ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የፍቅርን ባሕል መለማመድ ምህረት የማድረግ ባሕል እንዲፈጠር ያደርጋል”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እርሳቸው በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ለመከታተል ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በየካቲት 17/2011 ዓ.ም ቅዱስነታቸው ያሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል (6፡27-38) ላይ ተወስዶ በተነበበውና “ጠላቶቻችሁን ውደዱ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ” (ሉቃስ 6፡27-28) በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “የጥላቻ መንፈስን ድል ለማድረግ ይቻል ዘንድ የምህረት እና የይቅርታ ባህል መከተል እንደ ሚገባ” ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በትላንትናው እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮ አደባባይ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 6፡27-38) የክርስቲያን ሕይወት ማዕከላዊና ባህሪያዊ ነጥብ የሆነውን ጠላቶቻችንን መውደድ እንዳለብን ያሳስበናል። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ግልፅ ናቸው፦ “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ” (ሉቃስ 6፡27-28) በማለት ይናገራል። እናም ይህ አማራጭ ሳይሆን ነገር ግን ትዕዛዝ ነው። ይህ ትዕዛዝ ለሁሉም የተሰጠ ሳይሆን ነገር ግን ኢየሱስ “ለእናንተ ለምትሰሙኝ” በማለት ለተቀሳቸው ለደቀ-መዛሙርቱ የሰጠው ትዕዛዝ ነው። እርሱ ጠላቶቹን ከመውደድ ባሻገር መሄድ እንዳለበት በደንብ ጠንቅቆ ያውቃል፣ ለዚህም ነው ሥጋ ለብሶ ሰው የሆነው፣ እኛንም ባለንበት ቦታ እንዲያው ሊተወን አስቦ ሳይሆን ነገር ግን የአባቱን እና የእኛም አባት የሆነውን አብ ታላቅ ፍቅሩን ሊያሳዩ የሚችሉ ወንዶችና ሴቶች መሆን እንችል ዘንድ መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ ሊረዳን መጣ። ይህም ኢየሱስ እርሱን "ለሚያዳምጡ" ሰዎች የሚሰጠው ፍቅር ነው። ከእዚያን በኋላ ሁሉም ነገር ይቻላል! ከእርሱ ጋር፣ ለእርሱ ፍቅር እና ለመንፈሱ ምስጋና ይግባውና እኛን የማይወዱንን ሰዎች ሳይቀር መውደድ እንችላለን።

በዚህ መንገድ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ፍቅር የትኛውንም ዓይነት ጥላቻና ክፋት እንዲያሸንፍ ይፈልጋል። የክርስቶስ መስቀል ውጤት የሆነው የፍቅር አመክንዮ የክርስቲያን አርማ በመሆኑ የተነሳ ሁሉንም ሰዎች በወንድማዊ ፍቅር ለመገናኘት እንድንችል ይረዳናል። ነገር ግን የሰውን ደመ ነፍሳዊ የሆነ ስሜት እና ዓለማዊ የሆነ የመበቀል ሕግን እንዴት ማስወገድ ይቻላል? የዚህ ጥያቄ መልስ ደግሞ በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ይገኛል እንዲህም ይላል “የሰማይ አባታችሁ መሃሪ እንደ ሆነ እናንተም መሃሪዎች ሁኑ” (ሉቃስ 6፡36) ይለናል። ኢየሱስን የሚያዳምጥ ሰው ምንም እንኳን ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለው ቢሆንም  እርሱን ለመከተል የሚጥር ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል፣ እናም በሰማይ ካለው አባት ጋር መመሳሰል ይጀምራል። ከዚህ ቀደም ልንናግራቸው ወይም ልንሰራቸው ባለመቻላችን ምክንያት የአፈርንባቸውን ሁኔታዎች በመቀየር ነገሮችን የማከናወን ችሎታ እንድናገኝ በማድረግ አሁን ደግሞ ደስታን እና ሰላምን እንድንጎናጸፍ ያደርገናል። ከዚህ በኋላ ደግሞ በኃይል እና በንግግሮች ሁከት መፍጠር የለብንም፣ እኛ እራሳችን ቸር እና መልካም መሆናችንን እንገነዘባለን፣ እኛም ይህ ያገኘነው ነገር ከእኛ ከራሳችን የመጣ ነገር ሳይሆን፣ ነገር ግን ይህ ነገር ወደ እኛ የመጣው ከእርሱ መሆኑንም እንረዳለን፣ በዚህም ምክንያት ልንኩራራ አይገባም፣ ነገር ግን አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል።

ከፍቅር በላይ የሆነ ታላቅና የበለጠ ፍሬያማ የሚያደርግ ነገር የለም፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ሙሉ መብታቸውን ይሰጣል፣ በተቃራኒው ግን ጥላቻ እና በቀል ያጠፋል፣ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን ፍጥረት ውበት ያበላሹታል።

ይህ ትዕዛዝ በስድብ እና በተሳሳተ መንገድ ላይ ለሚመላለሱ ሰዎች በፍቅር ምላሽ ለመስጠት ይቻል ዘንድ በዓለም ላይ አዲስ ባህል አመጣ፡ “ይህም አዲስ ባሕል ምሕረት የማድረግ ባሕል ይባላል- ይህንንም የግድ በሚገባ መማር ይኖርብናል! ይህንን ምሕረት የማድረግ ባሕል በሚገባ ተግባራዊ ማድረግ ይገባናል-ይህም እውነተኛ የሆነ ሰላም ይሰጣል፣ ሕይወታችንን በአዲስ መልክ ያድሳል”። የፍቅር ኡደት ገጸባሕሪን በሕይወታቸው ተውነው ያለፉት የሁልጊዜም ሰማዕታት ምስክሮች ናቸው፣ እንዲያሁም እኛን የሚያሳድዱንን ሰዎች ፍቅር በማሳየት የምንመልሰው በፍቅር የተሞላ ባህሪ በከንቱ እንደማይቀር ኢየሱስ ያረጋግጥልናል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ “አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ […] ምክንያቱም በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና” (ሉቃስ 6፡ 37-38)። ይሄ በጣም ጥሩ የሆነ ነገር ነው። ለጋስ እና መሃሪ ከሆንን እግዚአብሔር የሚሰጠን መልካም ነገር ነው። ይቅር ማለት አለብን ምክንያቱም እግዚአብሔር ይቅር ብሎናል፣ እርሱ ሁልጊዜ ይቅር ይለናል። ሙሉ በሙሉ ይቅር ማለት ካልቻልን ደግሞ እኛም ሙሉ በሙሉ ይቅር አንባልም። ይልቁንም ልባችን ይቅር ለማለት ክፍት ከሆነ፣ ይህ ይቅርታ በወንድማማችነት መንፈስ በመተቃቀፍ ተጨባጭ በሆነ መንገድ ከተገለጸ እና ጥብቅ የሆነ ኅበረት መፍጠር ከቻለ ክፉ ነገሮችን ማሸነፍ እንደ ሚቻል በዓለም ፊት እንመሰክራለን ወይም እናውጃለን ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በእኛ ላይ የፈጸሙብንን በደሎች እና በእኛ ላይ የተደረጉትን ክፉ የሆኑ ነገሮችን ማሰብ እንጂ መልካም የሆኑ ነገሮችን ማስታወስ አይቀናንም፣ የዚህ ዓይነት ልማድ ያላቸው ሰዎች አሉ፣ የዚህ ዓይነቱ ባሕሪይ ቀስ በቀስ ወደ በሽታ ይቀየራል። እነርሱ “ፍትህን ብቻ የሚሹ ሰዎች” ይባላሉ፣ በእነርሱ ላይ የተፈጸሙትን መጥፎ የሆኑ ነገሮችን ብቻ ያስታውሳሉ። እናም ይህ መልካም የሆነ መንገድ አይደለም። በተቃራኒው መመልከት አለብን በማለት ኢየሱስ ተናግሯልና። መልካም የሆኑ ነገሮችን ማሰብ፣ አንድ ሰው ወደ እኛ መጥቶ ስለሌላ ሰው መጥፎ ነገር ቢያወራ “አዎን ይህ እውነት ሊሆን ይችላል. . . ነገር ግን ይህ ሰው እነዚህን የመሳሰሉ መልካም የሆኑ ጎኖች አሉት . . .” ብለን ልንመልስ ይገባል። ወሬውን በመልካም ሁኔታ መቀየር። ይህም የምሕርት ኡደት ይባላል።

ይህ ቅዱስ፣ እንደ እሳት የሚያቃጥል፣ መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ የሚረዳን እና ምላሽ ሳንጠብቅ መልካም የሆኑ ነገሮችን ማከናወን እንችል ዘንድ የሚያግዘንን ይህ የኢየሱስ ቃል ልባችንን ይነካው ዘንድ፣ የፍቅርን አሸናፊነት በሁሉም ቦታዎች መመስከር እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
24 February 2019, 15:49