ፈልግ

ቅዱስነታቸው ስብሰባውን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ከፍተዋል ቅዱስነታቸው ስብሰባውን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ከፍተዋል 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ስደተኞችን እና ድሆችን እርዷቸው እንጂ አትፍሯቸው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ዓርብ፣ የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ. ም. በሮም ከተማ አካባቢ፣ ፍራቴርና ዶሙስ ሳክሮፋኖ በተባለ ሥፍራ ተገኝተው፣ የስደተኞችን የኑሮ ሁኔታ በዝርዝር ለመመልከት ታስቦ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ መገኘታቸውን በትናንትናው ዕለት ዝግጅታችን መዘገባችን ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ስብሰባውን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት የከፈቱት ሲሆን፣ በዕለቱ በተነበቡት  የቅዱሳት መጽሕፍት ንባባትን መሠረት በማድረግ አስተንትኖ አድርገዋል። የአስተንትኖአቸውንም ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ የተነበቡትን የቅዱስ መጽሐፍት ንባባት መልዕክት በአጭሩ ፍርሃት አይዛችሁ በማለት ልናጠቃልል እንችላለን። ከመጽሐፈ ዘጸዓት ተወስዶ የተነበበው ምንባብ እስራኤላዊያን ቀይ ባሕርን ሲሻገሩ የፈሪዖን ሠራዊት ጥቃት ለማድረስ በተቃረቡ ጊዜ የተሰማቸውን ፍራሃት እና ድንጋጤን ያስታውሰናል። ከእስራኤላዊያኑ አብዛኛዎቹ ከፍርሃት የተነሳ በባርነት ይኖሩ በነበሩበት በግብጽ መቆየት ይሻለናል ብለው አስበው ነበር። ነገር ግን ሙሴ ለሕዝቡ “አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ።  አይዞአችሁ አትፍሩ” (ዘጸዓት ምዕ. 14.13) በማለት ያበረታታችው ነበር። እስራኤላዊያን ቃል ወደተገባላቸው ምድር ለመድረስ የጀመሩት ጉዞ ይህን በመሰለ ሁኔታ ጀምሮ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ የተጠራው ከጠላቶቻቸው የሚሰነዘረውን ጥቃት እና የሚያድርሱባቸውን መከራ እንዲመለከት ሳይሆን በመካከላቸው የነበረውን ፍርሃት አስወግደው  በእግዚአብሔርን የማዳን ሃይል ሙሉ እምነቱን እንዲያደርግ ነው።

በማቴ. 14. 22-33 ላይ ሐዋርያት ኢየሱስ በውሃ ላይ ሲራመድ ባዩት ጊዜ በፍርሃት ተውጠው ይጮሁ ነበር። የተሳፈሩበትን ጀልባ ሃይለኛ ነፋስ ሲያናውጠው በውሃ ላይ ሲራመድ የተመለከቱት ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን መረዳት አልቻሉም ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፣ “አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው። (ማቴ. 14.27) ጴጥሮስ በጥርጣሬ በመሞላት “ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ አለው”። ኢየሱስም ይጠራዋል። ጴጥሮስም የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ። ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው።

በእነዚህ የቅዱሳት መጽሐፍት ንባባት አማካይነት እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን ይናገረናል። ከያዘን ፍርሃት ሊያላቅቀን እንደሚችል ይነገረናል። ለዚህ ስብሰባ የተመረጠው መሪ ሃሳብም “ፍርሃትን አስወግዱ” የሚል ነው። ፍርሃትን አስወግዱ፣ ፍርሃት የባርነት ምንጭ ነውና። እስራኤላዊያን ከፍርሃታቸው የተነሳ ባርነትን መርጠዋል። ፍርሃት ባርነትን ብቻ ሳይሆን አመጽን እና አምባገነንነትን ይወልዳል።

በዘመናችን በሚታዩት ክፋቶች እኛም እንደ እስራኤል ሕዝብ ከፍርሃት የተነሳ ነጻነታችንን የመገፈፍ ፈተና ደርሶብናል። ለሚያጋጥሙን ችግሮች መፍትሄ የለም ብለን በፍርሃት ብቻ ተውጠን እንገኛለን። የእግዚአብሔርን አለኝታነት እና የእርሱ የማዳን ሃይል ካልተረዳን በስተቀር በሰዎች የማበረታቻ ቃላት ተስፋ ማድረግ አንችልም። እውነተኛ ተስፋ በማይሰጡን ነገሮች በመመካት እንደ እስራኤል ሕዝብ ጉዞአችንን ቃል ወደ ተገባልን ወደ ነጻነት አገር ከመጓዝ ይልቅ ወደ ባርነት ምድር ወደ ግብጽ መመለስን እንመርጣለን።

ይህ ፍራታችንም ሌሎችን የተረሱትን፣ የተገለሉትን፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሰደት እና መከራ  የደረሰባቸውን እንዳናስብ፣ እንዳንጨነቅላቸው አድርጎናል። ይህ ደግሞ በዛሬው ዓለም በግልጽ የምንመለከተው ነው። ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ለሕይወታቸው ዋስትናን ጥበቃ እና ከለላን በመፈለግ በሮቻችንን በማንኳኳት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ እርዳታ ጠያቂዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ፍርሃት ሊኖር ይችላል። የፍርሃቱ ምንጭም አስቀድሞ አስፈላጊውን ዝግጅት ካለማድረግ የተነሳ ነው። ባለፈው ዓመት ታስቦ በዋለው ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን እንዳሳሰብኩት ሁሉ፣ በባሕልም ሆነ በአስተስሰብ የተለዩ ሰዎች ዘንድ በመሄድ ሃሳባቸውን እና ልምዳቸውን መረዳት ቀላል አይሆንም። ከሰዎች ጋር ሊኖረን የሚገባን ግንኙነት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ወደ ጎን ይባላል።

የተጠራነው ከፍርሃት ወጥተን ልባችንን ክፍት በማድረግ ከሰዎች ጋር ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት እንድናሳድግ ነው። ይህንን ለማድረግ ትክክለኛ የሚያስመስሉ ምክንያቶችን እና የሂሳብ ስሌቶችን ማቅረብ በቂ አይደሉም። ሙሴ ከጠላቶቹ ለመሸሽ የቀይ ባሕርን ለማቋረጥ ሲዘጋጅ ሳለ ለህዝቡ “እግዚአብሔር ሕዝቡን ብቻውን  አይተውምና፣ የማዳን ሥራውን በተግባር ይፈጽማል።  ስለዚህ አይዞአችሁ አትፍሩ” በማለት በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት ገልጾላቸዋ።

ከሌሎች ሰዎች ጋር ግንኑነት ሲኖር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋርም ግንኙነት ይኖራል። ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ በረሃብ፣ በውሃ ጥም፣ በእርዛት፣ በሕመም እና በእስራት ምክንያት ከደረሰባቸው ስቃይ እንድናወጣቸው በሮቻችንን ለሚያንኳኩት በሙሉ እርዳታን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። “እውነት እላችኋለሁ ከእነዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው”። (ማቴ. 25.40)

ከዚህም ጋር በማዛመድ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን “አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” በማለት ብርታትን እንደሰጣቸው በማሰብ (ማቴ. 14.27)፣ የተራቆቱትን፣ የቆሸሹትን፣ የተጎሳቆሉትን፣ የደከሙትን፣ ቋንቋችንን መናገር የማይችሉትን ለይተን ለመመልከት ዓይኖቻችን ቢቸገሩም፣ እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስን በመጥራት ከያዘን ፍርሃት ለመውጣት እንሞክር። ድምጻችንን ወደ እርሱ በምናነሳበት ጊዜ ከፍርሃት የተነሳ ተመልሰን እንወድቅ ይሆናል። ነገር ግን እግዚአብሔር እኛን ለውድቀት አሳልፎ አይሰጠንም። ደካማ እምነት ቢኖረንም ኢየሱስ ክርስቶስ በማዳን ሃይሉ ዘወትር ደግፎን ደስታን በማጎናጸፍ ደቀ መዝሙሩ እንድንሆን ያደርገናል።

በዛሬው ዕለት የተነበቡት የቅዱስ መጽሐፍት ንባባት የምንኖርበትን ዓለም ሁኔታ በትክክል እንድናውቅ የሚያግዙን ከሆነ እግዚአብሔርን በማመስገን፣ የያዘንን ፍርሃት አስወግደን፣ ከደረሰባቸው ችግር እንድናላቅቃቸው በማለት በሮቻችንን ለሚያንኳኩት በሙሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በአካል ተቀብለን ለማስተናገድ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል። ከፍርሃት ለመላቀቅ የቻሉት፣ ከዚህም የተነሳ ደስታን ያገኙት በሙሉ ሌሎችም ነጻ የሚሆኑበትን መንገድ በማሳየት እንዲያግዟቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በማግኘት የእርሱን ድነት እንዲመሰክሩ ተጠርተዋል።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ የዚህ ተልዕኮ ጸጋ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ብቸኛው መታመኛችን በመሆኑ በግልም ሆነ በጋራ ሆነን “ጉልበቴም ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆኖልኛል፤ ስለዚህ አምላኬን አመሰግነውማለሁ፥ ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። በማለት እግዚአብሔር መዳኛቸው ከሆነላቸው ሕዝቦች ጋር ጸሎታችንን እናቀርባለን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት ባቀረቡት የምስጋና ቃላቸው፣ ስብሰባውን ያዘጋጁትን በሙሉ፣ ይነስም ይብዛ ለስደተኞች በሚደረግ የእርዳታ አገልግሎት ላይ የተሰማሩትን በሙሉ አመስግነው፣ ለተቸገሩት በማበርከት ላይ ያሉት አገልግሎት ትንሽ መስሎ ቢታይም በታሪክ ውስጥ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸው፣ በአገልግሎታቸው ወቅት ፍርሃት እንዳይዛቸው፣ በድፍረት ወደ ፊት እንዲጓዙ በማሳሰብ ቡራኬአቸውን በመስጠት አመስግነዋቸዋል።   

16 February 2019, 16:36