ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ቤተክርስቲያንን ከልብ የሚወዳት ሊያጠፋት አይነሳም”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢጣሊያ የበነቨንቶ ሊቀ ጳጳሳት፣ ብጹዕ አቡነ ፌሊቸ አክሮካ ወደ 2500 ከሚገመቱ የሃገረ ስብከታቸው ምዕመናን ጋር በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተገኙበት ወቅት ከትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አስቀድመው ባሰሙት ንግግር፣ ቤተክርስቲያንን ከልብ መውደድ ማለት ይቅርታንም ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል። በመጋቢት 8 ቀን 2010 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅዱስ ፒዮስ ቅንዋት የታየበትን መቶኛ ዓመት እና ያረፈበትን 50ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ለተገኙት ምዕመናን እንደገለጹት ክብረ በዓሉ የቅድስና አዋጅ ይፋ የሆነበት ዕለት ይመስላል በማለት በምዕመናኑ ብዛት መገረማቸው ይታወሳል። 

ቅዱስነታቸው፣ ፍራንችስካዊ መነኩሴ የነበረው ቅዱስ አባ ፒዮስ ቤተክርስቲያንን ከልብ እንደወደዳት፣ ወደ ፔትርልቺና ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ገልጸው እንደ ቅዱስ አባ ፒዮስ ቤተክርስቲያንን ማፍቀር እያንዳንዱ ምዕመን እምነቱን የበለጠ እንዲያሳድግ ያግዛል ብለዋል። ቅዱስ አባ ፒዮስ ሕይወቱን ለወንጌል አገልግሎት የሰጠ፣ የማያወላውል ሰማያዊ ተስፋን የሰነቀ እንደነበር ገልጸዋል። ቅዱስ አባ ፒዮስ ቤተክርስቲያንን ከልብ ወዷታል ያሉት ቅዱስነታቸው ቤተክርስቲያን ብዙ ችግሮች ቢያጋጥማትም፣ ብዙ ጠላቶች ቢኖሯትም፣ በውስጧ ብዙ ሐጢአተኞች ቢገኙባትም ቅዱስ አባ ፒዮስ ቤተክርስቲያንን ከመውደድ ወደ ኋላ አላለም፣ ምክንያቱም ቤተክርስቲያን ቅድስት እና የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ እንደሆነች አስረድተው ነገ ግን እኛ ልጆቿ ሐጢአተኞች ነንስንሆን ከእኛም መካከል ወደ ከፋ ሐጢአት ውስጥ የወደቁ አሉ ብለዋል። ቅዱስ አባ ፒዮስ ቤተክርስቲያንን የወደዳት ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት በመሆኗ እንጂ በዘመናችን እንደሚሰማው ስም በማጥፋት እና በሐሜት ሊያጠፋት አልተነሳም ብለዋል። ቤተክርስቲያንን የሚወድ ይቅርታ ማድረግንም ያውቃል ብለው ምክንያቱም እርሱ ራሱ የእግዚአብሔር ምሕረት የሚያስፈልገው መሆኑን ስለሚገነዘብ ነው ብለዋል።

ሕይወትን በሙሉ ቤተክርስቲያንን እየከሰሱ መኖር አይቻልም፣

ምሕረትን በማድረግ የሰውን ልጅ ወደ ትክክለኛ መንገድ ሊመራ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ወደ መልካም ጎዳና ለመመለስ ታስቦ የሚደረግ ተግሳጽ መልካም ነው ብለው ይህም ቤተክርስቲያንን ከመውደድ ወይም ከማፍቀር የተነሳ መሆን አለበት ብለዋል። ቅዱስ አባ ፒዮስ ቤተክርስቲያንን የወደዳት ከሙሉ ችግሮቿ እና በልጆቿ በኩል ከሚፈጸሙ በደሎች እና ሐጢአቶች ጋር ነው ብለዋል። በሕይወት ዘመን ሁሉ ቤተክርስቲያንን እየከሰሱ እና ስሟን እያጎደፉ መኖር አይቻልም ብለው ለመሆኑ የዚህ ከሳሽ መኖሪያው የት አለ? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ታላቁ ከሳሽ ሰይጣን አይደለምን? ስይጣን የከሳሾች አባት ነው እንዳይባል ሰይጣን ልጆች የሉትም፣ ነገር ግን ወዳጆች ወይም ዘመዶች ይኖሩታል ብለዋል።

ፍቅር ከጥላቻ እንደሚበልጥ መመስከር ያስፈልጋል፣

እውነተኛ የሆነውን የእግዚአብሔር ፍቅር መያዝ ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የእግዚአብሔር ፍቅር የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ነው ብለዋል። የእግዚአብሔር ፍቅር የደካሞችን ሕይወት የሚለውጥ፣ እውነተኛ ፍቅርን ለሚሹት ፈጥኖ የሚደርስ ፍቅር ነው ብለዋል። እያንዳንዳችን መለኮታዊ ቸርነትን በማሳደግ ፍትህ እና አንድነት የሚገኝበት ዓለም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን ማድረግ የምንችለው የእውነተኛ ፍቅር መስካሪዎች ሆነን ስንገኝ ነው ብለዋል። ቅዱስ ፍራንቺስኮስ ተከታዮቹን ሂዱ እምነታችሁን፣ ፍቅራችሁን በቃል ሳይሆን በተግባር መስክሩ። አንዳንድ ጊዜ በቃልም መመስከር ያስፈልግ ይሆናል ነገር ግን ክርስቲያናዊ የሆነ ሕያው ምስክርነታችሁን በተግባር ግለጹ። ፍቅር ከጥላቻ፣ ወዳጅነት ከጠላትነት እንደሚበልጥ በመገንዘብ በመካከላችን በተግባር የሚገልጽ ወንድማማችነት ከጦርነት ይሻላል ብለዋል።          

21 February 2019, 17:20