ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ክርስቲያኖች የተቀበሉትን ጸጋ በመለዋወጥ በጽናት ወደ ፊት ሊጓዙ ይገባል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥር 10/2011 ዓ. ም. ለክርስቲያኖች ሕብረት የታሰበ የጸሎት ሳምንት፣ በሮም ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ ማስጀመራቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ተኩል ላይ ባስጀመሩት የክርስቲያኖች ሕብረት የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሳሰቡት ለክርስቲያኖች አንድነት ጸሎት በምናቀርብበት ጊዜ በእውነት ላይ የቆምን እና ፍትሃዊ ልንሆን ያስፈልጋል ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለት በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ተገኝተው ለክርስቲያኖች ሕብረት በተደረገው የጸሎት ሳምንት የመጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ሁላችንም እግዚኣብሔር ይሰጠን ዘንድ ስንማጸነው የነበረውና ለክርስቲያኖች ኅብረት ፀሎት የሚደረግበት የመጀመሪያው ሳምንት ዛሬ ይጀምራል። ክርስቲያናዊ ኅበረት የእግዚአብሔር ጸጋ ፍሬ ነው፣ እናም ለጋስ በሆነ እና በተከፈተ ልብ ለመቀበል ራሳችንን ማሰናዳት ይኖርብናል። በዚህ ምሽት በሮሜ ከሚገኙ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ጋር በመገናኘቴ በጣም ተደስቻለሁ፣ እናም ለወንድሞቼ ከልብ የመነጨ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። በተጨማሪም ስለካቶሊክ ቤተክርስቲያን ያላቸውን እውቀት ለማዳበር በማሰብ ከፊንላንድ ተነስተው ወደ ሮም የመጡትን ለሐይማኖት ሕብረት የሚሰራው ተቋም ተማሪዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት እፈልጋለሁ። ሰላምታዬ የክርስቲያን ባሕል ትብብርን በማጠናከር ላይ የሚገኙ ወጣት የኦርቶዶክስ እና የምስራቃዊ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተማሪዎች እና እንዲሁም ለክርስቲያኖች ሕብረት ድጋፍ ለሚያደርገው ምክርቤት ጭምር ሰላምታዬ ይድረሳችሁ።
የኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፍሮ እንደ ነበረ ይገልጻል። በዚህ ስፍራ ሙሴ እንደ አንድ ደግ አባት እና በጌታ የተሾመ መሪ በመሆን ህጉን ለሕዝቡ በመድገም ሕዝቡ ኑሮውን በተስፋዪቱ ምድር ውስጥ ከመሠረተ በኋላ በታማኝነት እና በፍትህ መኖር እንዳለባቸው ያስተምራቸዋል፣ ያስታውሳቸዋል። አሁን የሰማነው ምንባብ ውስጥ እንደ ተገለጸው በዓመቱ ውስጥ የሚከበሩትን የፋሲካ፣ በእለተ ቅዳሜ የሚከበረው ሳምንታዊ በዓል እና የቤተ መቅደስ አመታዊ በዓል እነዚህ ሦስት ዋና ዋና በዓላት እንዴት መከበር እንዳለባቸው ይገልጻል። በእያንዳንዳቸው በእነዚህ በዓላት የእስራኤል ሕዝብ ከእግዚአብሔር ለተሰጡት መልካም ነገሮች ምስጋና እንዲያቀርብ ያደርጉታል። እነዚህ በዓለት የእያንዳንዱን ሰው ተሳትፎ ይጠይቃሉ። “አንተ፥ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፥ ወንድ ባሪያህና ሴት ባሪያህ፥ በአገርህም ደጅ ውስጥ ያለው ሌዋዊ፥ በመካከልህም ያሉት መጻተኛና ድሀ አደግ መበለትም አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራበት ዘንድ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ” (ዘዳግም 16፡11) በማለት ማንም ሰው እነዚህን በዓላት ከማክበር የተገለለ እንዳይሆን ይናገራል።
በእያንዳንዳቸው በእነዚህ በዓላት አምላክ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራበት ዘንድ እያንዳንዱ መንፈሳዊ ነጋዲ ወደ እዚያው መሄድ ይኖርበታል። እዚያም ታማኝ እስራኤላዊ በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ አለበት። ምንም እንኳን እስራኤላዊያን በግብፅ በባርነት ቀነበር ሥር የነበሩ ቢሆንም ቅሉ "በእግዚአብሔር ፊት ግን ባዶ እጃቸውን ይዘው አልቀረቡም”፡ የእያንዳንዱ ሰው ይዞ ሊቀርብ የሚገባው ስጦታ ከጌታ ከተቀበሉት በረከት ጋር የሚመጣጠን ስጦታ መሆን ነበረበት። በዚህ መንገድ ሁሉም የሀገራቸውን ሀብት በጋራ የሚቋደሱ ሲሆን ከእግዚአብሔር መልካምነትም ይጠቀማሉ።
ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሦስቱ ዋና ዋና ክብረ በዓላት በመነሳት የመሳፍንት ሹመቶችን የመግለጹ ጉዳይ ሊያስደንቀን አይገባም። በዓላት በእነርሱ ኃላፊነት የሚመሩ በመሆናቸውና ሁሉም በእግዚአብሄር ምህረት ላይ ጥገኛ እንደሆኑ በመግለጽ ህዝቡ ፍትሃዊ ይሆን ዘንድ ያበረታታሉ። በተጨማሪም ሁሉም የተቀበሉዋቸውን ስጦታዎች ከሌሎች ጋር እንዲጋሩ ጥሪ ያደርጋሉ። በእነዚህ አመታዊ በዓላት እግዚአብሄርን ከማመስገን እና ለእርሱ ክብር ከመስጠት ጋር ጎን ለጎን ሊሄድ የሚገባ ነገር ቢኖር ለባልንጀሮቻችን በተለይም ደግሞ ደካማ ለሆኑ እና ለተቸገሩ ሰዎች ክብር እና ፍትህን በመስጠት ሊሆን ይገባል።
ኢንዶኔዥያውያን ክርስቲያኖች ለዚህ ለሳምንት ያህል ለክርስቲያን ሕብረት ጸሎት በሚደረግበት ሳምንት በተመረጠው የጸሎት ጭብጥ ሐሳብ ላይ በማሰላሰል የመረጡት ቃል “እውነተኛውን ፍርድ ተከተል” (ዘዳግም 16፡20) የሚለው እና ስለፍትህ እና ፍትህ ብቻ የሚያወሳው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። በሀገሪቱ በውድድር መንፈስ የተነሳ በጨመረው ከፍተኛ ፍላጎት በመነጨ መልኩ እየተከሰተ የሚገኘው የሀገራቸው የኢኮኖሚ ዕድገት ብዙዎችን ለድህነት እየዳረገ እና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሀብታም እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ስለሆነ ይህ ጉዳይ አሳስቡኃቸዋል። ይህም የተለያየ ዘር፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች አንድ ላይ ሲኖሩ እርስ በእርሳቸው የኃላፊነት ስሜት የሚጋሩበት ህብረተሰብ መስተጋብርን አደጋ ላይ ይጥላል።
ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ እንዲሁ በቀላሉ በኢንዶኔዥያ ብቻ የሚታይ ነገር ብቻ ሳይሆን ይህ በዓለም ዙሪያ የምናየው ሁኔታ ጭምር ነው። ማህበረሰቡ በጋራ ተጠቃሚ የሚሆንበት እና በሕበረት መኖር የሚያስችላቸው መሰረታዊ መርሆች እየተጣሱ በሚመጡበት ወቅት በጣም አስገራሚ በሆነ መልኩ በሐብት የበለጸጉ፣ በታላላቅ ሕንጻዎች ውስጥ የሚኖሩ፣ በቅንጦት መዐከሎች ውስጥ የሚኖሩ በጣም ብዙ ሰዎች በድህነት ሲማቅቁ፣ ነገር ግን በጣም ጥቂት የሚባሉት ደግሞ በሐብት የሚንፈልሳሰሱበትን አጋጣሚ ይፈጥራል። ፍትሃዊ የሆነ የሐብት ክፍፍል የሌለ ከሆነ ማህበረሰቡ ይከፋፈላል የሚለውን የሙሴ በጥበብ የተሞላ ሕግ ረስተዋል ማለት ነው።
ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ሲጽፍ በነበረው መልእክቱ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ተመሳሳይ ጽንሰ-ሃሳቦችን ይጠቀማል-ጠንካራ የሆኑት ደካማዎቹን መሸከም አለባቸው በማለት ይናገራል። “ራስን ብቻ ማስደሰት” ክርስቲያናዊ የሆነ ነገር አይደለም። የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ደካማ የሆኑትን ለማጽናት የተቻለንን ሁሉ ጥረት ማድረግ አለብን። አጋርነት እና የጋራ ኃላፊነት የክርስቲያን ቤተሰብን የሚገዙ ህጎች መሆን አለባቸው።
እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ህዝብ እኛም በተሰጠን የተስፋ ቃል ውስጥ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ድፍረቱ ይኖረናል። ሆኖም እኛ የተከፋፈልን ስለሆነ የእግዚአብሔርን ፍርድ መለስ ብለን ማስታወስ ያስፈልገናል። የዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች በጥንት ጊዜ የነበሩ እስራኤላውያን እና በአሁኑ ወቅቱ ያሉት በኢንዶኔዥያውያን ዘንድ የሚታወቁትን የአስተሳሰብ አድማስ ለመያዝ ይገደዳሉ፣ ይህም ሀብትን ማሳደድ ደካሞችን እና ርዳታ የሚፈልጉትን ሰዎች መርሳት ማለት ነው። እኛ ሁላችንም የኃጢአት ባሪያዎች ከሆንን፣ ጌታ በጥምቀት ያዳነን እና ልጆቹን እንድንሆን እንደ ጠራን የሚገልጸውን መሰረታዊ ሐሳብ እንረሳለን ማለት ነው። ያገኘነው መንፈሳዊ ጸጋ የግል ንብረታችን አድርገን እንቆጥራለን፣ ለእኛ የተሰጠ እና ለእኛ ብቻ የሚያገለግል የግል ንብረታችን አድርገነው እንወስዳለን። ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸው ስጦታዎች ለሌሎች ክርስቲያኖች የተሰጡት ስጦታዎች እንዳናይ ዓይኖቻችንን ሊያስውር ይችላል። ጌታ ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን የሰጣቸውን ስጦታዎች ማቃለል እና ማጣጣል፣ እግዚአብሔር በአብዛኛው እነርሱን ዝቅ ባለ አስተያየት እንደ ሚመለከታቸው አድርጎ ማሰብ ከባድ ኃጢአት ነው። እንደነዚህ ዓይነት ሀሳቦችን ስናስተናግድ የተቀበልነው ጸጋ በኩራት፣ ፍትሕ በማዛባትና ክፍፍልን በመፍጠር እንዲበላሽ እናደርጋለን። ታዲያ በዚህ መልኩ እንዴት ነው ቃል ወደ ተገባልን መንግሥት ለመግባት የምንችለው?
ይህ መንግሥት አምልኮ የሚጠይቅ መንግሥት ነው፣ ፍትህን የሚጠይቅ መንግሥት ነው፣ ሁሉንም ሰዎች ባማከለ መልኩ የሚከበረ ክብረ በዓል ሲሆን ለሁሉም የተሰጡ ስጦታዎች የሚታዩበት፣ ለሁሉም የሚሰጡበት እና ሁሉም የሚጋበዙበት በዓል የተዘጋጀበት መንግሥት ነው። ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች ሕብረትን መፍጠር ነው፣ በመጀመሪያ የተቀበልናቸው በረከቶች የእኛ በረከት ውጤት አለመሆናቸውን በትህትና መቀበል እና የተቀበልናቸውን ስጦታዎች ከሌሎች ጋር መካፈል ያስፈልጋል። ከዚያም ለሌሎች የክርስቲያን ማህበረሰቦች ለተሰጡ ፀጋዎች ዋጋ ወይም ክብር መስጠት ይኖርብናል። ውጤቱንም ከሌሎች ስጦታዎች ጋር ለመካፈል እንፈልጋለን። ጸጋዎችን አንዱ ለአንዱ በመስጠት እና በመለዋወጥ መንፈስ የበለጸጉ ክርስቲያን ግለሰቦች ወደ አንድነት በሚያመራው መንገድ ላይ በጽናት እና በራስ መተማመን መንፈስ እየተራመዱ የሚገኙ ክርስቲያኖች ናቸው።
 

19 January 2019, 16:50