ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ሕሙማንን ሰላም ባሉበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ሕሙማንን ሰላም ባሉበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለ27ኛው ዓለማቀፍ የበሽተኞች ቀን ያስተላለፉት መልእክት

እያንዳንዳችን ድሆች፣ ችግረኞች እና ሚስኪኖች ነን። ስንወለድ ለህልውናችን እና ለእድገታችን የወላጆቻችን እንክብካቤ እና ድጋፍ ያስፈልገናል፣ በተጨማሪም በሁሉም የእድገት ደረጃዎች ውስጥ በሆነ መንገድ እኛን በሚረዱ ሰዎች ላይ ጥገኞች እንሆናለን።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 04/2011 ዓ.ም ለሚከበረው 27ኛው ዓለማቀፍ የበሽተኞች ቀን ያስተላለፉት መልእክት
“በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ” (ማቴ. 10፡8)

በመጪው የካቲት 04/2011 ዓ.ም “በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ” (ማቴ. 10፡8) በሚል መሪ ቃል 27ኛው ዓለማቀፍ የበሽተኞች ቀን እንደ ሚከበር ይታወቃል። ለዚህ 27ኛው ዓለማቀፍ የበሽተኞች ቀን ተገቢ በሆነ መልኩ ቅድመ ዝግጅት ይደረግ ዘንድ በማሰብ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለድዕረ አስተንትኖ የሚረዳ መልእክት አስተላልፈዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ” (ማቴ. 10፡8) በሚል መሪ ቃል ለ27ኛው ዓለማቀፍ የበሽተኞች ቀን ያስተላለፉትን መልእክት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!
“በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ” (ማቴ. 10፡8)። ኢየሱስ ቅዱስ ወንጌልን እንዲሰብኩ ሐዋርያቱን በላካቸው ወቅት በነጻ በተቀበሉት ፍቅር ተሞልተው የእርሱን መንግሥት ያስፋፉ ዘንድ የላካቸው እነዚህን ቃላት ተጠቅሞ ነበር።
በየካቲት 04/2011 ዓ.ም 27ኛው ዓለማቀፍ የበሽተኞች ቀን በሕንድ አገር በሚገኘው በካልካታ ጠቅላይ ግዛት የሚከበር ሲሆን ቤተክርስትያን የሁሉም ልጁቹዋ በተለይም ደግሞ ሕሙማን ለሆኑ ልጆቿ እናት እንደ መሆኗ መጠን እንደ ደጉ ሳምራዊ በፍቅር በተሞላ ስሜት በሽተኞችን ማገዝ በራሱ በጣም ታማኝ የሆነ የቅዱስ ወንጌል ማስፋፊያ ስልት እንደ ሆነ ታስታውሰናለች። በሽተኞችን መንከባከብ ሙያዊ ክህሎትን፣ ርኅራኄን፣ ቅጥተኛ እና ቀለል ያሉ መገለጫዎችን፣ ለምሳሌም በሽተኞች እነርሱን የሚንከባከብ እና የሚወዱዋቸው ሰዎች እንዳሉ ሆኖ እንዲሰማቸው በማድረግ ሊፈጸም ይገባል።
ሕይወት የእግዚኣብሔር ስጦታ ነው። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ “ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ?” (1 ቆሮ 4፡7) በማለት ይናገራል። በአጭሩ የሰው ልጅ ሕይወት በስጦታ መልክ የተገኘ በመሆኑ ይህንን ስጦታ ወደ ግል ስጦታ ብቻ ወይም ደግሞ የግል ንብረታችን ነው ወደ ሚለው አስተሳሰብ ቀንሰነው መመልከት አንችልም፣ በተለይም ደግሞ በሕክምና እና በባዮቴክኖሎጂ ምጥቀት የተነሳ በዚህ እይታ ሕይወትን በመመልከት “የሕይወት ዛፍ” (ዘፍ. 3፡24) በሆነው ላይ ጫና መፍጠር ተገቢ አይደለም።
በዛሬ ዘመን በከፍተኛ ሁኔታ በሚታየው ቁሳቁሶችን የማባከን እና የግዴለሽነት ባሕል መካከል “ስጦታ” የሚለው ቃል በዛሬ ዘመን የሚንጻባረቀውን ግለሰባዊ እና ማህበራዊ ክፍፍል ለመፈተሽ የተሻለው ዓይነት አማራጭ ነው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በማህበረሰብ እና ባህሎች መካከል አዲስ የሆኑ ግንኙነቶችን እና ዘዴዎችን ለማራመድ ጭምር ያስችለናል። የውይይት መድረክ [ . . .] የስጦታ ጽንሰ-ሐሳብ እንድንረዳና- በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ኃይል ለማንቀሳቀስ የሚረዱትን ሰብዓዊ ዕድገትና እድሎች ይፈጥራል። “ስጦታ” ማለት ቁስ የሆኑ ነገሮችን በስጦታ መልክ ከመስጠት የበለጠ ትርጉም አለው - እራስን መስጠት ማለት እንጂ ንብረትን ወይም ቁሳቁሶችን ማስተላለፍ ወይም መስጠት ብቻ ማለት ግን አይደለም። “ስጦታ” ስጦታን ከመስጠት ጋር በጣም ይለያያል፣ ምክንያቱም ነፃ ስጦታን እና ግንኙነትን ለመገንባት ፍላጎት ስላለው ነው። ይህም ለኅብረተሰብ ግንባታ መሠረት የሆነውን ለሌሎች እውቅና መስጠትን ያካትታል። “ስጦታ" የእግዚአብሔር ፍቅር ነጸብራቅ ነው፣ ይህም በወልድ ሥጋ መልበስ እና በመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ የተረጋገጠ ነው።
እያንዳንዳችን ድሆች፣ ችግረኞች እና ሚስኪኖች ነን። ስንወለድ ለህልውናችን እና ለእድገታችን የወላጆቻችን እንክብካቤ እና ድጋፍ ያስፈልገናል፣ በተጨማሪም በሁሉም የእድገት ደረጃዎች ውስጥ በሆነ መንገድ እኛን በሚረዱ ሰዎች ላይ ጥገኞች እንሆናለን። ሁልጊዜም ቢሆን ውስን መሆናችንን መዘንጋት አይኖርብንም፣ በሌሎች ሰዎች እና ሁኔታዎች ፊት "ፍጡራን" መሆናችንን መገንዘብ ይገባል። ይህንን እውነታ በግልጽ ከተቀበልነው ይህ እውነታ እኛ ትሁት እንድንሆን እና በህይወት ውስጥ አስፈላጊ የሆነውን በጎነትን በመፈጸም እንድንመላለስ ያበረታታናል።
እንዲህ ዓይነቱ እውቅና በግለሰብም ሆነ በማህበረሰባችን ውስጥ አንድ መልካም ነገርን ለማራመድ በኃላፊነት እንድንሠራ ያደርገናል። እኛ ራሳችን ከዓለም የተለየን ሳንሆን ከሌሎች ጋር በወንድማማችነት መንፈስ ግንኙነት በምንመሰርትበት ወቅት ለጋራ ጥቅም ዓላማ የሆነውን ማህበራዊ ልምምድ ለማዳበር እንችላለን። ራሳችንን እንደ ችግረኛ ወይም የሌሎች ሰዎች ድጋፍ እንደ ሚያስፈልገን አድርገን መቁጠር መፍራት የለብንም፣ ምክንያቱም በግለሰብ ደረጃ እና በራሳችን ጥረት የእኛን የአቅም ውስንነት ማሸነፍ ስለማንችል ነው። ስለዚህ ውስን መሆናችንን አምኖ መቀበል መፍራት የለብንም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ በኢየሱስ በኩል በትህትና ወደ እኛ መጥቱዋልና (ፊሊ 2 8) በዚህም መልኩ መምጣቱን ስለሚቀጥልም ነው፣ በድህነታችን ውስጥ እርሱ ገብቶ እኛ ካሰብነው በላይ ስጦታዎችን ይሰጠናል።
በሕንድ በሚከበረው በዓል ላይ የካልካታ ቅድስት የሆነችውን የእማሆይ ትሬዛን ተግባር በደስታ እና በአድናቆት ለማስታወስ እፈልጋለሁ - ለድሆች እና ለታመሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ፍቅር ያሳየ የበጎ አድራጎት ተግባር ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። የቅድስና ማዕረግ በተሰጣቸው ወቅት “እማሆይ ትሬዛ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ውስጥ መለኮታዊ ምሕረትን ለሁሉም ሰዎች እንዲዳረስ ያደርጉ፣ ራሳቸውን ለሁሉም ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ የሞከሩ፣ ገና ያልተወለዱ እና በማህጸን የሚገኙትን፣ እንዲሁም የተረሱ እና የተጣሉ የሰው ልጆችን ሕይወት የተንከባከቡ ቅድስት እንደ ነበሩ ተረድቻለሁ። እርሳቸው በመንገድ ላይ እንዲሞቱ በተተው ሰዎች ፊት ለፊት ተንበርክከው በእነርሱ ውስጥ እግዚኣብሔር የሰጣቸውን ክብር ተመለከቱ፣ ኃያላን በሚባሉ የዓለም መንግሥታት ፊት ቀርበው ድምጻቸውን በማሰማት ኃያላን የዓለም መንግሥታት ድህነትን በመፍጠራቸው የተነሳ በመጸሙት ወንጄል የተነሳ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው እና ይህንንም ጥፋታቸውን እንዲገነዘቡ አድርገዋል! ለእማሆይ ትሬዛ ተግባር እንደ “ጨው” በመሆን ጣዕም የሰጠው የርኅራኄ ተግባራቸው ነው፣ ይህም ደግሞ ድህነታቸውን እና ስቃዮቻቸውን ለመግለጽ የሚያስችላቸው እንባቸው በመድረቁ የተነሳ ጠብታ እንባ አጥተው በጨለማ ውስጥ ተቀምጠው ለነበሩ ሰዎች የፈነጠቀ ብርሃን ነበር። እርሳቸው በከተማ እና በከተማ አቅራቢያ ጀምረውት የነበረው ተልዕኮ ዛሬ እኛ ይህንን የእርሳቸውን ተልዕኮ በማስቀጠል የሰው ልጆች ሕልውና መሰረት የሆነውን እምነት በመጠቀም እግዚኣብሔር ለድሆች ሁሉ ቅርብ መሆኑን መመስከር ይኖርብናል።
የእኛ ብቸኛ መስፈርት መሆን የሚገባው ለእያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር የቋንቋ፣ የባህል፣ የጎሳ ወይም የሐይማኖት ልዩነት ሳንፈጥር፣ ከራስ ወዳድነት መንፈስ ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት እንደ ሚገባን እንድንረዳ ዘንድ ቅድስት እማሆይ ትሬዛ ያግዙናል። የእርሳቸው በጎ ምሳሌ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ የደስታ እና የተስፋ ጭላንጭል የሚያመላክት አድማስ እንድንከፍት በማድረግ አሁንም ይመራናል።
በጤናው ክብካቤ ዘርፍ ውስጥ በጣም ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት የሚሰጡ እና የደጉን ሳምራዊ መንፈስ በመከተል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ በጣም ብዙ ሰዎች ተነሳሽነታቸውን ይደግፈዋል፣ መልካም ተግባራቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይረዳል። ለሕሙማን የመጓጓዣ አገልግሎት በመስጠት ላይ የምትገኙ እና ለሕሙማን ድጋፍ በማድረግ ላይ ለምትገኙ የበጎ አድራጎት ማህበራትና የደም፣ የአካል ክፍል በመስጠት ድጋፍ የምታደርጉ ግለሰቦች እና ተቋማት ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በተለይም ደግሞ ለየት ባለ ሁኔታ ለታመሙ ሰዎች መብት፣ በተለይም ልዩ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው በሽታዎች ጋር የተዛመዱ ጉዳዮችን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችላችሁ ዓይነተኛ መድረክ ወይም ቦታ ቤተክርስትያን ናት። በተጨማሪም ግንዛቤ ለማስጨበጥና በሽታን አስቀድሞ መከላከልን ለማበረታታት በማሰብ የተደረጉትን በርካታ ጥረቶችን ለማንሳት እፈልጋለሁ። የእናንተ የበጎ ፈቃድ ተግባር የጤና እንክብካቤ ከመስጠት አንፃር በጤና ተቋማት እና በቤት ውስጥ ከመንፈሳዊ ተግባራት ጋር በተቀናጀ መልኩ የምታደርጉት ተግባር በጣም ጠቃሚ የሆነ ተግባር ነው። በበሽታ የተያዙ፣ በብቸኝነት መንፈስ የሚሰቃዩ፣ አረጋውያን ወይም አቅመ ደካማዎች አእምሮአዊ ወይም አካላዊ በሆነ መልኩ ከእነዚህ እናንተ ከምታበረክቱዋቸው አገልግሎቶች ብዙ ጥቅም ያገኛሉ። በዓለም ውስጥ የቤተ ክርስትያን ምልክት በመሆን ተግባራችሁን እንድትቀጥሉ አበረታታችኋለሁ። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጥ ሰው የግል ሐሳባችንን እና ስሜቶቻችንን ሊጋራ የሚችል ጥሩ ጓደኛ ነው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸው አማካኝነት በሽተኞች እክሎቻቸውን በስሜታዊነት እንዳይቀበሉ እና የዝግጅት ጊዜያቸውን ወደ ተሻለ ህክምና ለማሸጋገር በሚያስችል ግንኙነት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። የበጎ አድራጎት ተግባር ለጋስ ለመሆን ካለው ጥልቅ ምኞት የተወለዱ እሴቶች፣ ባህሪያት እና የአኗኗር ዘይቤዎችን በመፍጠር መልካም ሰዎች ለመሆን እንድንጓጓ ያደርገናል። በተጨማሪም የጤና እንክብካቤን ይበልጥ ሰብዓዊ ለማድረግ የሚረዳ ዘዴ ነው።
በተለይም ደግሞ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሕክምና መስጫ ተቋማት ውስጥ ለጋስነት በተሞላ የፍቅር መንፈስ የሚደረጉ ተግባራት ተነቃቅተው በዓለማችን ውስጥ የሚገኙ በጣም ድሃ በሚባሉ አገራት ውስጥ ሥራቸውን በወንጌል ብርሃን ታግዘው በማካሄድ ላይ ናቸው። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተቋማት የተጠሩት በተቻላቸው መጠን ሁሉ ትርፍ ማግኘትን ያላማከለ ትክክለኛ አገልግሎት በመስጠት፣ ይህንን አገልግሎት የሚሰጡት በምትኩ ሌላ ነገር ለመቀበል በማሰብ ሳይሆን ራስን በመስጠት በለጋስነት እና ሕብረትን መፍጠር በሚያስችል መንፈስ ሊሆን ይገባል።
በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ ትርፍ የማጋበስ እና የማባከን ባህል ለማሸነፍ ወሳኝ የሆኑትን የልግስና እና ስጦታ ሆኖ የመቅረብ ባህልን ማስፋፋት እንደ ሚኖርባቸው ጥሪ አቀርባለሁ። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጤና ክብካቤ መስጫ ተቋማት ራሳቸውን እንደ አንድ የገቢ ማስገኛ ተቋም አድርገው እንዲቆጥሩ ከሚያደርጋቸው የአሰራር ወጥመድ ውስጥ መውጣት ይኖርባቸዋል፣ ከትርፍ ይልቅ ለሰዎች እንክብካቤ መጨነቅ ይኖርባቸዋል። የጤና ክብካቤ ከእውነታው ጋር የተገናኘ፣ ከሌሎች ጋር በመስተጋብር ላይ የተመሠረተና እምነትን፣ ጓደኝነትን እና ትብብርን የሚጠይቅ መሆኑን እንገነዘባለን። ሙሉ በሙሉ ልንጋራው የምንችለው ውድ ሀብት ነው። በልግስና መንፈስ በምንሰጥበት ወቅት የሚሰማን ደስታ የአንድ ክርስቲያን ጤናማ የሆነ የስሜት መለኪያ መሳሪያ ነው።
የበሽተኞች ፈውስ ለሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሁላችሁንም በአደራ እሰጣለሁ። እርሷ እኛ የተቀበልናቸውን ስጦታዎችን በውይይት መንፈስ እና እርስ በእርሳችን በመቀባበል ከሌሎች ጋር መጋራት እንድንችል፣ እንደ ወንድም እና እንደ እህት ሆነን ለጋራ ጥቅማችን ትኩረት በመስጠት እንድንኖር፣ ከመልካም ልብ በመነጨ መልኩ ለጋስ እንድንሆን፣ ከራሳችን ይልቅ ሌሎችን ማገልገል የሕይወት የደስታ ምንጭ እንደ ሆነ እንድንማር ልትረዳን ትችላለች። ከታላቅ ፍቅር ጋር በጸሎት ከእናንተ ጋር መሆኔን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፣ በአክብሮት የእኔ ሐዋርያዊ ቡራኬ ይድረሳችሁ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ
በየካቲት 04/2011 ዓ.ም ለሚከበረው
27ኛው ዓለማቀፍ የበሽተኞች ቀን
ያስተላለፉት መልእክት።
ጥቅምት 15/2011 ዓ.ም ቫቲካን
ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ በዓል
በተከበረበት ወቅት የተጻፈ።

 

11 January 2019, 15:23