ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የላምፔዱሳ ስደተኞችን በጎበኙበት ወቅት  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የላምፔዱሳ ስደተኞችን በጎበኙበት ወቅት  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የስደተኞችን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ፣

በሮም የሚገኝ አስታሊ የስደተኞች መቀበያ እና አገልግሎት መስጫ ማዕከል የስብሰባውን ዓላማ ይፋ እንዳደረገው እስካሁን ጠብቆ ላቆየው ባሕል ታማኝ በመሆን የወንድማማችነትን እና የመተጋገዝን መንፈስ ከጊዜ ወይም ከዓመታት መርዘም የተነሳ እንዳይዘነጋ የጣሊያንን መንግሥት ለማሳሰብ ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜያዊ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጭው ዓርብ የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ. ም. በሚካሄደው እና ባሁኑ ጊዜ ስደተኞች የሚገኙበትን የኑሮ ሁኔታ በዝርዝር ለመገምገም ተብሎ፣ በሮም ከተማ አካባቢ፣ ፍራቴርና ዶሙስ ሳክሮፋኖ በተባለ ሥፍራ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዓርብ የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ. ም. የስብሰባው መክክፈቻ የሆነውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት የሚመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበት ይህ ስብሰባ ስብሰባው ባሁኑ ጊዜ ስደተኞች የሚገኙበትን አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታን፣ የሚደረግላቸውንም መስተንግዶን በዝርዝር የሚያጠና እና የሚመለከት መሆኑን አስረድተው ስብሰባውን በጋራ ያዘጋጁትም ካሪታስ ኢጣሊያና ወይም የኢጣሊያ በጎ አድራጊ ድርጅት በሮም ከሚገኝ የአስታሊ የስደተኞች መቀበያ እና አገልግሎት መስጫ ማዕከል መሆናቸውን አስረድተዋል።

ስብሰባው የስደተኛ ቤተሰቦች እና ማሕበራት የሚገኙበት ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ታሕሳስ 29 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮችን ወደ ቫቲካን ተቀብለው እንዳስገነዘቡት ሁሉ፣ ስብሰባውን በጋራ ያዘጋጁት፣ ካሪታስ ኢጣሊያ እና በሮም የሚገኝ አስታሊ የስደተኞች መቀበያ እና አገልግሎት መስጫ ማዕከል የስብሰባውን ዓላማ ይፋ እንዳደረጉት እስካሁን ጠብቆ ላቆየው ባሕል ታማኝ በመሆን የወንድማማችነትን እና የመተጋገዝን መንፈስ ከጊዜ ወይም ከዓመታት መርዘም የተነሳ እንዳይዘነጋ ለኢጣሊያ መንግሥት ድምጽ ለማሰማት እንደሆነ አስረድተዋል። በስብሰባውን የሚሳተፉትም ባሁኑ ጊዜ ስደተኞችን ወደ ግል መኖሪያ ቤታቸው እንዲሁም ወደ ማዕከላቸው ተቀብለው በማስተናገድ ላይ በመላው ኢጣሊያ የሚገኙ ቤተሰቦች፣ ቁምስናዎች እና ማሕበራት እንደሆኑ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

ስብሰባው ለኢጣሊያ መንግሥት መልዕክት ለማስተላለፍ ታስቦ የሚድረግ ነው፣

በኢጣሊያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በጎ አድራጊ ድርጅት ካሪታስ ኢጣሊያና የስደተኞች ፋውንዴሽን ዳይሬክተር የሆኑት አባ ጂቫኒ ደ ሮቤርቲስ፣ ስደተኞችን ወደ ቤታቸው፣ ወደ ማዕከላቸው በማስገባት እገዛን ከማድረግ አንስቶ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ የረዲኡትን በሙሉ አመስገነው፣ ዛሬ በኢጣሊያ ውስጥ መንግሥት ማበርከት የሚችለው የእርዳታ እጅ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው ብለው ይህም በቂ እንዳልሆነ ገልጸው በተለይም ለስደተኞች የሚሰጥ ሰብዓዊ ክብር ማነስ እንደሌለበት አስረድተው የሳክሮፋኖ ስብሰባ ዋና ዓላማ የኢጣሊያ መንግሥት እምነት የተጣለበትን የዕርርዳታ አገልግሎትን ለስደተኞች እንዲያቀርብ ለማሳሰብ ነው ብለዋል።

ስብሰባው ለኢጣሊያ መንግሥት በሚልከው መልዕክት ይፈጸማል፣

ስብሰባው ለስደተኞች በመደረግ ላይ ባሉት የተለያዩ የእርዳታ አገልግሎቶች ላይ እንደሚወያይ፣ በተጨማሪም በመርሃ ግብሩ መሠረት የጸሎት እና የአስተንትኖ፣ ከስደተኞች የሚቀርቡ ምስክርነቶች የሚሰሙበት፣ በጋራ ሆነ በግል የሠሯቸው ባሕላዊ የስነ ጥበብ ሥራዎች የሚቀርቡ መሆኑ ታውቋል። በመጨረሻም በሮም ከተማ የአስታሊ የስደተኞች መርጃ ማዕከል ፕሬዚደንት የሆኑት አባ ካሚሎ ሪፓሞንቲ ስብሰባውን በተካፈሉ የመንግሥት ተወካዮች በኩል ለኢጣሊያ መንግሥት በሚልኩት መልዕክት የሚጠናቀቅ መሆኑን፣ በቅድስት መንበር የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜያዊ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ገልጸዋል።                 

12 February 2019, 16:43