ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በጋራ መከላከል ያስፈልጋል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ጨምሮ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚታዩ ሌሎች ችግሮችም ከብጹዓን ጳጳሳት፣ ከካህናት እና ደናግል በተጨማሪ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማሕበራት ውስጥ የሚገኙ ምእመናን ሃላፊነት እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው እሁድ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች፣ በሉቃስ ወንጌል ላይ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥ የሚረግሟችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሏችሁም ጸልዩ” (6፡27-38) በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ  መሠረት በማድረግ ካቀረቡት አስተንትኖ ቀጥለው በቫቲካን ከተማ ከየካቲት 14 ቀን እስከ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ሲካሄድ የቆየውን እና የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሊቃነ መናብርትን፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የምስራቅ ቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮን የሚከተሉ ብጹዓን ፓትሪያርኮችን፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የልዩ ልዩ ገዳማት አለቆችን እና ጥሪ የተደረገላቸውን ምሁራንን ያሳተፈ ስብሰባን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል። የስባሰባው ዋና ዓላማም ከጥቃት ለማምለጥ አቅም በሚያንሳቸው ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ በደሎችን ለመከላከል የሚያስችሉ መንገዶችን የሚያፈላልግ እንደነበር ገልጸዋል።

በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በብዛት የሚወሩ የቤተክርስቲያናችን ችግሮች ናቸው ያሉት ቅዱስነታቸው እነዚህ ጥቃቶች በሕጻናት ላይ ከሚያደርሱት የስነ ልቦናዊ ጉዳት ባሻገር ጥቃቱን የፈጸሙ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ባፈጸሙት በደል ተጸጽተው ይቅርታን አለመጠየቃቸው፣ ከዚህም በላይ በቤተክርስቲያን የሃላፊነት አደራ ያለባቸው አባቶች ለጉዳዩ ትኩረትን ካለመስጠት የተነሳ ከፍተኛ ወቀሳን አስከትሏል ብለዋል።

ችግሩ በአምስቱም አህጉራት ውስጥ የሚታይ ችግር ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ጨምሮ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚታዩ ሌሎች ችግሮችም ከብጹዓን ጳጳሳት፣ ከካህናት እና ደናግል በተጨማሪ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማሕበራት ውስጥ የሚገኙ ምእመናን ሃላፊነት እንደሆነ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን በመቀጠል አራት ቀናትን በወሰደው የስብሰባ ቀናት ጥቃቱ ከደረሰባቸው ሰዎች አንደበት የጥቃቱን አስከፊነት አዳምጠናል ብለው የስብሰባው ተካፋዮች በሙሉ የተፈጸሙትን ሐጢአቶች በማስታወስ እና ከልብ በመጸጸት ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን መለመናቸውን ገልጸዋል። የቤተክርስቲያን አገልግሎት ከባድ አደራ እና ሃላፊነት የተጣለበት እንደሆነ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእውነት እና በፍትህ ማገልገል የቤተክርስቲያን አባቶች የሕሊና ግዴታ ነው እንደሆነ አስረድተው በቤተክርስቲያን ውስጥ የአገልግሎት ስልጣንን ለተሳሳተ ዓላማ መጠቀምን በሙሉ ድምጽ መቃወም ያስፈልጋል ብለዋል።

አክለውም በቤተክርስቲያን በኩል ለታዳጊ ሕጻናት የሚሰጡ አገልግሎቶች ደህንነታቸውንም የሚያስጠብቁ መሆን ያስፈልጋል ብለው ይህን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበርታል ብለዋል። ቤተክርስቲያን ሙሉ እምነት የሚጣልባት፣ የአገልግሎት ተልእኮዋንም በታማኝነት የምታከናውን እና ታዳጊ ሕጻናትን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለችውን ትምህርት የምታስተምር መሆን አለባት ብለዋል።

በዓለም ዙሪያ በሙሉ በጎ ፈቃድ ካላቸው የማሕበረ ሰብ አባላት ጋር በመተባበር በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙትን ጥቃቶች መከላከል የሚቻለው በሕብረት በመሥራት እንደሆነ አስረድተዋል መልዕክታቸውን ፈጽመዋል።

26 February 2019, 16:47