ፈልግ

የጥቃቱ ሰለባዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ የጥቃቱ ሰለባዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኬንያ የደረሰውን የአሸባሪዎች ጥቃት አውግዘው የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ ሆቴል መሣሪያ ታጣቂ አሸባሪዎች በሰዎች ሕይወት ላይ ባደረሱት የሞትና የማቁሰል ጥቃት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በመልዕክታቸው ገልጸዋል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የቅዱስነታቸውን መልዕክት ተቀብለው በመፈረም መላካቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአሸባሪዎቹ ጥቃት የግፍ ተግባር ነው ብለው፣ በሰው ሕይወት መጥፋትና የመቁሰል አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው፣ አደጋው ከደረሰባቸው ጋር በመንፈስ በመተባበር በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም ለመላው የኬንያ ሕዝብ በተለይም በጥቃቱ ሕይወታቸውን ላጡት እና ለቆሰሉት ሰዎች ቤተሰቦች በሙሉ መጽናናትን ተመኝተውላቸዋል።

ጥቃቱን ባካሄደው በአሸባሪ ታጣቂ ቡድን አል ሻባብ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 21 መድረሱ የታወቀ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 16 ኬንያዊያን፣ አንድ ብሪታንያዊ፣ አንድ አሜርካዊ፣ ሌሎች ሦስት ደግሞ አፍሪቃዊ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል። የኬንያ መንግሥት በዚህ ጥቃት እጃቸው አለበት ብሎ የጠረጥራቸውን ዘጠኝ ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉ ታውቋል።

17 January 2019, 17:04