ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ሰይጣንን የምናሸንፈው በክርክር ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው”።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሠረት ትናንት እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ. ም. ባደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ከሰይጣን ጋር ምንም ሳይከራከሩ በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ማሸነፍ እንደሚቻል አስተማሩ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ. ም. ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አቅርበናል።

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የጾም ጊዜ በገባ የመጀመሪያ እሑድ በሆነው በዛሬው ዕለት የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ከሉቃስ ውንጌል ምዕ. 4 ከቁጥር 1-13 የተወሰደ ነው። ይህ የወንጌል ክፍል የሚነግረን ኢየሱስ ክርስቶስን ስላጋጠሙት የበረሃ ላይ ፈተናዎች ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀናትን ከጾመ በኋላ በሰይጣን ለሦስት ጊዜ ያህል ተፈትኗል። የመጀመሪያው ፈተና፣ በሉቃስ ወንጌል በምዕ. 4 ቁጥር 3 ላይ እንደተገለጸው የእግዚ አብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ይህን ድንጋይን እንጀራ እንዲሆን እዘዘው የሚል ነበር። ቀጥሎም በቁጥር 5 እና 6 ላይ እንደተገለጸው፣ አንተ ለእኔ ብትሰግድልኛ ይህን ሁሉ ሥልጣን እና ክብር ላንተ እሰጥሃለሁ የሚል ነበር። የመጨረሻው ፈተናም፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ከዚህ ወደ ታች ዘልለህ ውረድ የሚል ነበር። እነዚህ ሦስቱ ፈተኛዎች ዓለም የሰውን ልጆች በሙሉ ውጤታማ ለማድረግ ቃል የሚገባላቸው አሳሳች እና አታላይ መንገዶችን የሚያመለክቱ ናቸው። እነዚህ ሦስቱ አታላይ የፈተና መንገዶች የሰው ልጅ ከሚጠቅመው ነገር ይልቅ የማይጠቅመውን ነገር እንዲጓጓ እና እንዲሰበስብ የሚያደርጉ ናቸው።

የመጀመሪያው የስግብግብነት ባህርይ የተገለጸበት ነው። የስግብግብነት ባህርይ ሁል ጊዜ ከሰይጣን ዘንድ የሚቀርብ የፈተና መንገድ ነው። ሰይጣን የስግብግብነትን የፈተና መንገድ የሚመርጠው የሰውን ልጅ ፍላጎት እና ምኞት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ፣ የሰው ልጅ ልቡን ለዕለታዊ ኑሮ በሚያስፈልጉ ፍጆታዎች ላይ እንዲያደርግ፣ ጊዜያዊ ደስታን በሚሰጡ ነገሮች ላይ ብቻ እንዲያደርግ፣ ነገር ግን ፈጣሪውን፣ እግዚአብሔርን እንዲረሳው ስለሚያደርግ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰይጣንን ተንኮል በመገንዘብ፣ በሉቃስ ወንጌል በምዕ. 4 ቁጥር 4 ላይ እንደተገለጸው “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፏል” በማለት መልሶለታል። ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በበረሃ ውስጥ ይጓዝ ለነበረ ሕዝቡ ወይም ልጆቹ ያደረገውን እርዳታ በማስታወስ በእግዚአብሔር እርዳታ ሙሉ እምነቱን አድርጓል።

ኢየሱስ ክርስቶስን ያጋጠመው ሁለተኛው ፈተና፣ በሉቃስ ወንጌል በምዕ. 4 ቅይር 7 ላይ እንደተጻፈው፣ “አንተ ለእኔ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ ሥልጣን እና ክብር ላንተ እሰጥሃለሁ” የሚል ነበር። ምድራዊ ሃብትን እና ምድራዊ እውቅናን ለማግኘት፣ ወደ ምንፈልገው እና ወድ ምንመኘው የኑሮ ደረጃ ላይ ለመድረስ ሲባል ሰብዓዊ ክብራችንን ማጣት ይቻላል። ነገር ግን በኋላ ላይ የምናገኘው ደስታ ሁሉ ባዶ እና ከንቱ ይሆናል። ስለዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ብቻ ስገድ፣ እርሱንም ብቻ አገልግል ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰለት።

ኢየሱስ ክርስቶስን ያጋጠመው ሦስተኛው ፈተና፣ ለግል ምቾት ሲል እግዚአብሔርን በዓለማዊ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲለውጥ የሚጋብዝ ነበር። ሰይጣን ይህን ፈተና ለኢየሱስ ክርስቶስ ሲያቀርብለት “አንተን እንዲጠብቁህ እግዚአብሔር መላዕክቱን ያዝዛል፣ እግርህም በድንጋይ እንዳይሰናከል በእጃቸው ደግፈውህ ይይዙሃል” ተብሎ የተጻፈውን የቅዱሳት መጽሐፍ ጥቅስ በማቅረብ ነበር። አሁንም ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ ላይ ያለውን ሙሉ እና የማይናወጥ እምነቱን በመግልጽ የሰይጣታንን የፈተና ተንኮል፣ በሉቃስ ወንጌል በምዕ. 4 ቁጥር 12 ላይ እንደተገለጸው “እግዚአብሔር አምላክህን አትፈታትነው” በማለት ተቃውሞታል። እነዚህን የመሳሰሉ እንቅፋቶች፣ ዕለታው የሕይወታችን አሳሳች ምኞቶች  ከእግዚአብሔር እንድንርቅ የዘውትር ፈተና ሆነው ይቀርባሉ።

በዓለም ላይ እውቅና እና ደስታ የሚገኝባቸው መንገዶች እየመሰሉን በፈተና እንድንወድቅ የሚገፋፉን እነዚህ ናቸው። እውነተኛ ደስታ ከሚገኝበት ከእግዚአብሔር መንገድ ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። ከእግዚአብሔር የሚያርቁን እንጂ ወደ እርሱ እንድንደርስ የሚያግዙን መንገዶች አይደሉም። ምክንያቱ የሰይጣን እቅዶች ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ እቅድ ላይ በመተማመን እነዚህን ፈተኛዎች ሦስት ጊዜ አሸንፎ በማለፍ ድልን ተቀዳጅቶባቸዋል። የሰይጣንን ፈተና የምናሸንፍባቸው መንገዶች ውስጣዊ ሕይወታችንን በማገናዘብ፣ በእግዚአብሔር ላይ ሙሉ እምነትን በማድረግ እና በዘለዓለማዊው ፍቅር በመታመን እርግጠኞች እንድንሆን ያስተምራል። እግዚአብሔር አፍቃሪ አባት እንደሆነ እርግጠኞች መሆን ያስፈልጋል። ይህን እርግጠኝነት ይዘን ማንኛውንም ዓይነት ፈተና ማሸነፍ እንችላለን።

ነገር ግን ማሳሰብ የምፈልገው አንድ አስፈላጊ ጉዳይ አለ። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰይጣን የቀረበትን የፈተና ጥያቄዎች በአግባቡ በመለሰለት ጊዜ ለድርድር ወይም ለውይይት ቦታን አልሰጠም። ነገር ግን የእግዚአብሔርን አብ ቃል ብቻ በመጥቀስ መልስ ይሰጠው ነበር። ይህም ከሰይጣን ጋር ምንም ዓይነት ድርድር ወይም ክርክር እንደማያስፈልግ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል ብቻ በመታገዝ ልናሸንፈው እንደምንችል ያስተምረናል።

ስለዚህ ይህ የጾም ወቅት ራሳችንን ከሐጢአት ለማጽዳት፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር እና የዘወትር አለኝታነትን በሚገባ የምናውቅበት ጊዜ እንዲሆንልን ማድረግ ያስፈልጋል።

ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆነች እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በጉዞአችን እንድታግዘን፣ ክፉ የሆኑ ነገሮችን ከሕይወታችን አስወግደን መልካም የሆነውን እንድንከተል ከልጇ የጸጋ በረከትን ታማልድልን”።                           

11 March 2019, 17:24