማይችል መልካም ነገር የማያደርገውን ሕልውና ይወክላል። ለራሱ ብቻ የሚኖር፣ የተሟላ እና የተረጋጋ ሕይወት ያለው፣ በእራሱ ምቾት ብቻ ተዘናግቶ የተቀመጠ፣ በአከባቢው ለሚኖሩ ሰዎች ትኩረት ያልሰጠ፣ በአጠገቡ ለሚኖሩ በችግር፣ በስቃይ እና በድህነት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ግድ የሌለው ሰውን ይወክላል። ይህ የራስ ወዳድነት መንፈስ እና መንፈሳዊ ድርቀት በንጽጽር ስንመለከት አትክልተኛው ሰው ለዚህ የበለስ ዛፍ ያለውን ታላቅ ፍቅር ይመለክታል፣ እርሱ ስራውን በሚገባ እስክያከናውን ድረስ እና ተገቢውን እንክብካቤ እስኪያደርግለት ድረስ ጌታው በትዕግስ እንዲጠባበቅ ይጠይቀዋል። ያ ፍሬያማ ያልሆነ ዛፍ ፍሬያማ ይሆን ዘንድ ልዩ የሆነ እንክብካቤ እንደ ሚያደርግለት ለጌታው ቃል ይገባል።

ይህ የአትክልት ስፍራ ምሳሌ የእግዚያብሔርን ምሕረት ያሳያል፣ ይህም እኛ መንፈሳዊ ለውጥ እስክናመጣ ድረስ ጊዜ የሚሰጠን ነው። ሁላችንም መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት እንደ ሚገባን፣ በእየለቱ በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ በማምጣት ወደ ፊት መጓዝ እንደ ሚገባን፣ በዚህም የጉዞ ሂደት ውስጥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት እና ምህረት አብሮን እንደ ሚጓዝ ያሳያል። ምንም እንኳን በሕይወታችን ውስጥ አንዳንዴ ፍሬያማ ባንሆንም እንኳን እግዚአብሔር ይታገሰናል፣ ወደ መልካም ጎዳና እንድንመለስ እና በመንፈሳዊ ሕይወታችን እድገት ማምጣት እንችል ዘንድ እድል ይሰጠናል። አትክልተኛው ሰው ለባለቤቱ፣ “ጌታ ሆይ ለአንድ ዓመት ያህል ተወው” በማለት እንደ ተናገረው ቅዱስ ወንጌል ይተርካል። መንፈሳዊ ለውጥ የማምጣት ሂደት ገደብ የለውም፣ ስለዚህም በተቻለ መጠን በቶሎ መንፈሳዊ ልወጥ ማምጣት ይኖርብናል፣ ያለበለዚያ ግን ያ እድል መቼም ቢሆን ተመልሶ ሊመጣ አይችልም። በዚህ አሁን በያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት በይበልጥ ወደ ጌታ ለመቀረብ ምን ማደርግ አለብኝ፣ መንፈሳዊ ለውጥ ለማምጣት ምን ማድረግ ይኖርብኛል፣ በሕይወታችን ውስጥ ፍሬያማ እንዳንሆን የሚያደርጉንን ነገሮች እንዴት ቆርጠን መጣል እንችላለን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። “አይ እኔ የሚቀጥለውን የዐብይ ጾም ወቅት እጠብቃለሁ!” ማለት አይኖርብንም። በሚቀጥለው አመት የዐብይ ጾም ወቅት በሕይወት እኖራለሁ ብላችሁ ታስባላችሁ ወይ? ሁላችንም ብንሆን ዛሬን ብቻ ነው ማሰብ የሚገባን፣ በዚህ በትዕግስት በተሞላው የእግዚኣብሔር ምሕረት ፊት ሆኜ ምን ማድረግ ይኖርብኛል? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። በእግዚአብሔር የምሕረት ጸጋ ላይ በእጅጉ ልንታመን እንችላለን፣ ነገር ግን ይህንን የምሕረት ጸጋ አላግባብ መጠቀም አይኖርብንም። በእግዚኣብሔር ምሕረት ተማምነን መንፈሳዊ ድክመቶቻችንን ጤናማ አድርገን በመቁጠር መኖር አይኖርብንም፣ ነገር ግን በልበ ቅንነት ለዚህ የእግዚኣብሔር ምህረት ፈጣን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል።

 

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እና ምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ
24 March 2019, 11:14