ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “እኛ ለጋሾች ስንሆን እግ/ር ታላላቅ ነገሮችን በሕይወታችን ውስጥ ይፈጽማል”

ተስፋ ቆርጠው እና ደክመው ለነበሩ ለስምዖን እና ለሌሎች ዓሳ አስጋሪዎች በኢየሱስ የተከናወነው ታላቁ ተአምር መረባቸው እስኪሞላ ድረስ ዓሳ መያዛቸው ሳይሆን በተስፋ መቁረጥ መንፈስ የተነሳ የሽንፈት መንፈስ ውስጥ ገብተው እንዳይሰቃዩ በማሰብ ያደርገው ትላቅ ተዐምር ነው።

ርዕሰ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በዕለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት በትላንትናው እለት ማለትም በየካቲት 03/2011 ዓ.ም ያደርጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ 5፡1-11 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና ጴጥሮስ እና ጓደኞቹ ኢየሱስ ባዘዛቸው መሰረት መረባቸውን ጥለው በጣም ብዙ ዓሳ መያዛቸውን፣ በዚህም የተነሳ ጴጥሮስ በኢየሱስ እግር ሥር ተንበርክኮ “መምህር ሆይ እኔ ኃጢኣተኛ ሰው ነኝ እና ከእኔ ራቅ” ብሎ በተናገረው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 03/2011 ዓ.ም በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመስርተው ያደርጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ሉቃ 5 1-11) ወንጌላዊው ሉቃስ የቅዱስ ጴጥሮስን ጥሪ የሚያመለክት ታሪክ ያቀርብልናል። የእርሱ ስም ስምዖን እንደ ሚባል እና ዓሳ አስጋሪ እንደ ነበረም ይታወቃል። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ዳርቻ አከባቢ ሲመላለስ በባሕር ዳርቻ ላይ ሆኖው የዓሣ ማስገሪያ/ማጥመጃ መረቦቻቸውን ስያበጃጁ ነበር የተመለከተው። በዚያ ምሽት ምንም ዓይነት ዓሳ ስላልያዘ በጣም ደክሞት እና ተስፋ ቆርጦ በነበረበት ወቅት ነበር ያገኘው። እናም ጴጥሮስ ባልጠበቀው መልኩ እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ ኢየሱስ ጴጥሮስን እንዲገረም ያደርገዋል፡ በእርሱ ጀልባ ላይ ይወጣና ጀልባዋን ወደ ባሕሩ ትንሽ ፈቀቅ እንዲያደርግ ይጠይቀዋል፣ ምክንያቱ በእዚያ ካሉ ሰዎች ጋር መነጋገር ፈልጎ ነበር - በእርግጥ በእዚያን ስፍራ ብዙ ሰዎች ነበሩ። በእዚህ ዓይነት ሁኔታ ኢየሱስ በስምዖን ጀልባ ላይ ተቀምጦ በባሕሩ ዳርቻ የተሰበሰቡትን ሰዎች ማስተማር ጀመረ። ነገር ግን የእርሱ ቃሎች መተማመንን የሚፈጥሩ በመሆናቸው የተነሳ የስምዖንን ልብ ዳግም በመክፈት በእርሱ እንዲታመን ያደርገዋል። ከዛም ኢየሱስ ሌላ አስገራሚ ነገር እንዲከሰት ለማድረግ "ተንቀሳቀሰ"  እንዲህ አለው: “ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ወደ ውሃ ውስጥ ጣሉ አለቸው” (ሉቃ 5፡4)።

ስምዖንም መልሶ “ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም”  በማለት የተቃውሞ መልስ ይሰጣል። እንደ አንድ የዓሳ አጥማጅ ባለሙያ “ማታ ምንም ዓይነት ዓሳ ካልያዝን፣ በቀን ደግሞ ምንም ልንይዝ አንችልም” በማለት ጨምሮ መናገር ይችል ነበር። ነገር ግን በተቃራኒው ኢየሱስ በእዚያ ስፍራ በመገኘቱ ተደስቶ እና በእርሱ ቃል ብርሃን ታግዞ “ . . . ነገር ግን በቃልህ ተማምኜ መረቡን እጥላልሁ” በማለት መለሰ። ይህም በእምነት የተሰጠ ምላሽ ነው፣ እኛም በዚህ መልኩ ምላሽ እንድንሰጥ ተጠርተናል፡ ይህም ጌታ የእርሱ ደቀ-መዛሙርት ሁሉ ሊኖራቸው የሚፈልገው ዓይነት ባህሪይ ሲሆን በተለይም ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያየ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች እንዲኖራቸው የሚፈልገው ዓይነት ባህሪይ ነው። የጴጥሮስ ታዛዥነት ከፍተኛ ውጤት ያስገኛል “ይህንንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ” (ሉቃ 5፡6) ይለናል።

ይህ ተአምራዊ የሆነ የዓሣ ጠመዳ ነበር፣ የኢየሱስን ኃይል ያመለክታል፡ እርሱን ለማገልገል እራሳችንን በልግስና ስናቀርብ በእኛ ውስጥ ታላላቅ ነገሮችን ይፈጽማል። በዚህ መንገድ እርሱ በእያንዳንዳችን ላይ ይሠራል: እንደገና ከእርሱ ጋር በአዲስ መልክ ሕይወትን ለመጀመር እንድንችል እና በአስደናቂ ሁኔታ የተሞላውን አዲስ ባህር ለመሻገር እንድንችል እርሱ በህይወታችን ጀልባ ውስጥ እንዲገባ ልንጋብዘው ያስፈልጋል። በአሁን ወቅት ካለው ክፍት ከሆነው ሰብዓዊ ውቅያኖስ እንድንወጣ እኛን በመጋበዝ የእርሱን  መልካምነት እና ምህረት መስካሪዎች እንድንሆን፣ ለእኛ ሕልውና አዲስ ትርጉም ይሰጣል። አንዳንዴ መለኮታዊው መምህር ለእኛ በሚያቀርበው ጥሪ በመገረም እና በመደነቃችን የተነሳ ‘እኔ የተገባው አይደለሁኝም’ በሚል እሳቤ ተነሳስተን ጥሪውን ላለመቀበል ልናገራግር እንችላለን። ስምዖን ጴጥሮስም ቢሆን በአስደናቂ ሁኔታ በጣም ብዙ ዓሳዎችን ከያዘ በኋላ “ጌታ ሆይ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ራቅ” ብሎ ተናግሮ የነበረውም በዝሁ ምክንያት ነው። “ጌታ ሆይ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ራቅ” የሚለው የዚህን ዓይነት ትሁት የሆነ የትሕትና ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው። እርሱ ግን ይህንን የተናገረው በወቅቱ “እርሱ ጌታ መሆኑን” በመረዳቱ የተነሳ በኢየሱስ እግር ሥር ተንበርክኮ ነበር የተናገረው። ኢየሱስም “ ስምዖንን ሆይ! አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” በማለት ያበረታታዋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር በእርሱ ከተማመንን ከኃጢአታችን ነጻ ያወጣናል፣ በፊታችን አዲስ አድማስ ይከፍትልናል የእርሱ ተልዕኮ ተባባሪዎች እንድንሆን ያደርገናል።

ተስፋ ቆርጠው እና ደክመው ለነበሩ ለስምዖን እና ለሌሎች ዓሳ አስጋሪዎች በኢየሱስ የተከናወነው ታላቁ ተአምር መረባቸው እስኪሞላ ድረስ ዓሳ መያዛቸው ሳይሆን በተስፋ መቁረጥ መንፈስ የተነሳ የሽንፈት መንፈስ ውስጥ ገብተው እንዳይሰቃዩ በማሰብ ያደርገው ትላቅ ተዐምር ነው። በዚህም ተግባሩ የእርሱ ቃል እና የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስክሮች እንዲሆኑ መንፈሱን ገለጸላቸው። እናም “ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት” እንደ ሚለው የአንድ ደቀ-መዝሙር ምላሽ በዚሁ መልክ ፈጣን እና ሁለንተናዊ ሊሆን ይገባል። ራሷን ለእግዚኣብሔር ፈቃድ ያስገዛችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚኣብሔር የሚያቀርብልንን ጥሪ መስማት እንችል ዘንድ ከእርሱ ጋር ተባብረን መስራት እንችል ዘንድ እንድታግዘን የእርሱን የደህንነት ቃል በመላው ዓለም ማዳረስ የምንችልበትን ጸጋ እንድትሰጠን ልንማጸናት ይገባል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ርዕሰ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በየካቲት 03/2011 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ
10 February 2019, 15:04