ፈልግ

“የኢየሱሳውያን ማህበር ሐዋርያዊ አገልግሎት ምርጫ የቤተክርስቲያንን ቀዳሚ ተልዕኮ በጋራ ማሳካት ነው”

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ስደተኞችን በክብር ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ከማሕበረሰቡ ወደ ተገለሉት ዘንድ መሄድ፣ የወጣቶችን ሕይወት በቅርብ በመከታተል መርዳት፣ እነዚህ አገልግሎቶች ዓለም አቀፉ የኢየሱሳውያን ማህበር፣ የቤተክርስቲያን ቀዳሚ ተልዕኮ የሆኑትን ሐዋርያዊ አገልግሎቶች በመጋራ ሆነው በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የሚያከናውኗቸው መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እርሳቸው የሚገኙበት የኢየሱሳዊያን ማሕበር ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ምርጫ፣ መላዋ ቤተክርስቲያን በቅድሚያ የምታስቀምጣቸውን ሐዋርያዊ እቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ ጠንክረው መሥራት እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ይፋ የሆኑት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮዎች እና ሰነዶች፣ የብጹዓ ጳጳሳት ሲኖዶስ ያጸደቃቸው ሰነዶች፣ የጳጳሳት ጉባኤዎች ያዘጋጁት የሐዋርያዊ አገልግሎ እቅድ “ከወንጌል የሚገኝ ደስታ” የተሰኘውን ሐዋርያዊ ሰነድን መሠረት በማድረግ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ለማበርከት ያታቀዱ እቅዶች መኖራቸውን፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢየሱሳውያን ማሕበር ጠቅላይ አለቃ ለሆኑት ለክቡር አባ አርቱሮ ሶሳ በላኩት መልዕክታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው የቤተክርስቲያን ቀዳሚ ምርጫ፣ ዓለም አቀፉ የኢየሱሳውያን ማሕበር ከሁሉ አስቀድሞ በግልም ሆነ በጋራ ሆነው በሚያደርጉት የጸሎት እና የአስተንትኖ ሕይወት ግንኙነታቸውን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ማድረግ ነው ብለዋል።

ማሕበሩ ጥበብ እና ማስተዋል በታከለበት መንገድ መጓዝ ይኖርበታል

የኢየሱሳውያን ማሕበር የሐዋርያዊ አገልግሎት ምርጫ ብለው ያቀረቧቸው የአገልግሎት ዓይነቶች ለሁለት አመታት ሲመከርበት እና አስተንትኖ ሲደረግበት የቆየ፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችም ዓለማችን የሚገኝበትን ሁኔታ ያገናዘቡ አራት የአገልግሎት ዓይነቶችን ያካተተ መሆኑን የማሕበሩ ጠቅላይ አለቃ የሆኑት ክቡር አባ አርቱሮ ሶሳ አስታውቀዋል። በቅድሚያ ማሕበሩ ጥበብ እና ማስተዋል በታከለበት መንገድ ራሱን በሚገባ ማወቅ እንዳለበት የሚያግዙ የአስተንትኖ እና የጸሎት ጊዜ ሊኖረው እንደሚገባ እና ይህም ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ከዓለማችን ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ ለማከናወን ያግዛል ብለዋል።

ከማሕበረሰቡ ከተገለሉት ጋር መጓዝ፣

ሁለተኛው የአገልግሎት ዘርፍ ከማሕበረሰቡ ዘንድ ከተገለሉት ጋር መጓዝ እንደሆነ የገለጹት አባ አርቱሮ ሶሳ ሰሚ፣ ረዳት እና ተንከባካቢ በማጣት የስቃይ ሕይወት የሚኖሩ በርካታ ሰዎች በዓለማችን እንደሚኖሩ በመገንዘብ፣ በእነዚህ ሰዎች መካከል የዕድሜ፣ የጾታ፣ የባሕል እና የሐይማኖት ልዩነት ሳይደረግባቸው የማሕበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ወጣቶችን መደገፍ፣

ከወጣቶች ጋር በመጓዝ የሚኖሩበትን ዓለም በሚገባ በማወቅ ማገዝ የማሕበራቸው ሦስተኛው የሐዋርያዊ አገልግሎት ምርጫ ወይም ዘርፍ እንደሆን ክቡር አባ አርቱሮ ሶሳ ገልጸው፣ ወጣቶች የምንኖርበትን ዓለም ቶሎ ብለው የመረዳት ችሎታ ስላላቸው በዚህ ረገድ ማሕበራቸውን ማገዝ እንደሚችሉ ገልጸው ከወጣቶች ብዙ መማር እንደሚቻል አስረድተዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤታችንን መንከባከብ፣

የምንኖርባት ምድራችን ለተለያዩ አደጋዎች የተጋለጠች በመሆኗ የጋራ እንክብካቤ እና ጥበቃ ያስፈልጋታል ያሉት አባ አርቱሮ ሶሳ፣ በአራተኛው ሐዋርያዊ የአገልግሎት ምርጫ ይህች ዓለማችን ለሰው ልጆች እና ለፍጥረታት በሙሉ ምቹ  የመኖሪያ ስፍራ እንድትሆን ለማድረግ ነዋሪዎቿ የሚሳተፉባቸውን የተለያዩ እቅዶች በማዘጋጀት በሕብረት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

19 February 2019, 16:53