ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለዓለም የእምነት ተቋማት መሪዎች እና ተወካዮች ንግግር አደረጉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥር 26 – 28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ፣ 27ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መሄዳቸው ታውቋል። እሁድ ጥር 26 ቀን 2011 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ወደ አቡዳቢ ከተማ ሲደርሱ ልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ሆነው አቀባበል አድርገውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት፣ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በሆነችው በአቡ ዳቢ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የሐይማኖት መሪዎች ስብሰባንም መካፈላቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በሰብሰባው ለተገኙት፣ የሲቪል ማሕበረሰብ ተወካዮች፣ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች እና ከፍተኛ ባለ ስልጣናት በተገኙበት የሚከተለውን ንግግር አድረገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

ለልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን እና የኣል ኣዛር ታላቁ ኢማም ለሆኑት ለዶ/ር አህመድ ኣል ጣይብ ላደረጉት ንግግር ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ከታላቁ የሼክ ዛይድ መስጊድ የአባቶች ምክር ቤት ጋር ስላደረገነው ስብሰባም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ከሲቪል ማህበረሰብ፣ ከዲፕሎማት አካላትና እና ከሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ለተደረገልን መልካም አቀባበል  ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ለጉዞዬ መሳካት እና ይህን የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ስብሰባ ዝግጅት መሳካት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ አስተዋጽዖን ላበረከቱት የስብሰባው አዘጋጅ ኮሚቴዎች፣ የፕሮቶኮል ቢሮ፣ የደህንነት ተቋማት እና በተለያዩ መንገዶች አስተዋጽኦን ላደረጉት በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በተጨማሪም የታላቁ ኢማም የቀድሞ አማካሪ የሆኑትን አቶ መሐመድ አብደል ሳላምን አመሰግናለሁ። ለመላው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሕዝብ እና ለባሕረ ሰላጤው አገሮችም በሙሉ ልባዊ የወዳጅነት ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የግብጹ ሱልጣን አል-ማሊክ አል ካሚል የተገናኙበትን 800ኛ ዓመት መታሰቢያ ስብሰባ ላይ እንድንገናኝ ላበቃን እግዚአብሔር ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ የሆንኩበት ምክንያት እንደ አንድ አማኝ ሰላምን በመጠማት፣ በወንድሞች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ስለ ፈለግሁ ነው። እኛ ሁላችን እዚህ የተገኘንበት ዋና ዓላማ ለሰላም ካለን ፍላጎት፣ ሰላምን ለማራመድ እና የሰላም መሣሪያ ለመሆን ነው።

ለሐዋርያዊ ጉብኝቴ አርማ የወይራ ቅጠልን ባነገበች እርግብ የተሳለ ሲሆን ይህም በተለያዩ ሐይማኖታዊ ባሕሎች የሚጠቀሰውን የጥፋት ውሃን ታሪክ የሚያስታውስ ነው። በክርስትና እምነቶች ዘንድ እንደሚታወቀው እግዚአብሔር የሰው ዘር ከጥፋት ውሃ እንዲተርፍ ኖሕ ቤተሰቡን ወደ መርከብ ይዞ እንዲገባ ማዘዙን የሚያስታውስ ነው። እኛም ዛሬ ሰላምን ለማስከበር የአንድ ቤተሰብ አባላት በመሆን በወንድማማችነት መንፈስ በአንድ መርከብ ውስጥ መሳፈር ይኖርብናል።

የጋራ ጉዞ መነሻችን፣ ለሰው ልጆች ቤተሰባዊ አንድነት ብቸኛ መሠረቱ እግዚአብሔር መሆኑን ስንገነዘብ ነው። እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ በመሆኑ በወንድማማችነት እና እህታማማችነት መንፈስ፣ በጋራ የምንኖርበትን ስፍራ አዘጋጅቶልናል። ይህ የወንድማማችነት መንፈስ የተመሠረተው እንደ እግዚአብሔር እቅድ፣ አንዱ በሌላው ላይ የላይነትን በመቀዳጀት ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው እኩል ሰብዓዊ ክብርን በማግኘት ነው።

ለሰው ልጅ በሙሉ ፍቅርን የማንሰጥ ከሆነ ለፈጣሪው ክብርን መስጠት አንችልም።

እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር ዓይን እኩል ነው። እግዚአብሔር በሰዎች መካከል ልዩነትን አያደርግም። ሁሉን በእኩል የፍቅር ዓይን ይመለከታል። በመሆኑም ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ እኩል መብት መስጠት ማለት የእግዚአብሔር ስም በምድር ላይ እንዲመሰገን ማድረግ ነው።  የፍጥረታት ፈጣሪ በሆነው በእግዚአብሔር ስም ማንኛውም ዓይነት አመጽ መወገዝ ይኖርበታል እንጂ በእግዚአብሔር ስም በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ላይ የሚፈጸም ጥላቻ እና አመጽ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። በሐይማኖት ስም የሚፈጸም ማንኛውም አመጽ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።

የአንድነት ትልቁ ጠንቅ ራስን ብቻ ለይቶ መመልከት፣ ራስን ከሌሎች ነጥሎ ወገኑ ለሆኑት ብቻ እውቅና እና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ይህ አደጋ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ውስጥ ዘልቆ በመግባት፣ በሃይማኖቶች ውስጥም ሲንጸባረቅ ይታያል። እውነተኛ ሃይማኖታዊ አካሄድ እግዚአብሔርን በሙሉ ልብ መውደድን፣ ጎረቤትንም እንደ ራስ መውደድን ያጠቃልላል። ስለዚህ ትክክለኛው የሐይማኖት አካሄድ ከተለያዩ ፈተናዎች በመራቅ ሌሎችን እንደ ጠላት ከማየት መቆጠብን ይጠይቃል። እያንዳንዱ የእምነት ሥርዓት፣ ወዳጅ እና ጠላት ሳይል ሰዎችን በሙሉ ያለ ልዩነት የሚመለከት ነው።

ይህ አገር የሰዎችን የአምልኮ ነጻነት ለማስከበር፣ በእምነቶች መካከል መቻቻል እንዲኖር በማድረግ፣   የጠላትነትን ስሜት ለማስቀረት ስላደረገው ጥረት አድናቆቴን መግለጽ እፈልጋለሁ። ሰዎች በዚህ አገር  እምነታቸውን በነጻነት የሚገልጹበት መሠረታዊ መብታቸውም እንዲከበር ተደርጓል። ይህ ነጻነት ደግሞ የሰው ልጅ እራሱን እንዲያውቅ የሚያስችል መሠረታዊ ፍላጎት ሆኖ አገልግሏል። ስለዚህ ሐይማኖት የቆመለትን ዓላማ ዘንግቶ የአመጽ እና የሽብር መሣሪያ እንዳይሆን መከላከል ያስፈልጋል።

ወንድማማችነት በትውልድም ሆነ በተፈጥሮአዊ መንገዶች፣ በወንድሞች እና በእህቶች መካከል ያሉትንም ልዩነቶችን ሰብስቦ የያዘ ነው። የሃይማኖት ብዝሃነትም የዚህ ነጸብራቅ ነው። ከዚህ ባሕርይ ጋር ተያይዞ  ሐይማኖቶች በግድ አንድ እንዲሆኑ ወይም ሙሉ በሙሉ አንድ የሚያደርጋቸውን የመፍትሄ መንገዶችን የሚፈልጉ መሆን አይጠበቅባቸውም። ነገር ግን እንደ አማኞች ማድረግ ያለብን በሰዎች መካከል እውነተኛ እኩልነት እንዲመጣ፣ የምሕረት አምላክ በሆነው በአንድ እግዚአብሔር ስም በግጭቶች መካከል እርቅ፣ በልዩነቶች መካከልም ወንድማማችነት እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልጋል። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረን በሙሉ በወንድምነት ዓይን ሳትመለከት ቀርታ፣ እግዚአብሔርን የሁሉ አባት ብላ መጥራት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት አለመሆኑን እንደገና  ማረጋግጥ እፈልጋለሁ።

የአንድ ቤተሰብ አባል ነን ካልን፣ አንዱ ሌላውን እንዴት መመልከት እና እርስ በእርስ እንዴት አድርገን መተባበር እንችላለን? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በመካከላችን የሚገኘውን እውነተኛ ወንድማማችነት እንዴት አድርገን በተግባር መግለጽ እንችላለን? የራሱ ወገን ያልሆነውን ከራስ ወገን ጋር ሕብረት እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? በሌላ አገላለጽ የተለያዩ ሐይማኖቶች ልዩነታቸውን ከማንጸባረቅ ይልቅ የአንድነት እና የፍቅር መገለጫ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?   

ሰብዓዊ ቤተሰብ እና ሌላነት ለመሆን ያለን ድፍረት፣

ሰብዓዊ ቤተሰብ እንዳለ የምናምን ከሆነ ይህ ቤተሰብ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው እንገነዘባለን። በእያንዳንዱ ቤተሰብ እንደሚታየው ሁሉ በቤተሰብ መካከል ውጤታማ የሆነ ዕለታዊ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ የራስን ማንነት ብቻ ማስከበር ሳይሆን የሌላውንም ወገን መልካም ጎን መግለጽን ይጠይቃል። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ የሌላ ወገን አባል መሆን ድፍረትን ይጠይቃል። የሌላ ወገን አባል ከሆኑ የዚያ ወገን መሠረታዊ ነጻነት በየትም ስፍራ እና በማንም ዘንድ እንዲከበር የግል ጥረትን ማድረግ ያስፈልጋል። ነጻነት ከሌለን የሰብዓዊ ቤተሰብ አባል ሳንሆን ባሪያዎች እንሆናለን። ከዚህ ነጻነት ጋር በማያያዝ በሐይማኖት ነጻነት ላይ ትኩረት ማድረግ እፈልጋለሁ። የሐይማኖት ነጻነት በምንልበት ጊዜ የአምልኮ ነጻነትን ሳይሆን ማንም ሰብዓዊ ተቋም የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት ሊነጥቀው የማይችለው እና እግዚአብሔር ራሱ ለእያንዳንዳችን የሰጠንን ነጻነት ማለታችን ነው።     

የጋራ ውይይት እና የጸሎት አስፈላጊነት፣

የሌላ ወገን አባል መሆን በእውነተኛ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እና ግልጽ የሆነ የጋራ ውይይቶችን ለማድረግ ያስችላል። እውነተኛ ውይይት ልዩነትንና ጥርጣሬ ያስወግዳል። በአንድ ወገን ወንድማማችነትን ለማሳደግ እየጣርን በሌላ ወገን ጥላቻን ማራመድ አንችልም። አንድ የዘመናችን ደራሲ እንደተናገሩት “ለራሱ የሚዋሽ እና የራሱን ውሸት የሚያዳምጥ ሰው በራሱ እና በአካባቢው ያለውን እውነት ለይቶ ማወቅ ይቸገራል” ብሏል። ይህን በማድረጉ እርሱ ለራሱ የሚሰጠውን እና ከሌሎች የሚያገኘውን ክብር ያጣል።

ይህ ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ ጸሎት እጅግ አስፈላጊ መሣሪያ ነው። ጸሎት በንጹሕ ልብ የሚደረግ ከሆነ የሌላ ወገን አባል ከማድረግ በተጨማሪ ልባችን ንጹሕ እንዲሆን ያደርጋል። እውነተኛ ልባዊ ጸሎት የወንድማማችነት ፍቅር እንዲያድግ ያግዛል። በሐይማኖቶች መካከል ለምናደርጋቸው የወደ ፊት ውይይቶች ጸሎት ቅድሚያ ሊሰጠው ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ ወንድማማቾ እና እህትማማቾች በመሆናችን አንዳችን ለሌላው መጸለይ ያስፈልጋል። ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሊሆን የሚችል ነገር የለም፣ በእርሱ በኩል ሁሉ ነገር ሊከናወን ይችላል። እያንዳንዱ ሐይማኖት የእምነት ባሕሉን በመከተል፣ እንደ እግዚአብሔር እቅድ መሠረት አንድ የሚያደርገንን የእግዚአብሔር ፈቃድ እና እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ መጸለይ ይኖርብናል።  

የወደ ፊት ዕጣ ፈንታችንን መልካም እንዲሆን ለማድረግ በጋራ ከመሥራት በስተቀር ሌላ አማራጭ የለንም። በተለይም ሐይማኖቶች በሕዝቦች እና በባሕሎች መካከል ግንኙነትን ለመፍጠር ድልድይ የመገንባት ሥራን ወደ ጎን ሊሉ አይገባም። ሰብዓዊ ቤተሰብ እርቅን ለማምጣት የሚያስችል ችሎታን እንዲጠቀሙ፣ ለእርቅ ያላቸውን ተስፋ በመሰነቅ የሰላም ጎዳናን እንዲጓዙ ለማድረግ ሃይማኖቶች ከምን ጊዜም በበለጠ በንቃት እና በድፍረት መነሳሳት አለባቸው።  

ትምህርት እና ፍትህ ይኑር፣

የሰላም እርግብን እንመልከት። ሰላም፣ ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ እንዲበር ለማድረግ በትምህርት የሚገኝ የዕውቀትና የፍትህ ክንፎች እንዲኖረው ያስፈልጋል። ትምህርት የሚለው ቃል በላቲን ቋንቋ ሲገለጽ ማመንጨትን ወይም ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ የሚለውን ሐሳብ ይገልጻል። ይህ ማለት ትምህርት ውድ የሆኑ የሕይወት ልምዶች ወይም እውቀቶች ተገልጸው እንዲታዩ ያደርጋል። እንደምንመልከተው በዚህ አገር የተከናወኑ የልማት ውጤቶች ከተፈጥሮ ሃብት ብቻ ሳይሆን ወጣቶች የቀሰሙትን እውቀት በተግባር ገልጸው በማሳየታቸው ነው። ይህን የመሰለ ጥረት በሌሎች አካባቢዎችም በተግባር ተገልጾ እንደሚታይ ተስፋ አደርጋለሁ። ትምህርት ወይም እውቀት ሰዎች በመካከላቸው በሚያደርጉት ግንኝነቶች የሚመጣ ውጤት ነው። እንደ ጥንታዊ አባባል፣ “ራስህን እወቅ” ሲባል “ወንድምህን እና እህትህን እወቅ” የሚለውን መልዕክት የሚያስተጋባ ሲሆን ወንድምህን እና እህትህን ማወቅ ደግሞ ታሪካቸውን ባሕላቸውን እና እምነታቸውን ማወቅ ማለት ነው። ስለ ሌሎች ካላወቅን ስለ ራሳችን ትክክለኛ የሆነ ዕውቀት ሊኖረን አይችልም። ሰው እንደ መሆናችን መጠን ከዚህም በበለጠ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች እንደመሆናችን መጠን ልንገነዘበው የሚገባን ነገር ቢኖር ለሰው ልጆች ጥቅም ተብሎ የተቀመጠ ሁሉ እንግዳ ነገር ሊሆንብን አያስፈልግም። ወደ ግለኝነት አዝማሚያ የሚወስደን ፈተና እንዳያጋጥመን ግልጽ የሆነ ማንነትን ማሳደግ ያስፈልጋል።  

ባሕልን ማሳደግ በሰዎች መካከል የሚፈጠር ጥላቻን በመቀነስ ሰብዓዊነትን እና ብልጽግናን ለማምጣት ያግዛል። ትምህርት እና አመጽ በተቃርኖ የተመጣጠኑ ናቸው። የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች በዚህች አገር እና በአካባቢው አገሮች ዘንድ ይወደሳል። በአመጽ ፈንታ ሰላምን ለማንገሥ ትምህርትን ማስፋፋት ያስፈልጋል።

በብዙ መልኩ አሉታዊ መልዕክቶች እና የውሸት ዜናዎች የሚደርሷቸው ወጣቶች በእነዚህ ቁሳዊ እና ጥላቻን በሚቀሰቅሱ መልዕክቶች ሊወናበዱ አይገባም። ስለ ፍትህ ምንነት በሚገባ ሊያውቁ፣ ከዚህ በፊት ስለተፈጸሙ መጥፎ ታሪኮች ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። ስለ ራሳቸው መብት እንደሚጨነቁ ሁሉ ስለ ሌሎችም መብት መጨነቅ ይኖርባቸዋል። ዛሬ በዚህ የወጣትነት እድሜአቸው በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆሙ የማናደርጋቸው ከሆነ ወደ ፊት በእኛ ላይ የሚፈርዱ ይሆናል። በአመጽ መካከል የምንተዋቸው ከሆነ፣ ያለ ምንም እውቀት የምንተዋቸው ከሆነ መጥፎ ፍርድ ሊፈርዱብን ይችላሉ።

ፍትህ፣ ሰላምን ወደ ዓለም ዳርቻ ለማድረስ የሚያግዝ ሁለተኛው ክንፍ ሲሆን በተግባር ላይ ካልዋለ ቀስ በቀስ ሊጠፋ ይችላል። በመሆኑም ማንም በእግዚአብሔር እየኖረ ነገር ግን ያለ ፍትህ ሊኖር አይችልም።  “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና”። (ማቴ. 7.12)

ሰላም እና ፍትህ የሚለያዩ አይደሉም። ነብዩ ኢሳይያስ እንደሚለው “የጽድቅም ሥራ ሰላም፥ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል” (ኢሳ. 32.17)። ሰላም ከፍትህ የራቀ ከሆነ ይሞታል፣ ነገር ግን ፍትህ ዓለም አቀፍ ካልሆነ ደግሞ ውሸት ሆኖ ይቀራል። ፍትህ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ብቻ፣ በጎረ ቤታሞች  መካከል ብቻ የሚገለጽ ከሆነ ወይም ተመሳሳይ እምነት ባለቸው ሰዎች መካከል ብቻ የሚገለጽ ከሆነ ይህ ፍትህ ዋጋ የሌለው እና የተሳሳተ ፍትህ ሆኖ ይቀራል።

ትርፍን ብቻ ለመሰብሰብ መሮጥ ልብን ያለ ፍቅር እንደሚያስቀር፣ የዓለም የገበያ ሕጎች አስቀድመው በመካከላቸው የግንኙነት መስመር ሳይዘረጉ ሁሉ ነገር በፍጥነት እንዲከናወን በማድረግላይ መሆናቸውን፣ ይህ ደግሞ በቤተስብ መካከል አለመረጋጋን በመፍጠር ውይይት እንዳይደረግ ማድረጉን የዓለም ሐይማኖቶች ማወቅ ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ሐይማኖት ድምጽ ለሌላቸው ደሃ ለሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ድምጽ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። የዓለም ሐይማኖቶች በተጨማሪም በሰዎች መካከል ያለው ወንድማማችነት እንዳይጨልም፣ በሰዎች ላይ ሕገ ወጥ ድርጊት እንዳይፈጸም ማስጠንቀቂያን በመስጠት፣ በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ የሚደርሱ በርካታ ስቃዮችን ላለማየት ብለው ፊታቸውን ማዞር እንደሌለባቸው ማወቅ ያስፈልጋል።

በመለምለም ላይ ያለ በረሃ፣

ወንድማማችነትን እንደ ሰላም መርከብ አድርጌ ከተናገርኩ፣ ተመስጦዬን በወሰደው ሁለተኛው ምስል እና በዙሪያችን ከብቦን ስለሚገኘው በረሃማ ስፍራ መናገር እፈልጋለሁ። በአጭር ዓመታት ውስጥ ይህ አሁን የምንገኝበት በረሃማ ስፍራ፣ በጥበብ በመታገዝ ወደ ብልጽግና እና እንግዶች የሚስተናገዱበት ምቹ ቦታነት ተቀይሮ እንመለከታለን። ካለንበት ተጉዘን ለመድረስ አስቸጋሪ እና እንቅፋት ከበዛበት የበርሃማነት ስፍራ ተለውጦ ዛሬ የተለያዩ ሐይማኖቶች እና ባሕሎች የሚገናኙበት ስፍራ ሆኗል። የዚህ አካባቢ በረሃ የለማው ለጥቂት ዓመታት ብቻ እንዲያገለግል ተብሎ ሳይሆን ለሚቀጥሉት ዓመታትም ጭምር ነው። የአገሩ አሸዋማው መሬት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች እንዲታነጹ በማገዝ፣ የምዕራቡ እና የምስራቁ፣ የሰሜኑ እና የደቡቡ ዓለም እንዲገናኙ፣ ለኑሮ ምቹ ያልነበረ አካባቢ ዛሬ ለበርካታ የተለያዩ ዜጎች የሥራ ዕድልን በመክፈት የዕድገት ስፍራ ሆኗል።

በወንድማማችነት የጋራ ሕይወት ውስጥ ግለኝነት እና ስግብግብነት እንዳለ ሁሉ እድገትም በበኩሉ ጠላት አለውና፣ የተደረሰበትን እድገት ወደ በረሃማነት ሊቀይሩ የሚችሉ እንቅፋቶችን መጥቀስ እፈልጋለሁ። ሙሉ በሙሉ የሰዎችን መብት የሚገድብ የፖለቲካ ሥርዓት እውነተኛና ዘላቂ እድገትን ሊያመጣ አይችልም። ሁለ ገብ ማሕበራዊ ሕይወትን ያገናዘበ ልማት ብቻ ለሰው ልጅ ተስማሚ ይሆናል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከሰዎች ስብዕና ይልቅ ሠርተው በሚያገኙት ሃብት ብቻ ትኩረትን የሚያደርግ፣ ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ይልቅ እነርሱ ለሚያበረክቱት ሥራ ብቻ ትኩርተን የሚያደርግ ሥርዓት ለእድገት ተስማሚ አይደለም። በእነዚህ መካከል ልዩነትን የሚያደርግ ሥርዓት ሰብዓዊ ክብርን፣ ስለ ወደፊት ማሕበራዊ ሕይወት እና ስለ ሕጻናት የወደ ፊት ዕድል የሚጨነቅ አይደለም።

ይህን በተመለከተ ባለፈው ሕዳር ወር “የሕጻናት ክብር በዲጂታሉ ዓለም” በተሰኘ ርዕስ ላይ በአቡ ዳቢ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የተለያዩ ሐይማኖቶች የጋራ ጉባኤ የተደሰትኩበት ሲሆን ይህ ጉባኤ ከመካሄዱ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ በሮም ከተማ ለተካሄደው ተመሳሳይ ጉባኤ ሙሉ ድጋፌን መስጠቴ ይታወሳል። በዚህ ርዕስ ዙሪያ ለተሳተፉት መሪዎች በሙሉ ምስጋናዬን እያቀርብኩ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስም ሙሉ ድጋፌን እና አጋርነቴን መግለጽ እወዳለሁ”።                    

ከተለያዩ አገሮች፣ ባሕሎች እና እምነቶች ወደ እዚህ በረሃማ ስፍራ ለመጡት በሙሉ የሥራ ዕድልን ከመክፈት ጀምሮ ውጤታማ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛል። ከሠራተኞቹ መካከል በአካባቢው ዘመናትን ያስቆጠረው የክርስትና እምነት ተከታዮችም ይገኛሉ። ይህን ዕድል ተጠቅመው ለአገሩ እድገት የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽዖን ማበርከታቸው ይታወቃል። ከአገሩ ሕዝብ በሚሰጣቸ አክብሮት፣ በሐይማኖቶች መካከል ባለው መቻቻል እና በተመቻቸላቸው የአምልኮ ሥፍራ በኩል መንፈሳዊ እድገትን በማግኘት ራሳቸውን እና የሚኖሩበትን አገር እየጠቀሙ ይገኛል። በመሆኑም ይህን ጎዳና በመጓዝ በዚህች አገር የሚኖሩት ይሁኑ በጊዜያዊነት የሚቀመጡትም ቢሆኑ ከአገሩ ሕዝብ እና መንግሥት ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል እና ለተሰጣቸው ዕድል ማመስገን ያስፈልጋል። ይህ መልካም አቀባበል በዚህ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ተግባራዊ ሆኖ ማየትን እመኛለሁ። መአመጽ እና በሌሎች ወንጀሎች ተሰማርተው ካልሆነ በስተቀር የተለያየ እምነት ያላቸው ሰዎች የዜግነት መብታቸው ተከብሮላቸው ማየትን እመኛለሁ።

የወንድማማችነትን መንፈስ በመላበስ በትምህርት ወይም በዕውቀት እና በፍትሕ ላይ የተመሠረተ ማሕበራዊ ኑሮ፣ በአብሮነት መንፈስ እና ሰብዓዊ መብትን በማክበር የሚመጣ የሰው ልጆች እድገት፣ እነዚህ በሙሉ በአገሩ ውስጥ በተግባር እንዲታይ በማለት የዓለም ሐይማኖቶትች ያደረጉት የሰላም ፍሬ ነው። የሰው ልጆች የወንድማማችነት ሕይወት ከዓለም የሐይማኖት ተወካዮች የሚጠብቀው፣ ጦርነትን እና ለጦርነት የምንሰጠውን እውቅና ማስቀረትን ነው። ጦርነት የሚያስከትለውን ጥፋት እና ስቃይ በግልጽ እንመለከታለን። በተለይ በየመን፣ በሶርያ፣ በኢራቅ እና በሊቢያ ጦርነት የሚያስከትለውን ስቃይ ብዙ እያሳሰበኝ ይገኛል። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ወንድሞች እና እህቶች በመሆን ጦርነትን፣ በሃብት ብቻ የሚመሠረት ግንኙነትን፣ ድንበሮችን በጦር መሣሪያ መጠበቅን፣ ድንበሮችን በግድግዳ መዝጋትን፣ ድሆችን መበደልን ከጸሎት በሚገኝ ሃይል እና በጋራ በምናደርጋቸው ውይይቶች በኩል እንቃወማቸው። ዛሬ የእኛ በሕብረት መሆን የመተማመን ምልክት በመሆኑ መልካም ፈቃድ ያላቸው በሙሉ የአመጽ ተገዥ እንዳይሆኑ፣ የልዩነት መሣሪያ እንዳይሆኑ ማበረታታት ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ሰላምን ከሚመኙት ጋር ስለሆነ በምድራችን ለሰላም የሚደረገውን እያንዳንዷን እርምጃ ይባርካል”።

04 February 2019, 16:24