ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአቡ ዳቢ ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአቡ ዳቢ ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች እና ተወካዮች ያደረጉት ንግግር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥር 26 – 28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ፣ 27ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መሄዳቸው ታውቋል። እሁድ ጥር 26 ቀን 2011 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ወደ አቡዳቢ ከተማ ሲደርሱ ልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ሆነው አቀባበል አድርገውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት፣ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በሆነችው በአቡ ዳቢ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የሐይማኖት መሪዎች ስብሰባንም መካፈላቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በሰብሰባው ለተገኙት፣ የሲቪል ማሕበረሰብ ተወካዮች፣ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች እና ከፍተኛ ባለ ስልጣናት በተገኙበት የሚከተለውን ንግግር አድረገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን፣

ለልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን እና የኣል ኣዛር ታላቁ ኢማም ለሆኑት ለዶ/ር አህመድ ኣል ጣይብ ለደረጉት ንግግራቸው ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ከታላቁ የሼክ ዛይድ መስጊድ የአባቶች ምክር ቤት ጋር ስላደረገነው ስብሰባም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ከሲቪል ማህበረሰብ ከዲፕሎማት አካላትና እና ከሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ለተደረገልን መልካም አቀባበል  ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ከዚህም በተጨማሪ ለጉዞዬ መሳካት እና ይህን የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ስብሰባ ዝግጅት መሳካት ብቃት ያለውን ጥረት በማድረግ አስተዋጽዖን ላበረከቱት የስብሰባው አዘጋጅ ኮሚቴዎች፣ የፕሮቶኮል ቢሮ አባላት፣ የደህንነት ሠራተኞች እና በተለያዩ መንገዶች አስተዋጽኦን ላደረጉት በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በተጨማሪም የታላቁ ኢማም የቀድሞ አማካሪ የሆኑትን አቶ መሐመድ አብደል ሳላምን አመሰግናለሁ። ለመላው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሕዝብ እና ለባሕረ ሰላጤው አገሮችም በሙሉ ልባዊ የወዳጅነት ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

የአሲስው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የግብጹ ሱልጣን አል-ማሊክ አል ካሚል የተገናኙበትን 800ኛ ዓመት መታሰቢያ በጠራው ስብሰባ ላይ እንድንገናኝ ላበቃን እግዚአብሔር ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ የሆንኩበት ምክንያት እንደ አንድ አማኝ ሰላምን በመጠማት፣ በወንድሞች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ስለ ፈለግሁ ነው። እኛ ሁላችን እዚህ የተገኘንበት ዋና ዓላማ ለሰላም ካለን ፍላጎት፣ ሰላምን ለማራመድ እና የሰላም መሣሪያም ለመሆን ነው።

ለዚህ ጉዞ ምልክት እንዲሆን ተብሎ የተዘጋጀው አርማ የወይራ ቅጠልን ባነገበች እርግብ ሲሆን ይህም በተለያዩ ሐይማኖታዊ ባሕሎች የሚጠቀሰውን የጥፋት ውሃን ታሪክ የሚያስታውስ ነው። በክርስትና እምነቶች ዘንድ እንደሚታወቀው እግዚአብሔር የሰው ዘር ከጥፋት ውሃ እንዲተርፍ ኖሕ ቤተሰቡን ወደ መርከብ ይዞ እንዲገባ ማዘዙን የሚያስታውስ ነው። እኛም ዛሬ ሰላምን ለማስከበር የአንድ ቤተሰብ አባላት በመሆን ወደ ወንድማማችነት መርከብ መግባት ይኖርብናል።

የጋራ ጉዞ መነሻችን፣  ለሰው ልጆች ቤተሰባዊ አንድነት ብቸኛ መሠረቱ እግዚአብሔር መሆኑን ስንገነዘብ ነው። እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ በመሆኑ በወንድማማችነት እና እህታማማችነት መንፈስ፣ በጋራ የምንኖርበትን ስፍራ አዘጋጅቶልናል። ይህ የወንድማማችነት መንፈስ የተመሠረተው እንደ እግዚአብሔር እቅድ አንዱ በሌላው ላይ በላይነትን በመቀዳጀት ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው እኩል ሰብዓዊ ክብርን በማግኘት ነው።

ለሰው ልጅ በሙሉ ፍቅርን የማንሰጥ ከሆነ ለፈጣሪው ክብርን መስጠት አንችልም።

እያንዳንዱ ሰው በእግዚ አብሔር ዓይን እኩል ዋጋ ያለው ነው። እግዚአብሔር በሰዎች መካከል ልዩነትን አያደርግም። ሁሉን  በእኩል የፍቅር ዓይን ይመለከታል። በመሆኑም ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ እኩል መብት መስጠት ማለት የእግዚአብሔር ስም በምድር ላይ እንዲመሰገን ማድረግ ነው።  የፍጥረታት ፈጣሪ በሆነው በእግዚአብሔር ስም ማንኛውም ዓይነት አመጽ መወገዝ አለንበት እንጂ በእግዚአብሔር ስም በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ላይ የሚፈጸም ጥላቻ እና አመጽ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። በሐይማኖት ስም የሚፈጸም አመጽ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።

የአንድነት ትልቁ ጠንቅ ራስን ብቻ መመልከት፣ ራስን ከሌሎች ነጥሎ ወገናዊ በመሆን ወገኑ ለሆኑት ብቻ እውቅና እና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ይህ አደጋ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ውስጥ ዘልቆ በመግባት በሃይማኖቶች ውስጥም ሲንጸባረቅ ይታያል። እውነተኛ ሃይማኖታዊ አካሄድ እግዚአብሔርን በሙሉ ልብ መውደድን፣ ጎረቤትንም እንደ ራስ መውደድን ያጠቃልላል። ስለዚህ ትክክለኛው የሐይማኖት አካሄድ ከተለያዩ ፈተናዎች በመራቅ ሌሎችን እንደ ጠላት ከማየት መቆጠብን ይጠይቃል። እያንዳንዱ የእምነት ሥርዓት ወዳጅ እና ጠላት ሳይል ሰዎችን በሙሉ ያለ ልዩነት የሚመለከት ነው።

ይህ አገር የሰዎችን የአምልኮ ነጻነት ለማስከበር፣ በእምነቶች መካከል መቻቻል እንዲኖር በማድረግ   የጠላትነት ስሜትን ለማስቀረት ስላደረገው ጥረት አድናቆቴን መግለጽ እፈልጋለሁ። ሰዎች እምነታቸውን የሚገልጹበት መሠረታዊ መብታቸውም እንዲከበር ተደርጓል። ይህ ነጻነት ደግሞ የሰው ልጅ እራሱን እንዲያውቅ የሚያስችል መሠረታዊ ፍላጎት ሆኖ አገልግሏል። ስለዚህ ሐይማኖት የቆመለትን ዓላማ ዘንግቶ የአመጽ እና የሽብር መሣሪያ እንዳይሆን መከላከል ያስፈልጋል።

ወንድማማችነት በትውልድም ሆነ በተፈጥሮአዊ መንገድ በወንድሞች እና በእህቶች መካከል ያሉትን ልዩነቶችን ሰብስቦ የያዘ ነው። የሃይማኖት ብዝሃነትም የዚህ ነጸብራቅ ነው። ከዚህ ባሕርይ ጋር ተያይዞ  ሐይማኖቶች በግድ አንድ እንዲሆኑ ወይም ለሙሉ አንድነት መፍትሄዎችን የሚፈልጉ መሆን አይጠበቅባቸውም። ነገር ግን እንደ አማኞች ማድረግ ያለብን በሰዎች መካከል እውነተኛ እኩልነት እንዲመጣ፣ የምሕረት አምላክ በሆነው በአንድ እግዚአብሔር ስም በግጭቶች መካከል እርቅ፣ በልዩነቶች መካከልም ወንድማማችነት እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልጋል። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረን በሙሉ በወንድምነት ዓይን ሳትመለከት ቀርታ፣ እግዚአብሔርን የሁሉ አባት ብላ መጥራት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት አለመሆኑን እንደገና  ማረጋግጥ እፈልጋለሁ።

የአንድ ቤተሰብ አባል ነን ካልን አንዱ ሌላውን እንዴት መመልከት እና እርስ በእርስ መተባበር እንችላለን የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በመካከላችን የሚገኘውን እውነተኛ ወንድማማችነት እንዴት አድርገን በተግባር እንዲገለጽ ማድረግ እንችላለን? የራሱ ወገን ያልሆነውን ከራስ ወገን ጋር ሕብረት እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? በሌላ አገላለጽ የተለያዩ ሐይማኖቶች የልዩነት ምክንያት መሆናቸው ቀርቶ የአንድነት እና የፍቅር መገለጫ ሊሆኑ እንዴት ይችላሉ?   

ሰብዓዊ ቤተሰብ እና ሌላነት ለመሆን ያለን ድፍረት፣

ሰብዓዊ ቤተሰብ እንዳለ የምናምን ከሆነ ይህ ቤተሰብ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው እንገነዘባለን። በእያንዳንዱ ቤተሰብ እንደሚታይ ሁሉ በቤተሰብ መካከል ውጤታማ የሆነ ዕለታዊ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ የራስን ማንነት ብቻ ማስከበር ሳይሆን የሌላውንም ወገን መልካም ጎን መግለጽን ይጠይቃል። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ የሌላ ወገን አባል መሆን ድፍረትን ይጠይቃል። የሌላ ወገን አባል ከሆኑ የዚያ ወገን መሠረታዊ ነጻነት በየትም ስፍራ እና በማንም ዘንድ እንዲከበር የግል ጥረትን ማድረግ ያስፈልጋል። ነጻነት ከሌለን የሰብዓዊ ቤተሰብ አባል ሳንሆን ባሪያዎች እንሆናለን። ከዚህ ነጻነት ጋር በማያያዝ በሐይማኖት ነጻነት ላይ ትኩረት ማድረግ እፈልጋለሁ። የሐይማኖት ነጻነት በምንልበት ጊዜ የአምልኮ ነጻነትን ሳይሆን ማንም ሰብዓዊ ተቋም የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት ሊነጥቀው የማይችለው እና እግዚአብሔር ራሱ ለእያንዳንዱ ወንድም እና እህት እንዲሁም የእኔ ያስቀመጠውን ነጻነት ማለታችን ነው።     

የጋራ ውይይት እና የጸሎት አስፈላጊነት፣

የሌላ ወገን አባል መሆን በእውነተኛ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እና ግልጽ የሆነ የጋራ ውይይቶችን ለማድረግ ያስችላል። እውነተኛ ውይይት ልዩነትንና ጥርጣሬ ያስወግዳል። በአንድ ወገን ስለ ወንድማማችነትን ለማሳደግ እየጣርን በሌላ ወገን ጥላቻን ማራመድ አንችልም። አንድ የዘመኑ ደራሲ እንደተናገሩት፣ ለራሱ የሚዋሽ እና የራሱን ውሸት የሚያዳምጥ ሰው በራሱ እና በአካባቢው ያለውን እውነት ለይቶ ማወቅ ይቸገራል። በመሆኑም ለራሱ የሚሰጠውን እና ከሌሎች የሚያገኘውን ክብር ያጣል።

ይህ ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ ጸሎት እጅግ አስፈላጊ መሣሪያ ነው። በንጹሕ ልብ የሚደረግ ከሆነ የሌላ ወገን አባል ከማድረግ በተጨማሪ ልባችን ንጹሕ እንዲሆን ያደርጋል። እውነተኛ ልባዊ ጸሎት የወንድማማችነት ፍቅር እንዲያድግ ያግዛል። በሐይማኖቶች መካከል ለምናደርጋቸው የወደ ፊት ውይይቶች ጸሎት ቅድሚያ ሊሰጠው እና በተጨማሪም ወንድሞችን እህቶች በመሆናችን አንዳችን ለሌላው መጸለይ ያስፈልጋል። ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሊሆን የሚችል ነገር የለም፣ በእርሱ በኩል ሁሉ ነገር ሊከናወን ይችላል። እያንዳንዱ ሐይማኖት የእምነት ባሕሉን በመከተል፣ እንደ እግዚአብሔር እቅድ መሠረት፣ በሐይማኖት  የተለያየን ቢሆንም አንድ የሚያደርገንን የእግዚአብሔር ፈቃድ ተግባራዊ ለማድረግ መጸለይ ያስፈልጋል።

የወደ ፊት ዕጣ ፈንታችንን መልካም እንዲሆን ለማድረግ በጋራ ከመሥራት ይልቅ ሌላ አማራጭ የለንም። በተለይም ሐይማኖቶች በሕዝቦች እና በባሕሎች መካከል ግንኙነትን ለመፍጠር ድልድይ የመገንባት አስቸኳይ ስራን ወደ ጎን ሊሉ አይገባም። ሰብዓዊ ቤተሰብ እርቅን ለማምጣት የሚያስችል ችሎታን እንዲጠቀሙ፣ ለእርቅ ያላቸውን ተስፋ በመሰነቅ የሰላም ጎዳናን እንዲጓዝ ለማድረግ ሃይማኖቶች ከምን ጊዜም በበለጠ በንቃት እና በድፍረት መነሳሳት አለባቸው።  

ትምህርት እና ፍትህ ይኑር፣

የሰላም እርግብን እንመልከት። ሰላም ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ እንዲበር በትምህርት የሚገኝ የዕውቀትና የፍትህ ክንፎች እንዲኖረው ያስፈልጋል።

ትምህርት የሚለው ቃል በላቲን ቋንቋ ሲገለጽ ማመንጨትን ወይም ጎልቶ እንዲታይ የሚለውን ሐሳብ ይገልጻል። ይህ ማለት ትምህርት ውድ የሆኑ የሕይወት ልምዶች ወይም እውቀቶች ተገልጸው እንዲታዩ ያደርጋል። እንደምንመልከተው በዚህ አገር የተከናወኑ የልማት ውጤቶች ከተፈጥሮ ሃብት ብቻ ሳይሆን ወጣቶች የቀሰሙት እውቀት በተግባር ተገልጾ በመታየቱ ነው። ይህን የመሰለ ጥረት በሌሎችም አካባቢዎች በተግባር ተገልጾ እንደሚታይ ተስፋ አደርጋለሁ። ትምህርት ሰዎች በመካከላቸው በሚያደርጉት ግንኝነቶች የሚመጣ ነው። እንደ ጥንታዊ አባባል፣ “ራስህን እወቅ” ሲባል “ወንድምህን እና እህትህን እወቅ” የሚለውን መልዕክት የሚያስተጋባ ሲሆን ወንድምህን እና እህትህን ማወቅ ደግሞ ታሪካቸውን ባሕላቸውን እና እምነታቸውን ማወቅ ማለት ነው። ስለ ሌሎች ካላወቅን በስተቀር ስለ ራሳችን ትክክለኛ የሆነ ዕውቀት ሊኖረን አይችልም። ሰው እንደ መሆናችን ከዚህም በበለጠ ወንድሞች እና እህቶች እንደመሆናችን መጠን ልንገነዘበው የሚገባን ነገር ቢኖር የሰዎች የሆነ ሁሉ እንግዳ ሊሆንብን እንደማይችል ማስታወስ ያስፈልጋል። ወደ ግለኝነት አዝማሚያ የሚወስደን ፈተና እንዳያጋጥመን ግልጽ የሆነ ማንነትን ማሳደግ አስፈላጊ ነው።

ባሕልን ማሳደግ በሰዎች መካከል የሚፈጠር ጥላቻን በመቀነስ ሰብዓዊነትን እና ብልጽግናን ለማምጣት ያግዛል። ትምህርት እና አመጽ በተቃርኖ የተመጣጠኑ ናቸው። የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች በዚህች አገር እና በአካባቢው አገሮች ይወደሳል። በአመጽ ፈንታ ሰላምን ለማንገስ ይዚህን ዓይነት ትምህርት ማስፋፋት ያስፈልጋል።

በብዙ መልኩ አሉታዊ መልዕክቶች እና ውሸት ዜናዎች የሚደርሷቸው ወጣቶች በእነዚህ ቁሳዊ ኣና ጥላቻን በሚያስነሱ መልዕክቶች ሊታለሉ አይገባም። ስለ ፍትህ ምንነት በሚገባ ሊያውቁ እንዲሁም ስላለፉት መጥፎ ታሪኮች ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። ስለ ራሳቸው መብት እንደሚጨነቁ ሁሉ ስለ ሌሎችም መብት መጨነቅ ይኖርባቸዋል። ዛሬ በዚህ የወጣትነት እድሜአቸው በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆሙ የማናደርጋቸው ከሆነ ወደ ፊት በእኛ ላይ የሚፈርዱ ይሆናል። በአስጨናቂ አመጽ ውስጥ ያለ ምንም እውቀት የምንተዋቸው ከሆነ መጥፎ ፍርድ ሊፈርዱብን ይችላሉ።

ፍትህ፣ ሰላምን ወደ ዓለም ዳርቻ ለማዳረስ የሚያግዝ ሁለተኛው ክንፍ ሲሆን እና በተግባር ላይ ካልዋለ ቀስ በቀስ ሊጠፋ ይችላል። በመሆኑም ማንም ቢሆን በእግዚአብሔር እየኖረ ነገር ግን ያለ ፍትህ ሊኖር አይችልም።  “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና”። (ማቴ. 7.12)

ሰላም እና ፍትህ የሚለያዩ አይደሉም። ነብዩ ኢሳይያስ እንደሚለው “የጽድቅም ሥራ ሰላም፥ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል”። (ኢሳ. 32.17) ሰላም ከፍትህ የራቀ ከሆነ ይሞታል፣ ነገር ግን ፍትህ ዓለም አቀፍ ካልሆነ ውሸት ሆኖ ይቀራል። ፍትህ በአንድ ቤተሰብ አባላት መካከል ብቻ ወይም በጎረቤቶቻቸው ዘንድ ብቻ የሚገለጽ ከሆበ ወይም ተመሳሳይ እምነት ባለቸው ሰዎች መካከል ብቻ የሚገለጽ ከሆነ ይህ ፍትህ የቀለለ እና በራሱም የተሳሳተ ፍትህ ሆኖ ይቀራል።

የዓለም ሐይማኖቶች ለትርፍ ብቻ ተስገብግቦ መሮጥ ልብን ያለ ፍቅር እንደሚያስቀር፣ የዓለም የገበያ ሕጎች በመካከላቸው የግንኙነትን መስመር ሳያመቻቹ ሁሉን ነገር በፍጥነት እንዲከናወን በማድረግ፣ በተረጋጋ መንፈስ  በቤተስብ መካከል መደረግ ያለበትን ውይይት ተግባራዊ እንዳይሆን ያደርጋል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሐይማኖት ድምጽ ለሌላቸው ደሃ ለሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ድምጽ ሆኖ ማገልገል ይኖርበታል። በተጨማሪም በሰዎች መካከል ያለው ወንድማማችነት እንዳይጨልም፣ በሰዎች ላይ ለሚፈጸም ሕገ ወጥ ድርጊት ማስጠንቀቂያን በመስጠት እና በዝምታ እንዳይታለፍ በማድረግ፣ በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ የሚደርሱ በርካታ ስቃዮችን ላለማየት ብለው ፊታቸውን ማዞር እንደሌለባቸው ማወቅ ያስፈልጋል።

በመለምለም ላይ ያለ በረሃ፣

ወንድማማችነትን ልክ እንደ ሰላም መርከብ አድርጌ ከተናገርኩ በኋላ አሁን ደግሞ ተመስጦዬን በወሰደው ሁለተኛው ምስል እና በዙሪያችን ከብቦን ስለሚገኘው በረሃ መናገር እፈልጋለሁ። በአጭር ዓመታት ውስጥ በረሃማው ስፍራ፣ በጥበብ በመታገዝ ወደ ብልጽግና እና እንግዶች የሚስተናገዱበት ምቹ ቦታነት ተቀይሮ እንመለከታለን። ለመድረስም አስቸጋሪ እና እንቅፋት ከበዛበት የበርሃማነት ስፍራ ተለውጦ ዛሬ የተለያዩ ሐይማኖቶትች እና ባሕሎች የሚገናኙበት ስፍራ ሆኗል። የዚህ አካባቢ በረሃ የለማው በዓመታት ውስጥ ለተወሰኑት ቀናት ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥሉ ዓመታትም ጭምር ነው። የአገሩ አሸዋማው መሬት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች እንዲገነቡ በማገዝ፣ የምዕራቡ እና የምስራቁ፣ የሰሜኑ እና የደቡቡ ዓለም መገናኘትን የቀጠሉበት፣ ለኑሮ ምቹ ያልነበረ አካባቢ ዛሬ ለበርካታ የተለያዩ ዜጎች የሥራ ዕድልን በመክፈት የዕድገት ስፍራ ሆኗል።

በወንድማማችነት መንፈስ በሚመሠረት የጋራ ሕይወት ውስጥ ብቸኝነት እና ስግብግብነት እንዳለ ሁሉ እድገትም በበኩሉ ጠላት እንዳለው የሚታወቅ ሲሆን የተደረሰበትን እድገት ወደ መልሶ ወደ በርሃማነት ሊቀይሩ የሚችሉ እንቅፋቶችን መጥቀስ እፈልጋለሁ። ሙሉ በሙሉ የሰዎችን መብት የሚገድብ የፖለቲካ ሥርዓት እውነተኛና ዘላቂ እድገትን ሊያመጣ አይችልም። ሁለ ገብ ማሕበራዊ ሕይወትን ያገናዘበ ልማት ብቻ ለሰው ልጅ ተስማሚ ይሆናል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከሰዎች ይልቅ ሠርተው በሚያገኙት ገብ ትኩረት የሚያደርግ፣ ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ይልቅ በሚያበረክቱት ሥራ ብቻ ትኩርተን የሚያደርግ ሥርዓት ለእድገት ተስማሚ አይደለም። በእነዚህ መካከል ልዩነትን የሚያደርግ ሥርዓት ሰብዓዊ ክብርን፣ ስለ ወደፊት ማሕበራዊ ሕይወት እና ስለ ሕጻናት የወደ ፊት ዕድል የሚጨነቅ አይደለም።

ይህን በተመለከተ ባለፈው ሕዳር ወር “የሕጻናት ክብር በዲጂታሉ ዓለም” በተሰኘ ርዕስ ላይ በአቡ ዳቢ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የተለያዩ ሐይማኖቶች የጋራ ጉባኤ የተደሰትኩበት ሲሆን ይህ ጉባኤ ከመካሄዱ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ በሮም ከተማ ለተካሄደው ተመሳሳይ ጉባኤ ሙሉ ድጋፌን መስጠቴ ይታወሳል። በዚህ ርዕስ ዙሪያ ለተሳተፉት መሪዎች በሙሉ ምስጋናዬን እያቀርብኩ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስም ሙሉ ድጋፌን እና አጋርነቴን መግለጽ እወዳለሁ”።

04 February 2019, 19:46