ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እውነተኛ ጸሎት ተጨባጭ የሆነና በርኅራኄ መንፈስ የተሞላ ጸሎት ነው!”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት በኅዳር 26/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደርጉት የጠቅላላ የተምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ መሰረቱን ያደርገ የክፍል አንድ አስተምህሮ እንደ ነበረ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን “ኢየሱስ ጸሎት መጸለይ እንዲይስተምረን ልንጠይቀው ይገባል” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በታኅሳስ 03/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ ባደርጉት የክፍል ሁለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት “በእግዚኣብሔር በመተማመን ልንጸልየው የሚገባን ጸሎት ነው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን በታኅሳስ 24/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ ባደርጉት የክፍል ሦስት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ሳትለምነው  በፊት ምን እንደ ሚያስፈልግህ  በሚያውቀው አባትህ ፊት ሆነህ ጸልይ” (ማቴ. 6፡6) የእኛ አምላክ የሆነው እግዚኣብሔር እርሱ ከእኛ ምንም ነገር አይፈልግም፣ ነገር ግን እርሱ ከእኛ የሚፈልገው አንድ ነገር ቢኖር የእርሱ በጣም ተወዳጅ ልጆቹ የሆንን እኛ፣ በጸሎት ሁልጊዜ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት የሚያስችለንን የመገናኛ መስመር ሁልጊዜ ክፍት እንድናደርግ ብቻ ነው የሚጠይቀን” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በጥር 1/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ባደርጉት የክፍል አራት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “ማነኛውም ዓይነት ጸሎት ወደ እግዚ/ር ዘንድ ሳይደርስ እንዲሁ በከንቱ አይቀርም!  እርሱ እግዚኣብሔር አባት በመሆኑ የተነሳ በመከራ ውስጥ ሆነው እርሱን የሚለምኑትን ልጆቹን በፍጹም አይረሳም” ማለታቸውን የሚታወስ ሲሆን በጥር 08/2011 ዓ.ም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ባደረጉት የክፍል አምስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ደግሞ አባ" ማለት እግዚአብሔርን "አባት" ብሎ ከመጥራት የበለጠ ልብ የሚነካ ስሜት እንደ ሌለ ያሳየናል”  ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ በተከታታይ ሲያደርጉት የነበረውን የጠቅላላ አስተምህሮ ይህንን ያህል ካስታወስናችሁ ቅዱስነታቸው በዚህ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ በተከታታይ ስያደርጉት የነበረውን የጠቅላላ አስተምህሮ በቅርቡ በፓናማ፣ ቀጥሎም የተባበሩት የአረብ ኤምሬትስ ዋና ከተማ በሆነችው በአቡዳቢ አድርገውት በነበረው ሐዋርያዊ ጉብኝት ምክንያት ይህንን አስተምህሮ ለሦስት ሳምንታት ያህል አቋርጠው የነበረ ሲሆን በዛሬው እለት ማለትም በየካቲት 06/2011 ዓ.ም አሁንም በዚሁ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ ባደርጉት የክፍል ስድስት የጠቅላላ አስተምህሮ እንደ ግለጹት “እውነተኛ ጸሎት ተጨባጭ የሆነና በርኅራኄ መንፈስ የተሞላ ጸሎት ነው!” ማለታቸውን ከደረሰን መረጃ ለመረዳት ተችሉዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 06/2011 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ!

ኢየሱስ እንዳስተማረን እንዴት መጸለይ እንደሚቻል የበለጠ ለመማር እንችል ዘንድ አስተምህሮዋችንን እንቀጥላለን። ኢየሱስ “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ በርህንም ዝጋ ከዓለም ራቅ ጸሎትህንም ወደ እግዚኣብሔር “አባት ሆይ” በማለት አቅርብ ይለናል። ኢየሱስ የእርሱ የሆኑ ደቀ-መዛሙርት ሲጸልዩ እንደ ግብዝ ሰው ለታይታ በመንገድ ማዕዘን ላይ ቆመው እንዲጸልዩ አይፈልግም (ማቴ 6:5)። እውነተኛ ጸሎት በሕሊና እና በልብ ውስጥ በምስጢር የሚከናወን ነገር ነው፣ ይህም ለሰው ፈጽሞ የማይታወቅ፣ ነገር ግን  ለእግዚአብሔር ብቻ የሚታይ ጸሎት ነው። ከእግዚአብሔር ለመሸሽ መሞከር ስለማይቻል በዚህም ምክንያት የተነሳ ከእውሸት ያመልጣል። በዚህም መልኩ በዝምታ የሚደረግ ውይይት ስር መሰረቱን ይጥላል፣ ልክ ሁለት የሚዋደዱ ሰዎች ያለማቋረጥ እየተያዩ እንደ ሚነጋገሩ ሁሉ እንዲሁም በእግዚኣብሔር እና በሰው መካከል በጸጥታ የሚደርግ ጸሎት ይሆናል።

ምንም እንኳን አንድ ደቀ መዝሙር ጸሎቱ ሁሌም ምስጢራዊ የሆነ ጸሎት ቢሆንም፣ ነገር ግን ምንም ጊዜ ቢሆን ሳይሳካ አይቀርም። በህሊና ምስጢራዊነት የተነሳ ክርስቲያን ቤቱን ዘግቶ በሚጸልይበት ወቅት ዓለምን ከበሩ ውጭ አድርጎ ብቻውን ይጸልያል ማለት ሳይሆን፣ ነገር ግን በልቡ ውስጥ ሰዎችን እና የዓለምን ሁኔታ ይዞ ይጸልያል ማለት ነው።

“አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ውስጥ አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ፣ ነገር ግን የቀረ ነገር አለ። በተለይም ደግሞ በዘመናችን ውስጥ- ምንአልባትም ሁልጊዜ- በስፋት የሚንጸባረቅ አንድ ቃል ይጎለዋል ይህም ቃል “እኔ” የሚለው ቃል ነው። በምንጸልይበት ወቅት በከንፈራችን ላይ እንዲሆን ኢየሱስ ያስተማረን ቃል “የአንተ” የሚለው ቃል ሲሆን ይህንንም ያደርገበት ምክንያት የአንድ ክርስቲያን ጸሎት የውይይት መንፈስ እንዲኖረው ስለፈለገ ነው፡ ለዚህም ነው እንግዲህ “ስምህ ይቀደስ፣ ምንግሥትህ ትምጣ፣ ፈቃድህ . . . ይሁን” የሚሉትን ቃላት በመጠቀም ይህንን ጸሎት ያስተማረን በዚሁ ምክንያት ነው። ከዚያም በመቀጠል “እኛ” ወደ ሚለው ቃል ይሻገራል። “አባታችን ሆይ” የሚለው ጸሎት ሁለተኛ ክፍል ላይ “እኛ” ወደ ሚለው ብዝዐነትን ወደ ሚያመለክተው ግስ የሚያዘነብል ሲሆን “የእለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፣ በደላችንን ይቅር በልልን፣ ወደ ፈተና አታግባን፣ ከክፉ ሁሉ አድነን” የሚሉትን ብዝዐነትን የሚገልጹ ቃላትን ይጠቀማል። ከዚያም በጣም መሰረታዊ የሆኑ የሰዎች ጥያቄ ይነሳል- ለምሳሌም እንደ ረሃብን ማስታገስ የሚያስችል ምግብን ስለመጠየቅ የሚመለከቱ ጉዳዮች የመሳሰሉ ሐሳቦች ሁሉም ብዝዐነትን ያማከሉ የጸሎቱ ክፍል ናቸው። በአንድ ክርስቲያን ጸሎት ውስጥ ማንም ሰው ምግብ ለራሱ ብቻ አይጠይቅም፣ ነገር ግን ለሁሉም በዓለም ውስጥ ለሚገኙ ድሆች ምግብ ያገኙ ዘንድ ይጸልያል።

ከእግዚአብሔር ጋር በሚደርጉ ውይይቶች ውስጥ ግለሰባዊነት ምንም ቦታ የለውም። በዓለም ውስጥ ብቻውን  በመከራ የሚሰቃይ ማንም ሰው የለም። በኅበረት ለወንድሞች እና ለእህቶች ከሚደረገው ጸሎት ውጪ ወደ እግዚኣብሔር ሊደርስ የሚችል ጸሎት የለም።

በጸሎቱ ውስጥ አንድ ክርስቲያን በእርሱ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ችግሮቻቸውን ሁሉ ወደ እግዚኣብሔር ያቀርባል፡ ሲመሽ በዚያ ቀን ውስጥ ያጋጠሙትን መከራዎች ሁሉ ወደ እግዚኣብሔር ያቀርባል፣ እርሱ የብዙ ወዳጆቹን እና እንዲሁም የጠላቶቹን ሁኔታ ወደ እግዚኣብሔር ያቀርባል፣ እነርሱን ያጋጠማቸውን አደገኛ ሁኔታ ወደ እግዚኣብሔር ያቀርባል። አንድ ሰው በአከባቢው የሚኖሩ ብዙ ሰዎች መከራ ውስጥ እንደ ሚገኙ  ወይም እንዳሉ ካልተገነዘበ፣ ድሃው ለሚያፈሰው እንባ ርኅራኄ ከሌለው፣ ለምንም ነገር ደንታ ከሌለው፣ ይህ ማለት ደግሞ እርሱ ያለው ልብ ድንጋያማ የሆነ ልብ ነው ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ ሰዎች ከሆንን ደግሞ ጌታ በመንፈሱ ልባችንን እንዲነካ እና ልባችንን እንዲያለሰልስ መጸለይ ይገባል። ክርስቶስ በዓለም ውስጥ የተፈጠሩትን ችግሮች እና መካራዎች እያየ ዝም ብሎ አላልፋቸውም ነበር፣ ብቸኝነት፣ የአካልም ሆነ የመንፈስ ህመም የደረሰባቸውን ሰዎች በሚመለከትበት ወቅት ልክ እንደ አንድ እናት ከፍተኛ የሆነ የርኅራኄ ስሜት ይሰማው ነበር። ይህ “የርኅራኄ ስሜት” ደግሞ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ቁልፍ የሆነ ቃል ነው፡ ይህ ቃል ደጉ ሳምራዊ ተብሎ የሚጠራው ሰው ቆስሎ በመንገድ ላይ ተኝቶ የነበረውን ሰው እንዲቀርበው የገፋፋው ይህ ቃል ሲሆን፣ ሌሎቹ ግን ይህንን ሳያደርጉ መንገዳቸውን እንዲቀጥሉ ያደርጋቸው ደግሞ ድንጋያማ ልብ ስለነበራቸው ነበር።

እኔ በምጸልይበት ወቅት በአከባቢዬ ወይም ደግሞ ከእኔ ርቀው የሚገኙት ሰዎች ጩኸት ከግምት ባስገባ መልኩ ነው ወይ የምጸልየው? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። ወይም ደግሞ ጸሎትን እንደ አንድ የማረጋጊያ ማደንዘዣ መድኃኒት አድርጌ ነው የማስበው? በዚህ ሁኔታ የማስብ ከሆነ በተሳሳተ ችግር ውስጥ ገብቼ እዘፈቃለሁ ማለት ነው። በዚህ ዓይነት መንፈስ የሚጸለይ ጸሎት የአንድ ክርስቲያን ጸሎት ዓይነት ሊሆን በፍጹም አይችልም። ምክንያቱም “እኛ” የሚለውን ቃል ማዕከል ባደርገ መልኩ ጸሎት እንድናደርግ ያስተማረን ኢየሱስ ይህንን ቃል “እኔ” በሚለው ቃል ለውጠን በምንጸልይበት ወቅት፣ ራሳችን ብቻ በሰላም ለመኖር በመፈለግ “እኔ” እያልን የምንጸልየው ጸሎት ተገቢ ባለመሆኑ የተነሳ ኢየሱስ ለወንድሞቼ እና ለእህቶቼ ኃላፊነት ይሰማኝ ዘንድ ያሳስበኛል።

ምንም እንኳን እግዚኣብሔርን የማይፈልጉ ሰዎች ቢኖሩም ቅሉ፣ ነገር ግን ኢየሱስ ለእነዚህ ሰዎች እንድንጸልይ በማድረግ እግዚኣብሔር ከሁሉም በላይ እነዚህን ሰዎች ይፈልግ ዘንድ ለእነርሱ ጸሎት ማድረግ እንደ ሚገባን ያበረታታናል።  ኢየሱስ ወደ እዚህ ምድር የመጣው ለጻድቃን ሳይሆን፣ ነገር ግን ለታመሙት እና ኃጢአተኛ ለሆኑ ሰዎች ነው (ሉቃስ 5፡31) ይህም ማለት ሁላችንንም ለማዳን ነው የመጣው፣ ምክንያቱም ራሱን ቅዱስ አድርጎ የሚቆጥር ሰው ቅዱስ አይደለምና። እኛ ለፍትህ መረጋገጥ የምንሰራ ከሆንን፣ ከሌሎች የተሻልን እንደ ሆንን ሆኖ ሊሰማን በፍጹም አይገባም፣ አባታችን ጸሐዩን በመልካሞች እና በክፉዎች ላይ እኩል በሆነ መልኩ ነው እንዲወጣ የሚያደርገው (ማቴ 5፡45)። ከእኛ ጋር በመልካም ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ መልካም ማድረግ የለመድን እኛ በተቃራኒው ለሁሉም ሰዎች መልካም ከሚያስበው ከእግዚኣብሔር ይህንን መልካም ነገር እንማር።

ቅዱሳን እንሁን ኃጢያን ሁላችንም በአንዱ አባታችን የተወደድን ወንድማማቾች ነን። በሕይወታችን ፍጻሜ ላይ የምንዳኘው በፍቅር ላይ መሰረቱን ባደርገ መልኩ ነው። እንዲያው ዝም ብሎ ስሜታዊ በሆነ ፍቅር ላይ መሰረቱን ያደርገ ፍቅር ሳይሆን በርኅራኄ መንፈስ የተሞላ፣ ተጨባጭ በሆነ መልኩ  “እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ለሚያንሱ ለእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁ ለእኔ እንዳደረጋችሁ ቁጠሩት” (ማቴ 25፡40) በሚለው በቅዱስ ወንጌል ላይ መሰረቱን ባደርገ መልኩ ሊሆን ይገባዋል።

13 February 2019, 14:24