ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በእግዚ/ር መሐሪ ነው፣ በዚህ ተማምነን ኃጢያት መስራታችንን መቀጠል አይገባም”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 21/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ቀሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ክርስቲያኖች መቼና እንዴት ሕይወታቸው እንደ ሚጠናቀቅ ስለማያውቁ የሚፈጽሙዋቸውን ማነኛቸውም ዓይነት ድርጊቶችን በተመለከተ በዕየለቱ የሕሊና ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን መፈተሽ እንደ ሚገባቸው” ጠቅሰው “እግዚኣብሔር መሐሪ እንደ ሆነ ሁሉ ክፉ ነገሮችን አከናውነን የማንጸጸት ከሆንን ግን ቁጣውን በእኛ ላይ እንደ ሚያወርድ” ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት “የእግዚአብሔር ርኅራኄ ገደብ የለሽ ነው በሚለው ስሜት ውስጥ ገብተን ሁል ጊዜ መኖር እንደ ሌለብን” በማሳሰብ የሕይወታችን ፍጻሜ መቼ እንደ ሚሆን ስለማይታወቅ አንድ ጊዜ ቆም ብለን ውድቀቶቻችንን በማሰብ ስህተቶቻችንን መገንዘብ ይኖርብናል” ብለዋል።

በእለቱ ከመጽሐፈ መክብብ (5፡1-10) ላይ ተወስዶ በቀዳሚነት በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ባደርገው ስብከት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት መንፈሳዊ ለውጥ በማምጣት ልባችንን በመቀየር ወደ ጌታ መቅረብ ኣንደ ሚገባን ጨምረው ገልጸዋል።

ስሜቶቻችንን መቆጣጠር

“ጥበብ በሕይወት ላይ በማሰላሰል እና ዕለታዊ ኑሮዋችንን እንዴት መኖር እንዳለብን ከማሰብ የሚነጭ” እንደ ሆነ በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ስሜቶቻችሁን፣ ፍላጎቶቻችሁን እና ይልብ መሻታችሁን አትከተሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው እያንዳንዳችን የተለያየ ዓይነት ስሜት ቢኖረንም በጥንቃቄ ስሜቶቻችንን በሙሉ መቆጣጠር ግን ይኖርብናል ብለዋል።

“ስሜት መጥፎ የሆነ ነገር አይደለም፣ ነገር ግን ስሜቶቻችንን በሚገባ መቆጣጠር ግን ይኖርብናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ስሜቶቻችን ልክ በውስጣችን እንደ ሚገኝ ደም ብዙ ነገሮችን እንድናከናውን እንደ ሚረዱን የገለጹት ቅዱስነታቸው ነገር ግን ስሜቶቻችንን በሚገባ መቆጣጠር ካልቻልን ግን በተቃራኒው ስሜቶቻችንን እኛን ይቆጣጠሩናል ብለዋል።

ሳንዘገይ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል

ሕይወትን በንጽጽር ማየት እንደ ሚገባ በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እኛ ዘላለማዊ የሆንን ፍጡራን አይደለንም፣ የእግዚኣብሔር ዘላለማዊ ምሕረት አለ ብለን በማሰብ የፈልግነውን ማነኛውንም ነገር ማከናወን እንችላለን ብለን ማሰብ እንደ ማይገባ የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህ ሐሳብ ተሞልተን እግዚኣብሔርን ዘላለማዊ በሆነ መልኩ መሐሪ ነው ብለን ብቻ በማሰብ በያዝነው የጥፋት ጎዳና ላይ መረማመዳችንን ከቀጠልን ግን አንድ ቀን የሚደርስብንን ነገር አናውቅም ብለዋል።

"የእግዚአብሔር ርኅራኄ ታላቅ ነው፣ ብዙ ኃጢአቶቼንም ይቅር ይልልኛል በማለት በዚህም ምክንያት እኔ የፈለኩትን ነገር ሁሉ ማድረጌን እቀጥላለሁ” ማለት እንደ ማይገባ የገለጹት ቅዱስነታቸው “አንድ ቀን መንፈሳዊ ለውጥ አመጣለሁ እያልን ቀናትን ማራዘም አይገባም፣ መንፈሳዊ ለውጥ የማምጫ ቀናችንን ቀን በቀን እያራዘምን መሄድ አይገባንም፣ ምክንያቱም አንድ ቀን የጌታ ቁጣ ገንፍሎ ሊመጣብን ይችላልና” በማለት የመንፈሳው ለውጥ ማምጫ ቀናችንን እለት በእለት ማራዘም አይገባንም ብለዋል።

በእየቀኑ የ5 ደቂቃ አስተንትኖ ማድረግ

በእየለቱ የአምስት ደቂቃ የሕሊና ምርመራ በማድረግ መንፈሳዊ ለውጥ በማምጣት ወደ ጌታ መቅረብ ይኖርብናል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ስሜቶቻችን እኛን ሳይቆጣጠሩ በፊት እኛ ስሜቶቻችንን ተቆጣጥረን መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል ብለው ማነኛችንም ብንሆን መቼ እና እንዴት ሕይወታችን እንደ ሚጠናቀቅ ስለማናውቅ በእየለቱ በቀኑ ማብቆያ ላይ ለአምስት ደቂቃ ይህል የሕሊና ምርመራ በማድረግ መንፈሳዊ ለውጥ ለማምጣት በመጣር ልባችን ወደ ጌታ እንዲጠጋጋ በማድረግ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል ብለዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት
28 February 2019, 15:08