ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተካፋዮች ንግግር ሲያደርጉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተካፋዮች ንግግር ሲያደርጉ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ስብሰባ ተካፋዮች ንግግር አደረጉ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ፣ ኢፋድ 42ኛውን ዙር የዳይሬክተሮች ቦርድ ዓመታዊ ስብሰባ፣ በሮም በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት ዛሬ መጀመሩን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። ከዛሬ የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ. ም. የተጀመረው የድርጅቱ ስብሰባ ነገ የሚጠናቀቅ ሲሆን የመነጋገሪያ ርዕሥም በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች የምርት መጠንን እና ጥራትን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት የድርጅቱ ተጨማሪ እገዛ ምን ሊሆን ይገባል የሚል እንደሆነ ዘገባው አክሎ ገልጿል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ስብሰባው በሚካሄድበት በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተካፋዮች ያደረጉትን ንግግር ትርጉም እናቀርብላችኋለን።

ክቡር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ፕሬዚደንት፣

ክቡራት እና ክቡራን የመንግሥታት መሪዎች፣

ክቡር የኢጣሊያ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክርቤት ፕሬዚደንት፣

ክቡራን ሚኒስትሮች፣

ክቡራን የመንግሥታት ልኡካን እና ቋሚ ተወካዮች፣

ክቡራን እና ክቡራት፣

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ፕሬዚደንት በድርጅታቸው ስም ያደረጉልኝን ግብዣ በደስታ በመቀበል፣ ለ42ኛ ጊዜ በተዘጋጀው የአስተዳድር ቦርድ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እገኛለሁ ካሉ በኋላ በስባሰባው የተገኙበትን ዓላማ ሲገልጹ በዓለማችን ውስጥ በስቃይ ላይ የሚገኙትን የበርካታ ሰዎች ምኞት እና ፍላጎት ለማሰማት እንደሆነ ገልጸዋል። ጩሄታቸው ተደማጭነት እንዲኖረው፣ ጭንቀታቸውም ግንዛቤን እንዲያገኝ ፊታችንን ወደ እነርሱ መመለስ አለብን ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአስከፊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙትን የእነዚህ ሰዎች ሕይወት የተመለከትን እንደሆነ፣ የሚተነፍሱት አየር ተበክሏል፣ የተፈጥሮ ሀብቶች ደርቀዋል፣ ወንዞች በኬሚካሎች ተበክለዋል፣ የእርሻ መሬታቸው ወደ አሲዳማነት ተለውጠዋል፣ ለእነርሱም ሆነ ለሰብሎቻቸው በቂ ውሃ የላቸውም፣ የጤና መሠረተ ልማትዎ በጣም ደካማ፣ መጠለያቸውም ምቹ አይደሉም። በሌላ ወገን አሁን የምንኖርበት ማሕበረሰባችን በርካታ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችሉ እውቀቶችን በማካበት ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል። በትክክል የምንጠቀም ቢሆን ረሃብን ሆነ ሌሎችንም ማሕበራዊ ችግሮች ማቃለል እንችላለን። ብሶት ዘወትር እየሰሙ ዝም ከማለት ይልቅ መፍትሄን ለማግኘት በጋራ በርትተን ብንሠራ ይሻላል። ረሃብ ጊዜ እና ቀጠሮ የሚሰጠው አይደለም። ትቶ የሚያልፈውን ስቃይ ማስታወስ ይቻላል። ረሃብን ለማስወገድ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፣ የሲቪል ማሕበረሰብ እና የተፈጥሮ ሃብትን መጠቀም የቻሉት ወገኖች ድጋፍ ያስፈልጋል።

ቅድስት መንበር፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ፣ ኢፋድ ድህነትን ለማስወገድ ያደርጋቸውን ጥረቶች እና የወሰዳቸውን እርምጃዎች ስትደግፍ መቆየቷን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በታሕሳስ ወር 1957 ዓ. ም. በሕንድ ቦምቤይ ከተማ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ረሃብን እና ድህነትን ለመዋጋት ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ቅድስት መንበር  የድርጅቱን ዓላማ እና ተግባር በመደገፍ እና በማሳደግ ረገድ ያልተቋረጠ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን አስረድተዋል።

ዘንድሮ ለ42ኛ ጊዜ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ የአስተዳድር ቦርድ ዓመታዊ ስብሰባ ድርጅቱ የቆመለትን ዓላማ ለማሳካት እያንዳንዱን አገር የሚያጋጥመውን ችግር መጋፈጥ እንዲችል ማስተባበር ይኖርበታል ብለዋል። ከዚህም ጋር አያያዘው ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እስከ 2022 ዓ. ም. ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ የነደፋቸው 17 የዘላቂ ልማት እቅዶች መኖራቸውን አስታውሰው ከእነዚህ የዘላቂ ልማት እቅዶች መካከል የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ድህነትን ማስወገድ እና ረሃብን መዋጋት መሆኑን ገልጸዋል። በዓለማችን በገጠራማው አካባብቢ በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩትን አርሶ አደሮች መደገፍ እንደሚያስፈልግ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው ባሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በረሃብ እና በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩ 820 ሚሊዮን ሰዎች የሚገኙት በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ ናቸው በማለት አስረድተዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለተሰብሳቢዎች ባሰሙት ንግግር የአካባቢው ልማት በራሱ ዋጋን የሚያስከፍል፣ እያንዳንዱ ግለሰብ እና ማሕበረሰብ ጉልበታቸውን በማፍሰስ፣ ችሎታቸውንም ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ለሰው ልጅ ሕይወት ተስማሚ የሆነ ዓለምን ለመገንባት የሚያስችል ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ሃላፊነትን በመውሰድ፣ የማምረት አቅማቸውን በመጠቀም ድህነትን ለማጥፋት፣ ረሃብን ለመዋጋት የሚችሉ በርካታ መንግሥታት እና ድርጅቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እነዚህ መንግሥታት እና ድርጅቶች የገጠራማውን አካባቢ መሬቶችን በማልማት የበኩላቸውን ድርሻ እና ሃላፊነት በተግባር መወጣት ይችላሉ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ችግሮች የሚወገዱበትን መንገድ ሲያመለክቱ እዳሉት በአንዳንድ አካባቢዎች በርካታ ድርጅቶች ወይም መንግሥታት በግል የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ ሊያደርጋቸው እንደማይችል ነገር ግን ጉልበታቸውን ከሌሎች ጋር በማስተባበር በጋራ ቢሰሩ መልካም ውጤቶችን ማስመስገብ ይቻላል ብለው መፍትሄው ጥረታችንን ባስተባበር፣ ግንኙነታችንንም ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል። በዓለማችን ዙሪያ የሚታዩት ችግሮች መጠነ ሰፊ ናቸው ያሉት ቅዱስነታቸው አስቸኳይ መፍትሄን የሚሹ እና የማያቋርጥ ጥረት የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል።

ድህነትን ለማስወገድ፣ ረሃብንም ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ውስጥ ቀዳሚ ስፍራ ሊሰጠው የሚገባው የሰው ልጅ ሕይወት እንደሆነ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ችግሮችን ለማስወገድ በተግባር እየተገለጹ የሚገኙት ዘዴዎች ከውጫዊ አካል የሚመጡ ሳይሆን የሰዎችን ባሕል ያካተቱ መሆን አለባቸው።

ይህን በማድረጉ በመጨረሻዎቹ ዓመታት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ያመጣውን መልካም ውጤት መጥቀስ ይቻላል ብለው የግብርናውን ምርት ለማሳደግ፣ ረሃብን በዘላቂነት ለመቀነስ፣ የገጠራማውን አካባቢ ወደ ምርታማነት ለመለወጥ የሚያግዙ የተለያዩ የሥራ ፈጠራ እቅዶችን፣ አዳዲስ ሃሳቦች እና አመለካከቶች ማስተባበር ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም የስብሰባውን ተካፋዮች በሙሉ፣ ከማሕበረሰቡ ተገልለው በረሃብ እና በድህነት የሚሰቃዩትን ከችግራቸው ለማውጣት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ውስጥ በተለያዩ የሥራ ድርሻ ላይ ተሰማርተው ለሚገኙት በሙሉ ብርታትን ተመኝተው፣ የግለኝነትን ባሕርይ አስወግደን በሕብረት የምንቆም ከሆነ ረሃብን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንችላለን፣ ፍትህን እና ብልጽግናን ማየት እንችላለን ብለው የስብሰባውን ተካፋዮች በሙሉ አመስግነው ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።                       

14 February 2019, 16:18