ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብሰባው መካከል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብሰባው መካከል  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሴቶች የእናት ቤተክርስቲያን ተምሳሌቶች ናቸው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተካፋዮች እንደተናገሩት፣ በቤተክርስቲያን ላይ የወጣውን ቁስል እና የሚሰማትን ሕመም ሴቶች እንዲገልጹት ሲደረግ በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሴቶች ትልቅ የሃላፊነት ሥፍራን መስጠት ብቻ ሳይሆን ሴት የእናት ቤተክርስቲያን ተምሳሌት መሆኗን ያስገነዝባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ከተማ ከየካቲት 14 ቀን ጀምሮ በቤተክርስቲያን ውስጥ በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ መንገዶችን ለማጠናከር የታሰበ የብጹዓን ጳጳሳት ስብሰባ በመካሄድ ላይ መሆኑን በሰሞኑ ዜናችን መግለጻችን ይታወሳል። እስከ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ የሚቆየውን ስብሰባ በመከታተል ላይ የሚገኙ ከመላው ዓለም የተገኙት ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤዎች ሊቃነ መናብርት እና ተወካዮቻቸው፣ ምሁራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መሆናቸው ታውቋል። በትናንት የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ. ም. በተቀመጠው የከሰዓት በኋላ ስብሰባ ላይ የተገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከእርሳቸው አስቀድሞ ንግግር ያደረጉትን፣ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ ያሰሙትን ንግግር ካዳመጡ በኋላ ለስብሰባው ተካፋዮች እንደተናገሩት፣ በቤተክርስቲያን ላይ የወጣውን ቁስል እና የሚሰማትን ሕመም ሴቶች እንዲገልጹት ሲደረግ በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሴቶች ትልቅ የሃላፊነት ሥፍራን መስጠት ብቻ ሳይሆን ሴት የእናት ቤተክርስቲያን ተምሳሌት መሆኗን ያስገነዝባል ብለዋል።

የወይዘሮ ሊንዳ ጊሾንን ንግግር ካዳመጡ ባሰሙት ንግግር፣ የሚሰማትን ሕመም ቤተክርስቲያን ራሷ ገልጻለች ያሉት ቅዱስነታቸው አሁን በመካሄድ ላይ ባለው ስብሰባ ስለ ሴቶች ብንወያይ የስብሰባችንን ዓላማ ሊያሰፋው ይችላል ብለው፣ ቤተክርስቲያን የደረሰባትን ችግር እና የሚሰማትን ሕመም ሴቶች በአንደበታቸው እንዲገልጹት ሴቶች ሲጋበዙ ይህ ማለት የደረሰባትን ችግር እና የሚሰማትን ሕመም እናታችን የሆነች ቤተክርስቲያን ራሷ እንድትገልጸው እንጋብዛለን ብለዋል።   

ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ እንደ ምሳሌ የተጠቀሱትም የልጆች እናት በመሆናቸው፣ በወሊድ ጊዜ ያጋጠማቸውን ሕመም በሚገባ ስለሚያውቁት ነው ተብሏል። ከዚህም በላይ ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራነት እና የእናትነት ምስጢር የሚገለጥባት በመሆኑ ነው ተብሏል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት የስብሰባውን ተካፋዮች በሙሉ አመስግነው፣ ከስብሰባው መካከል ለሚቀርቡት የምስክርነት ቃሎች በሙሉ በድጋሚ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።   

23 February 2019, 16:45