ፈልግ

2019.03.25 Visita del Santo Padre a Loreto 2019.03.25 Visita del Santo Padre a Loreto 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሎሬቶ ከተማ ተገኝተው ለምእመናኑ ንግግር አድርገውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ. ም. በኢጣሊያ ወደ ሎሬቶ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ሐዋርያዊ ጉብኝት አድረገዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ስፍራው ሲደርሱ በርካታ ምዕመናን ደማቅ አቀባበልን አድርገውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስፍራው ለተገኙት ምዕመናን ንግግር ማድረጋቸው የታወቀ ሲሆን የንግግራቸው ትርጉም የሚከተለው ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ!

ላደረጋችሁልኝ ደማቅ አቀባበል ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

በሉቃስ ወንጌል በምዕ. 1፤28 ላይ እንደተገለጸው፣ መልአኩ ገብርኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን “አንቺ ጸጋን የተሞላሽ” በማለት ያቀርበው ሰላምታ የእግዚአብሔር ልጅ ስጋን የመልበሱን ምስጢር እንድናሰላስል ይጋብዘናል። በሎሬቶ የሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተመቅደስ፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያሰማውን ንግግር በተደጋጋሚ የምናስተውልበት መንፈሳዊ ስፍራ ነው። ይህ በሎሬቶ የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ፣ በአፈ ታሪክ እንደሚነገርለት፣ ቅድስት ድንግል ማርያም ለእግዚአብሔር ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በሰጠችው ጊዜ የኖረችበት የናዝሬት ከተማ መኖሪያ ቤታቸው በአካል ተዛውሮ መጥቶ የተቀመጠበት ሥፍራ ነው። በመሆኑም ይህ “የማርያም ቤት” በመባል የሚታወቀው የሎሬቶ ቤተመቅደስ የተቀደሰ የጸሎት ስፍራ፣ ጸሎታቸውን በእምነት ወደ እርሷ ዘንድ የሚያቀርቡት በሙሉ መንፈሳዊ በረከትን የሚቀበሉበት ሥፍራም በመሆኑ በርካታ ምእመናን ወደዚህ ሥፍራ መንፈሳዊ ጉዞን ያደርጋሉ። እኔም መልአኩ ገብርኤል ለቅድስት ድንግል ማርያም ያቀረበላት ብስራት በሚታወስበት በዛሬው ዕለት ወደዚህ ስፍራ ለመምጣት በመቻሌ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ።

ከአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከአካባቢው ሕዝብ በኩል ለተደረገልኝ ደማቅ አቀባበል ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እንደዚሁም የምእመናንን ሃሳብ እና ምኞት በመግለጽ ልባዊ ሰላምታቸውን ያቀረቡልኝን የሎሬቶ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ፋቢዮ ዳል ቺንን አመሰግናቸዋለሁ። ከእርሳቸው ጋር በመሆን ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙትን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያት እና ገዳማዊያንን፣ በተለይም ይህን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስን ለማስተዳደር ሃላፊነት የተጣለባቸውን የቅዱስ ፍራንችስኮስ ካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ማሕበር አባላትን በሙሉ አመሰግናቸዋልሁ። ለመላው የሎሬቶ ምእመናን እና ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ መንፈሳዊ ንግደት ላደረጋችሁት በሙሉ ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ።

ምዕመናን ብርታትን እና ተስፋን ለማግኘት በማለት የርህራሄ መንፈስ ወደሚገለጥበት ወደዚህ ሥፍራ፣ በተለይም ወጣቶች፣ ወላጆች እና ሕሙማን ከዓለም ዙሪያ እንደሚመጡ አውቃለሁ።

ይህ የሎሬቶ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ቤተመቅደስ የወጣቶች ቤት ነው። ይህን ያልኩበት ምክንያት ጸጋን የተሞላች ቅድስት ድንግል ማርያም በወጣትነት እድሜዋ የኖረችበት ቅዱስ ቤት በመሆኑ ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘመናችን ወጣት ትውልድ ሳታቋርጥ መልዕክት የምታስተላልፍበት፣ የሕይወት ጥሪያቸውን በሚገባ ለማወቅ ብለው በሚያደርጉት ጥረት መካከል ድጋፍ ስለምትሆናቸው ነው። ይህን በማሰብ ዘንድሮ ከመስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን ከተማ የተሰበሰበው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ 15ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ለወጣቶች የጻፉትን መልዕክት በፊርማዬ በማጽደቅ “ሕያው ክርስቶስ” በሚል አርዕስት የሚጠራ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኔን ለዓለም ወጣቶች በሙሉ ይፋ አድርጌአለሁ። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በጉባኤው መጨረሻ ላይ ወጣቶችን የሚመለከቱ ሦስት ርዕሠ ጉዳዮችን ግልጽ አድርገው አስቀምጠዋል። እነዚህም ወጣቶች የእግዚአብሔርን ቃል ማድመጥ እና መገንዘብ፣ በጥበብ እና በማስተዋል የተጠሩበትን የሕይወት መንገድ በትክክል ማወቅ፣ ጥሪያቸውን ከተረዱ በኋላ ቆራጥ ውሳኔን ማድረግ የሚሉት ናቸው።    

የመጀመሪያው እና ወጣቶች የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያዳምጡ እና እንዲገነዘቡ የሚያሳስበው፣ በሉቃ. ምዕ. 1 ቁጥር 30 እና 31 ላይ፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ማርያምን “ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አግኝተሻልና አትፍሪ፣ እነሆ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ” ከሚለው መልዕክት ጋር ስለሚዛመድ ነው። እግዚአብሔር እርሱን መከተል ለሚፈልጉት ጥሪውን ያቀርብላቸዋል። የእምነት እና የማያቋርጥ ክርስቲያናዊ ጉዞን እንዲያደርጉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለወጣቶች የሚቀርብ ጥሪ የፍቅር ጥሪ ነው። ይህ የእግዚአብሔር የፍቅር ጥሪ ድምጽ እንዳያልፋቸው ወጣቶች በንቃት ጠብቀው ማዳመጥ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ለግል እና ለማሕበራዊ ሕይወት እንዲሆን ያዘጋጀልንን ዕቅድ በመንፈሳዊነት እና በመልካም ስነ ምግባር ታግዘን የማንከታተል ከሆነ ልንረዳው አንችልም።  የሕይወታቸውን መንገድ ከእግዚአብሔር ድንቅ ዕቅድ ጋር እንዲያዛምዱት በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም ወጣቶችን ዘወትር ትጠይቃቸዋልች።

ሁለተኛው ወጣቶች የተጠሩበትን የሕይወት መንገድ በጥበብ እና በማስተዋል ማወቅ ያስፈልጋል የሚለው የእግዚአብሔር ጥሪ ትክክለኛ ፍሬ የሚታይበት ነው። በሉቃ. 1፤34 ላይ ማርያም መልአኩን “እኔ ድንግል ነኝ፣ ታዲያ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል”? ይላል። ይህ የማርያም ጥያቄ ጥርጣሬ ያለበት ወይም የእምነት ማነስ የሚታይበት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ጥሪ ለማወቅ ትልቅ ፋላጎት እንዳደረባት የሚገልጽ ነው። በእርሷ ውስጥ እግዚአብሔር ያዘጋጀላትን የሕይወት እቅድ ለማወቅ የሚገፋፋ ሃይል ከመኖሩም በላይ በእግዚአብሔር ዕቅድ ለመሳተፍ እና ከእግዚአብሔርም ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኗን ያሳያል።

በመጨረሻም ወጣቶች ጥሪያቸውን ከተረዱ በኋላ ቆራጥ ውሳኔን ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ሲሆን ይህም የክርስቲያናዊ ጥሪ ዋነኛ ባሕርይ ነው። በሉቃ. 1፤38 ላይ “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ፣ አንተ እንዳልህ ይሁንልኝ” በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም ለእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ የሰጠችህ የአወንታ መልስ ራሷን በሙሉ እምነት ለእግዚአብሔር ማቅረቧን ወይም መስጠቷን ይገልጻል። በመሆኑም ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር የመጣላትን ጥሪ በሙሉ ድፍረት እና እምነት በመቀበሏ ለሐዋርያዊ ጥሪ ምሳሌ ሆናለች። ስለዚህ ትክክለኛ የሕይወት አቅጣጫን በመፈለግ ላይ የሚገኙት ወጣቶች በሙሉ ቅድስት ድንግል ማርያም እንድታግዛቸው በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል . . .”።         

25 March 2019, 18:05