ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከካርዲናሎች ምክር ቤት ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከካርዲናሎች ምክር ቤት ጋር  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባን መጥራታቸው ተገለጸ።

በቅድስት መንበር የካርዲናሎች የመማክርት ጉባኤ ተግባር አዲስ የሚወጡ ሐዋርያዊ ቀኖናዎችን በማጤን ወደ ስምምነት መድረስ ነው

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ የካርዲናሎች መማክርትን በአዲሱ ሐዋርያዊ ቀኖና ላይ ለመወያየት ስብሰባ መጥራታቸው ታውቋል። ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2011 ዓ. ም. የተጀመረው 28ኛ ዙር የካዲናሎች የመማክርት ስብሰባ ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2011 ዓ. ም. የሚጠናቀቅ መሆኑ ታውቋል። የካርዲናሎች መማክርት ጉባኤ ከታሕሳስ 1 እስከ ታሕሳስ 3 ቀን 2011 ዓ. ም. ባካሄደው የመጨረሻ ስብሰባ በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የተወያየ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የቅድስት መንበር የገንዘብ ወጭዎችን የተመለከተ፣ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ የጳጳሳት ጉባኤዎች ሊቀ መናብርት ጋር በሕጻናት ላይ ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች መወያየቱ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ በቫቲካን የመገናኛ ጽሕፈት ቤት መዋቅርን በመመልከት ማጠናከሪያ ማድረጉ ታውቋል። ከታሕሳስ 1 እስከ ታሕሳስ 3 ቀን 2011 ዓ. ም. ከተካሄደው የካርዲኖሎች መማክርት ስብሰባ በኋላ “ወንጌልን አብስሩ” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ አዲስ ሰነድ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀረበ መሆኑ ይታወሳል።

የካርዲናሎች መማክርት ምክር ቤት አወቃቀር፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2006 ዓ.ም. በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የካርዲናሎች መማክርት ጉባኤን መመስረታቸው ይታወሳል። በቅድስት መንበር የካርዲናሎች የመማክርት ጉባኤ ዋና ተግባር አዲሱ የሚወጡ ሐዋርያዊ ቀኖናዎችን በማጤን እና ወደ ስምምነት መድረስ እንደሆነ ታውቋል። ይህን ተግባሩን ለመፈጸም የካርዲናሎች የመማክርት ጉባኤ የመጀመሪያውን ስብሰባ በመስከረም 23 ቀን 2006 ዓ. ም. ማካሄዱ ይታወሳል። ባሁኑ ጊዜ በቅድስት መንበር የካርዲናሎች የመማክርት ጉባኤ ስድስት አባላት ያሉት ሲሆን፣ የጉባኤው ሰብሳቢ እና በሆንዱራስ ተጓሲጋልፓ ሊቀ ጳጳሳት፣ ብጹዕ ካርዲናል ኦስካር አንድሬስ ሮድሪገስ ማራዲያጋ ሲሆኑ፣ የቫቲካን መንግሥት ፕሬዚዳንት ብጹዕ ካርዲናል ጁሴፐ በርቴሎ መሆናቸው ታውቋል። የተቀሩት አራቱ የምክር ቤቱ አባላት ካርዲናል ኦዝቫልድ ግራሲያስ በሕንድ የቦምቤይ ሊቀ ጳጳሳት፣ ብጹዕ ካርዲናል ሬይንሃርድ ማርክስ በጀርመን የሙኒክ እና የፍሪሲንጋ ሊቀ ጳጳሳት፣ ካርዲናል ዣን ፓትሪክ ኦ ማሊ በሰሜን አሜርካ የቦስተን ከተማ ሊቀ ጳጳሳት፣ የቫቲካን መንግሥት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መሆናቸው ታውቋል። በካርዲናሎች የመማክርት ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በኢጣሊያ የአልባኖ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቼሎ ሰመራሮ እንደ ጸሐፊ፣ በኢጣሊያ የክሬዚማ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርኮ መሊኖ ረዳት ጸሐፊ ሆነው በማገልገል ላይ መሆናቸው ታውቋል።                        

በካርዲናሎች የመማክርት ጉባኤ ጥያቄ መሠረት ከጳጉሜ 5 2010 ዓ. ም. እስከ መስከረም 2 ቀን 2011 ዓ. ም. በተካሄደው 26ኛ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ አባላት በተሰጣቸው የአገልግሎት ዘርፍ፣ በቅድስት መንበር የተለያዩ ጽሕፈት ቤቶች አወቃቀር እና በካርዲናሎች ምክር ቤት የአባላትን የዕድሜ ደረጃን የተመለከተ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው የጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የካርዲናሎች መማክርት ጉባኤ በአምስት አመቱ የሥራ ጊዜው ላከናወናቸው ተግባራት ምስጋናቸውን አቅርበው ለምክር ቤቱ አገልግሎት የበኩላቸውን ከፍተኛ እገዛን ያደረጉት ካርዲናል ጆርጅ ፔል፣ ካርዲናል ፍራንችስኮስ ያቬር እና ካርዲናል ሎሬንት ሞንሴንጉዎ ፓሲኒያን አመስግነዋቸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 February 2019, 14:27