ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መንፈሳዊ የሆኑ የስነ-አምልኮ ተግባራት ሰዎችን ወደ እግ/ር ማቅረብ ይኖርባቸዋል

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መንፈሳዊ የአምልኮ ስነ-ስርዓቶች እና የቅዱሳን ምስጢራት ጉባሄ ተሳታፊዎች ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት መንፈሳዊ የስነ-አምልኮ ተግባሮች ሰዎችን ወደ እግዚኣብሔር ሊያቀርቡ በሚችል ሁኔታ መዘጋጀት እንደ ሚኖርባቸው ገለጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉትን ንግግር የጀመሩት “በዚህ ጠቅላላ ጉባሄ ላይ ተገኝቼ እናንተን  በመገናኜቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። የመንፈሳዊ አምልኮ ስነ-ስርዓቶች እና የቅዱሳን ምስጢራት ጉባሄ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ካርዲናል ስላደርጉት ንግግር እና እንዲሁም የዚህ ጽሕፈት ቤት አባላት የሆናችሁ ሁላችሁ ስላቀረባችሁልኝ ሰላምታ ከልብ አመሰግናለሁ” በማለት እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ይህ ጉባሄ እየተደረገ የሚገኘው ወሳኝ በሆነ ጊዜ እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸው እንደ ነበረ ለመረዳት ተችሉዋል።

ይህ መንፈሳዊ የአምልኮ ስነ-ስርዓቶች እና የቅዱሳን ምስጢራት የሚመለከተው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የዛሬ 50 ዓመት ገደማ በወቅቱ እ.አ.አ በግንቦት 18/1968 ዓ.ም በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የተመሰረተ ጽሕፈት ቤት እንደ ነበረ የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የተቋቋመው በሁለተኛ የቫቲካን ጉባሄ ላይ መንፈሳዊ የሆኑ የአምልኮ ስነ-ስርዓቶች እና የቅዱሳን ምስጢራትን በሚመለከት የተወሰኑ ውሳኔዎችን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዶ የተመሰረተ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ይህ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በወቅቱ ከተሰጡት ተልዕኮዎች ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሰው በሁለተኛ የቫቲካን ጉባሄ ተሳታፊ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ባስተላለፉዋቸው ውሳኔዎች ላይ ተመርኩዞ በተለይም ደግሞ ለመንፈሳዊ ስርዓተ አምልኮ አገልግሎት የሚውሉ ቅዱሳን መጽሐፍትን  በአግባቡ ለሕትመት በማብቃት ምዕመናን የስርዓተ አምልኮ ስነ-ስረዓቶችን “በንቃት፣ በአስተዋይነት፣ እና በታማኝነት" መንፈስ እንዲሳተፉ ለማስቻል ታቅዶ የተመሰረተ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መሆኑን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።

ይህም የሚከናወነው የቤተክርስቲያኗን ጥንታዊ ቱባ የሆነ የጸሎት ባህሎችን እና እሴቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ከግምት ባስገባ መልኩ፣ በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያኗ የታሪክ ሂደት ውስጥ አዲስ የተገኙ አስተምህሮዎችን እና መንፈሳዊ ጸጋዎችን ከግምት ባስገባ መልኩ በአዲስ መልክ ክለሳ ተደርጎባቸው ለአገልግሎት የሚውሉ መንፈሳዊ ስርዓተ አምልኮ የሚከናወንባቸው ቅዱሳን መጽሐፍትን ለተጠቃሚው የማቅረብ ተልዕኮ የተሰጠው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

መንፈሳዊ “የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶችን ጥራት ከፍ ለማድረግ የአምልኮ ስነ-ስርዓቶች የሚከናወኑባቸውን መጽሐፍትን ማሻሻል እና መለወጥ በራሱ በቂ እንዳልሆነ” በንግግራቸው ወቅት የገለጹት ቅዱስነታቸው ሕይወታችን ለእግዚኣብሔር የተገባ ይሆን ዘንድ ለማስቻል በቅድሚያ ልብን መቀየር በሚችል መልኩ መታየት ይኖርባቸዋል ብለው የዚህ ዓይነት መነፈሳዊ ለውጥ ደግሞ ክርስትያናዊ ወደ ሆነ አድማስ ምዕመኑን በመምራት ሕያው የሆነውን አምላክ እንዲገናኙ ማስቻል ይኖርበታል ብለዋል።

ማነኛውም መንፈሳዊ የስርዓተ አምልኮ ስነ-ስረዓቶች ምናባዊ ሳይሆን ተጨባጭ እውነታን የዳሰሱ ሊሆኑ እንደ ሚገባ የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህ ረገድ ጥራዝ ነጠቅ የሆኑ ምናባዊ አስተሳሰቦች እንዳይካተቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደ ሚገባ ገልጸው አሁን ያለንበት ዓለም ተጨባጭ ሁኔታን ከግምት ባስገባ መልኩ መቀረጽ እንደ ሚገባቸው ገልጸው ያለፈው ጊዜ ምንም አይጠቅምም ብሎ ሙሉ በሙሉ መተው ወይም ደግሞ የመጪው ጊዜ ምንም አያስፈልግም ብሎ እርሱንም ሙሉ በሙሉ መተው እንደ ማያስፈልግ ገልጸው ያለፈውን ጊዜ ከፍተኛ በሆነ መልኩ ከግምት ባስገባ መልኩ የአሁኑን እና የመጪውን ጊዜ ከግምት ባስገባ መልኩ በአጠቃላይ ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ መከናወን ይገባዋል ብለዋል።

የሥራችሁ ሁሉ ዋነኛው የመነሻ ነጥብ ሊሆን የሚገባው መንፈሳዊ የሆነው ስርዓተ አምልኮ እውነታ ምን እንደ ሆነ በቅድሚያ ለይቶ ማወቅ እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው በስርዓተ አምልኮ ስነ-ስርዓቶች ውስጥ በፍጹም ሊቅየሩ የማይገባቸው ቅዱስ የሆኑ እሴቶች በከፍተኛ ደረጃ እንደ ሚገኙ የገለጹት ቅዱስነታቸው ነገር ግን እነዚህን ድንቅ የሆኑ በዘመን መሻገር ምክንያት ሊለወጡ የማይገባቸውን መንፈሳዊ እሴቶች አሁን ያለው ምዕመን ሊረዳቸው በሚችል መልኩ እና ቅዱሱን የእግዚኣብሔር ሕዝብ ልብ በመቀየር ወደ እግዚኣብሔር ሕዝቡን ማቅረብ በሚችል መልኩ መሰናዳት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

16 February 2019, 10:03