ፈልግ

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የአረብ ኤምሬቶች ሐዋርያዊ ጉብኝት ዝግጅት የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የአረብ ኤምሬቶች ሐዋርያዊ ጉብኝት ዝግጅት 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ታሪካዊ እንደሚሆን ተገለጸ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በሱኒ እስልምና ሐይማኖት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሳድግ፣ ሰላማዊና የእርስ በእርስ መከባበርን የሚያጎለብት ይሆናል ተብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የአገር ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው ዘገባ መሠረት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት እንደመሆኑ ታሪካዊና መልካም ጅምር እንደሚሆን ሚኒስቴሩ ገልጿል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእሑድ ጥር 26 – 28፣ 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከረጅም ዘመናት ጀምሮ ይዞ የቆየውን የአንድነት እና የአብሮ መኖርን ባሕል ያረጋግጣል ብሏል።

የአገር ሚኒስቴሩ በማከልም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተመሠረተው የክርስትናንና የሌሎችንም እምነቶች መብትና ነጻነት ለማስጠበቅ፣ ህገ መንግስቱውም በሐይማኖቶች መካከል ሊከሰቱ የሚችሉትን አድልዎ በማስወገድ፣ የእምነት ነጻነትንም የሚያከብር መሆኑን ገልጿል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በሚያደርጉባት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አብዛኛው ሕዝብ የእስልምና እምነት ተከታይ ይሁን እንጂ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ክርስቲያኖችም መገኘታቸው ታውቋል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከአርባ በላይ ቤተክርስቲያኖች በጎናቸው ከታነጹት መስጊዶች፣ የሂንዱ፣ የሲክ እና የቡዳ የአምልኮ ስፍራዎች ጋር በሰላም እና በጋራ የሚኖሩባት አገር መሆኗን የሃገር ሚኒስቴሩ ገልጿል። በማከልም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሥራ ብለው ከ200 በላይ አገሮች የመጡ ዜጎች የሚኖሩባት አገር መሆኗን፣ እነዚህ የተለያዩ ዜጎች እምነታቸውን በነጻነት መግልጽ የሚችሉበትን መብት ያረጋገጠችላቸው አገር መሆኗን ገልጿል። አገሪቱ ለሰው ልጅ በሙሉ የምትሰጠው ቸርነት የተሞላበት ተግባር የሃገሪቱ ባሕላዊ እሴቶች የተገለጹበት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መስራች የሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን ኣል ናያን መሠረታዊ ዓላማ መሆኑን የአገር ሚኒስቴሩ ገልጿል። የሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን ኣል ናያን ራዕይ አገራቸው ከአዋሳኝ አገሮች ጋር ከምታደርገው ሰፊ የባሕል ትስስር በተጨማሪ ለተቀረው ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል በማሰብ መሆኑን አስረድቷል። ይህ በጎ አላማ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዛሬ ለምትከተለው ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች  መንገድ የከፈተ እና ከተለያዩ መንግሥታት ጋር ተከባብሮ የመኖርን መንገድ ያመቻቸ ነው ብሏል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የክርስትና እምነት ከረጅም ዘመናት ጀምሮ የነበረበት መሆኑን በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በሲር ባኒ ያስ ደሴት ላይ የታነጹት ገዳማት እንደሚመሰክሩ የተገለጸ ሲሆን ይህም ሼክ ዛይድ ገዳማቱ በወጉ ተጠብቀው እንዲቆዩ እና በእምነቶች መካከል ያለው መንፈሳዊ ትስስር ቀጣይነት እንዲኖረው በማለት ያቆዩት እንደሆነ የሃገር ሚኒስቴር ገልጿል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከቅድስት መንበር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን የጀመረው በጎርጎሮሳዊው 2007 ዓ. ም. ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ታውቋል። ለመልካም ግንኙነታቸው ተጠቃሽ የሆነው በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ. ም. በአቡ ዳቢ ልዑል እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የጦር ኃይል ምክትል አዛዥ በሆኑት በሼክ መሓመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን የተደረገው ጉብኝት እንደሆነ ታውቋል። ቀጥሎም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተጠሪ የሆኑት  ልዑል ሼክ ኣብዱላህ ቢን ዛይድ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አረብ ኤምሬቶች ታሪካዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ በማለት የግብዣ መልዕክት ማቅረባቸው ይታወሳል።

   

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእሑድ ጥር 26 – 28፣ 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚያደርጉት ታሪካዊ ጉብኝታቸው ወቅት በአገሩ ለሚገኙት ካቶሊካዊ ምዕመናን መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያሳርጉ፣ የአል ዛር ከፍተኛ ኢማም እና የአገሩ የእስልምና አባቶች ምክር ቤት ሊቀ መንበር ከሆኑት ከሺክ አህመድ አል ጣይብ ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለቱን የሐይማኖት መሪዎችን ማለትም የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና የሱኒ እስልምና ሐይማኖት መንፈሳዊ መሪዎች እንዲገንኙ የሚያደርግ በመሆኑ ሁለቱ እምነቶች በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት የሚያሳድግ፣ ሰላማዊና የእርስ በእርስ መከባበርን የሚያጎለብት ኣንደሚሆን ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
01 February 2019, 16:33