ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ማርያም እንድትመለከተን፣ እንድታቅፈን እና እንድትይዝ ልንፈቅድላት የገባል!”

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የዓለማችን የማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ 2018 ዓ.ም ተጠናቆ የ2019 ዓ.ም ዓዲስ አመት በታኅሳስ 23/2011 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል። በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር የ2019 ዓ.ም የአዲስ አመት መጀመሪያ ላይ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ከአዲስ አመት በዓል ባሻገር ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ከተደነገጉ አራት የእምነት እውነቶች መካከል በቀዳሚነት የሚገኘውና እ.አ.አ በ250 ዓ.ም አከባቢ ላይ የተደነገገው “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ናት” የሚለውን የሚዘክረው የእምነት እውነት በዓል በታኅሳስ 23/2011 ዓ.ም በታላቅ መንፈሳዊነት ተክብሮ ማለፉ ይታወሳል።
ይህ በዓል በታኅሳስ 23/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእርሳቸው መሪነት በተካሄደውና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ተከብሮ ማለፉን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅቱ ከሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡16-21 ላይ ተወስዶ በተነበበውና መልአኩ ለእረኞች ተገልጾ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላች” ብሎ ባበሰራቸው ወቅት “እረኞቹ እርስ በርሳቸው። እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ” (ሉቃ 2፡16-21) በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “የእግዚኣብሔር እናት የሆነችው ማርያም ወደ እኛ እንድትመለከት፣ እንድታቅፈን እና እጃችንን እንድትይዝ ልንፈቅድላት የገባል” ብለዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በታኅሳስ 23/2011 ዓ.ም የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የዓለማችን ማኅበረሰቦች ዘንድ ከተከበረው የ2019 ዓ.ም አዲስ አመት ጋር ተያይዞ የተከበረውን “ማርያም የአምላክ እናት” መሆኑዋን በሚዘክረው አመታዊ በዓል ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው እናስደምጣችኋለን አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

“የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ” (ሉቃ. 2፡18)። የገና ወቅት በዓላትን በምናጠናቅቅበት በዛሬው እለት ምንም ነገር የሌልው፣ ነገር ግን በፍቅር የተሞላ እና ለእኛ ሲል የተወለደው ሕጻን ልጅ ሁኔታ በማሰላሰል እንድንደነቅ ይጋብዘናል። በእያንዳንዱ አዲስ አመት መጀመሪያ ላይ መደነቅ አለብን፣ ምክንያቱም ስጦታ የሆነው ሕይወታችን እንደ ገና በአዲስ መንገድ ላይ መጓዝ እንድንጀምር እድሉን ስለሚሰጠን ነው።
በተጨማሪም ዛሬ በአምላክ እናት ላይ የምንደነቅበት ቀን ነው። አምላክ እንደ አንድ ትንሽዬ ሕጻን ልጅ በመሆን፣ አምላክ የሆነው ሕጻን በአንዲት ሴት እቅፍ ውስጥ ሆኖ ሲጠባ ታይቷል። ይህንን ምስል በተጨባጭ መልኩ የሚያሳየው ደግማ በፊታችን ያለው ሀውልት ሲሆን ይህም ማርያም እና ልጇ ተቃቅፈው አንድ ሆነው ያሳያል። ያንን ምስጢር ነው ታዲያ ዛሬ እያከበርነው የምንገኘው፣ በጣም የምያስደንቅ ምስጢር ነው፣ በሚገርም ሁኔታ አምላክ ከሰዎች ጋር ዘለዓለማዊ የሆነ ሕብረት ሲፈጥር እናያለን። እግዚኣብሔር እና የሰው ልጅ ሁልጊዜ አብሮ መሆናቸው ደግሞ በዚህ በአዲስ አመት ለእኛ የተገለጸ መልካም ዜና ነው። አምላክ ከእኛ ርቆ የሚገኝ ጌታ አይደለም፣ አምላክ ከእኛ እጅጉን በምያስገርም ርቀት ላይ በሰማይ ሰማያት ውስጥ ብቻውን ርቆ የሚገኝ አምላክ አይደልም፣ ነገር ግን ለእኛ ለእያንዳንዳችን ወንድም ለመሆን ፈልጎ የእኛን ሥጋ የለበሰ፣ ልክ እንደ እኛ ከእናት የተወለደ ነው። የእኛም እናት በሆነችው በእናቱ ታፋ ላይ ሆኖ በሰባዊነታችን ላይ ፍቅሩን ያፈሳል። በእዚያም በልጆቿ ማመንን ያላቆመችና፣ ፈጽሞ ልጆቹዋን ብቻቸውን የማትተው እናት በመሆን እንደ አባትና እናት የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ሙሉ በሙሉ ትገልጻለች።
አማኑኤል የሆነ እግዚኣብሔር ከእኛ ጋር ነው፣ ምንም እንኳን ስህተተኞች፣ ኃጢኣተኞች እና በዓለም ውስጥ የምናራምደው ነገር የተሳሳተ ነገር ቢኖርም እርሱ ግን እኛን ሁሌም ይወደናል። እግዚአብሄር በሰው ልጆች ይተማመናል፣ ምክንያቱም የመጀመሪያ እና ዋነኛው የሰብዓዊ ቤተሰብ አካል የነበረችው የእራሱ እናት ናትና።
በዚህ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ እግዚኣብሔር በሚገልጽልን ድንቅ የሆኑ ነገሮች መገረም እንችል ዘንድ ከማርያም ይህንን ጸጋ እንጠይቅ። እመነት በውስጣችን ለመጀመርያ ጊዜ በተወለደበት ወቅት የነበረንን ድንቅ የሆነ ስሜት በድጋሚ እናድስ። የአምላክ እናት ትርዳን። እርሷ የእግዚኣብሔር እና የሆነች፣ እርሷ የጌታ እናት የሆነች አሁንም ደግሞ በድጋሚ የተወለደውን ሕጻን ልጇን ታቀርብልናለች። እርሷ በልጆቿ ልብ ውስጥ አስደናቂ የሆነ እምነት በድጋሚ እንዲወለድ ታደርጋለች። የመደነቅ ስሜት የሌለበት ሕይወት ደግሞ እንዲሁ ቀዝቃዛ እና አሰልቺ ይሆናል፣ የመደነቅ ስሜት የሌለበት እመንት በዚሁ መልኩ ቀዝቃዛ እና አሰልቺ ይሆናል። ቤተ ክርስቲያን በበኩሉዋ ዘልዓለማዊ የሆነው የእግዚኣብሔር ማደሪያ፣ የክርስቶስ ሙሽራ፣ ልጆችን የምትወልድ እናት በመሆኗ የተነሳ ጭምር ዘወትር በምያስደንቁ ነገሮች መታደስ ይኖርባታል። ያለበለዚያ ግን ቤተ ክርስቲያን ያለፉትን ጊዜያት የምናይበት ውብ የሆነ ሙዚዬም ሆና ትቀራለች። በምትኩ ግን እመቤታችን ቤተ ክርስቲያን እንደ ቤታችን ሆኖ እንዲሰማን ታደርጋለች፣ አዲስ የሚያደርገን እግዚኣብሔር በዚያ እንደ ሚኖር ታረጋግጥልናለች።
ማርያም እንድትመለከተን እንፍቀድላት። በተለይም ደግሞ በችግር ውስጥ በምንገባበት ወቅት፣ ሕይወታችን አደጋኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በምትገባበት ወቅት፣ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓይናችንን ቀና በማድረግ እንመልከት። ይህንን በምናደርግበት ወቅት በቅድሚያ እርሷ ወደ እኛ እንድትመለከት በመፍቀድ ሊሆን ይገባል። እርሷ ወደ እኛ በምትመለከትበት ወቅት በእኛ ውስጥ የምታየው ኃጢኣት ሳይሆን የልጅነት መንፈስ በመሆኑ የተነሳ ነው። ዓይን ለነፍሳችን ወስታወት ነው ይባላል፣ በጸጋ የተሞሉ የማርያም ዓይኖች የእግዚኣብሔርን ውበት የገልጻሉ፣ የሰማይን ነጸብራቅ ያሳያሉ። ኢየሱስ ራሱ በቃሉ ዓይን “የሰውነት መብራት ነው” (ማቴ. 6፡22) ይለናል፣ በመሆኑም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓይኖች ጨለማ በስፈረበት ቦታ ሁሉ ያበራሉ፣ በእየቦታው የጠፋውን የተስፋ ማጣት ስሜት ተመልሶ እንዲበራ ያደርጋሉ። እርሷ እኛን እየተመለከተች “ልብ በል ልጄ ሆይ፣ እኔ እናትህ እዚህ አለሁልህ!” ትለናለች።
የእርሷ እናታዊ የሆነ ምልከታ በእኛ ውስጥ በራስ የመተማመን እና የእምነት መንፈስ እንዲጠንክር ያደርጋል። እመነት ከእግዚኣብሔር ጋር ግንኙነትን መፍጠር የሚለውን ጭብጥ ስለምያመለክት ምልኣት ባለው መልኩ መሳተፍን ያሳያል፣ በምልኣት ከእግዚኣብሔር ጋር መገናኘት የምንችለው ደግሞ የእግዚኣብሔር እናት ከእኛ ጋር በምትሆንበት ወቅት ብቻ ነው። የእርሷ እናታዊ ምልከታ የእግዚኣብሔር ተወዳጅ ሕዝቦች እንደ ሆንን በመግለጽ ያለምንም ልዩነት እና ቅድመ ሁኔታ እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ እና እንድንቀባበል ያደርገናል። ከልዩነት ይልቅ አንድነት በሚታይበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማርያም በዚያ ትገኛለች፣ አንዳችን ለአንዳችን እንክብካቤ ማድረግ እንችል ዘንድ ትረዳናለች። የማርያም እይታ እመንት በፍቅር የተሞላ መሆን እንዳለበት ያመለክተናል። በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እይታ ውስጥ ያለ እምነት ደግሞ ጌታ የሆነው ልጇን የሁሉም ነገር ማዕከል አድርገን እንድንወስድ ያደርገናል፣ ማርያም በፍጹም ወደ ራሷ አመልክታ አታውቅም፣ ነገር ግን እርሷ የምታመለክተው ወደ ወንድሞቻችን እና ወደ እህቶቻችን ነው፣ ይህንንም የምታደርገው እናት በመሆኗ የተነሳ ነው።
ማርያም እንድታቅፈን እንፍቀድላት። ማርያም እንድትመለከተን ልንፈቅድላት ይገባል ከሚለው ሐሳብ በመቀጠል ወደ ልባችን በመመለስ በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውን “ማርያም ሁሉንም ነገር በልቧ ውስጥ ይዛ ታሰላስል ነበር” (ሉቃ 2፡19) የሚለውን እንመልከት። ይህም ማለት በሌላ አገላለጽ ማርያም ሁሉንም ነገር መጥፎም ይሁን በጎ ሁሉንም ነገሮች በልቧ ውስጥ ታስቀምጥ ነበር ማለት ነው። እነዚህም ነገሮች የእርሷ ምስጢራዊ የሆኑ ነገሮች ናቸው። በተመሳሳይ መልኩም ማርያም የእኛን የእያንዳንዳችንን ሕይወት ወደ ልቧ ትወስዳለች፣ ማነኛውንም የእኛን ግላዊ የሆነ ሁኔታ አቅፋ በመያዝ ወደ እግዚኣብሔር ታቀርባለች።
ዛሬ ባለንበት ዓለማችን ውስጥ በሕይወት ውስጥ ዋና ዋና የሚባሉ ነገሮችን ለማርያም በአደራ መስጠት እየተዘነጋ መጥቱዋል። በዚህም የተነሳ በተለይም ደግሞ ጭንቀቶቻችንን የሚቀበል በማጣታችን የተነሳ ትካዜ ውስጥ በመግባት የብቸኝነት ስሜት እየተጠናወተን ይገኛል። በሚገርም ሁኔታ አሁን ያለው ዓለማችን እርስ በእርሱ የተገናኘ ቢመስልም ቅሉ ነገር ግን በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ተለያይቶ ይገኛል። ራሳችንን በአደራ ለእናታችን ልናስረክብ ይገባል። በቅዱሳን መጽሐፍት ውስጥ እርሷ በማነኛው ስፍራ ተጨባጭ በሆነ መልኩ በጣም ብዙ በሚባሉ አጋጣሚዎች እና ሁኔታዎች ውስጥ የእርሷን እቅፍ እናገኛለን፣ በምትፈለግበት ቦታ ሁሉ እርሷ በዚያው ትኖራለች። ለምሳሌም አክስቷ የነበረችሁን ኤልሳቤጥን ጎብኝታለች፣ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይ ተገኝታለች፣ በላይኛው ቤተ ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር በነበረችበት ወቅት ደቀ-መዛሙርቱን አበረታታለች። ማርያም የብቸኝነት እና የትካዜ በሽታዎችን የምትፈውስ ፈዋሽ መድኃኒት ናት። የመማጽኛ እናት ናት። ብቻቸውን ከሆኑ ሰዎች ጋር ሁሉ ማርያም ከእነርሱ ጋር ትሆናለች። አንድን ሰው ለማጽናናት ቃላትን ብቻ መጠቀም በቂ እንዳልሆነ እርሷ በሚገባ ትረዳለች፣ ነገር ግን መጽናናት ከሚሻው ሰው ጋር አብሮ የሚሆን ሰው እንደ ምያስፈልግ ታወቃለች፣ እርሷ እናት በመሆኗ የተነሳ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ትሆናለች። በዚህም ምክንያት እርሷ ሕይወታችንን በእቅፏ ስር አስገብታ እንድትይዝ ልንፈቅድላት ይገባል።
ማርያም እጃችንን ይዛ እንድትጓዝ እንፍቀድላት። እናቶች የልጆቻቸውን እጅ ይዘው ሕይወት እንዴት መመራት እንደ ሚገባው ለልጆቻቸው ያስተምራሉ። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ልጆች በራሳቸው መንገድ ላይ በመጓዝ አስፈላጊውን የጎዞ ጎዳና ስስቱ ይታያል። ብርቱ የሆኑ ይመስላቸውና መንገዱን ስስቱ እናያለን፣ ነጻ የሆኑ ይመስላቸውና ባሪያዎች ሲሆኑ እናያለን። የእናትነትን ፍቅርን ረስተው በሁሉም ነገር ውስጥ በንዴት እና በቸልተኝነት የሚኖሩ ልጆች ስንት ናቸው! ወላጆቻቸው በሚናግሩት ነገር ላይ የሚያምጹ ስንት ልጆች አሉ! ጠንካራ የሆኑ ይመስላቸውና እናቶቻቸውን በቁጣ የሚናገሩ ስንት ልጆች አሉ። በእዚህ አግባብ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የሚኖሩ ጀግና የሆኑ እናቶችን ማድነቅ ያስፈልጋል፣ ለምያሳዩት ርኅራኄ፣ ጥበብ እና የዋዕነት ሊመስገኑ የገባቸዋል።
እግዚኣብሔር ራሱ እናት አስፈልጎት ነበር፣ እኛስ ከእርሱ በላይ እንዴት እናት አያስፈልገን! ኢየሱስ ራሱ በመስቀል ላይ ሆኖ “እችሁትና እናትህ” (ዮሐ. 19፡27) በማለት ለእኛ እናቱን ሰጥቶናል። ማርያም አማራጭ የሆነች የሕይወታችን አካል አይደለችም፣ ነገር ግን የግድ ለሕይወታችን ታስፈልገናለች። እርሷ የሰላም ንግሥት ናት፣ እርሷ ክፉ የሆኑ መንፈሶችን ድል የምታደርግ በመሆኗ በመልካም ጎዳና ላይ እጃችንን ይዛ እንድንራመድ ታደርገናለች፣ ኅበረት እንድንፈጥር ትረዳናለች፣ ርኅራኄ እንዲኖረን ታስተምረናለች።
ማርያም ሆይ እጃችንን ይዘሽ ተጓዢ! ከአንቺ ጋር በመጓዛችን የተነሳ ደግሞ በታሪክ ሂደት ውስጥ በቀላሉ ለመጓዝ ይረዳናል። በእጅሽ ይዘሽ እኛን በመምራት አንድ የምያደርጉንን እሴቶች መልሰን ለመጎናጸፍ እንችል ዘንድ እርጅን። በአንቺ መለኮታዊ ጥበቃ ስር ሰብስቢን፣ በእውነተኛ ፍቅር እንድንሞላ አድርጊን “ቅድስት የአምላክ እናት ሆይ በአንቺ ጥበቃ ሥር እንታመናለን”።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
01 January 2019, 17:21