ፈልግ

Pope Francis' audience Pope Francis' audience 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት የማበረታቻ መልዕክታቸውን አስተላለፉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ለጀመሩት የጸሎትና የሱባኤ ሂደት እገዛ እንዲሆናቸው በማለት በማር. 14. 38 ላይ “ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው” የሚለውን በመጥቀስ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልግሎት ጊዜው፣ ሌሊቱን በጸሎት እንደሚያሳልፍ፣ ሐዋርያቱንም ለጸሎት እንደሚጋብዛቸው አስታውሰዋል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሱባኤ ወቅትን ለሚጀምሩ የሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት በላኩት መልዕክታቸው በቤተክርስቲያናቸው በተፈጸሙት የጾታ ጥቃት በደሎች ላይ በጥልቀት በማስተንተን፣ ምሕረትንም በመለመን ወደ ወንድማዊ ሕብረት እንዲመለሱ አደራ ብለዋል። የሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ብጹዕ ካርዲናል ዲናርዶ በበኩላቸው ለቅዱስነታቸው በላኩት መልዕክት እንደገለጹት በጸሎት በሚያገኙት መለኮታዊ ጥበብና እገዛ በመታገዝ ወደ ፊት የሚጠብቃቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎት በብቃት ለማከናወን የሚያስችል ጉልበት እንደሚያገኙ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በላኩት ሰፋ ያለ መልዕክታቸው እንደገልጹት አመኔታን ማጣት የሚወገደው የተለያዩ ድርጅታዊ ሃሳቦችን በማቅረብ ብቻ ሳይሆን እውነተኛ መለወጥን በማምጣት በመሆኑ ብጹዓን ጳጳሳት ከመላው ምዕመናን ጋር ሆነው የእርቅ መንገድ መጓዝ ይስፈልጋል ብለዋል። በቺካጎ ከተማ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በሚቆየው የሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የጸሎትና የሱባኤ ወቅት በሙሉ በጸሎት በማገዝ ከጎናቸው እንደሚሆኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ገልጸው እየተስፋፋ የመጣውን የበደል ባሕልን መዋጋትና አመኔታን በማጣት የሚደርሰውን ቀውስ ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ለጀመሩት የጸሎትና የሱባኤ ሂደት እገዛ እንዲሆናቸው በማለት በማር. 14. 38 ላይ “ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው” የሚለውን በመጥቀስ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልግሎት ጊዜው፣ ሌሊቱን በጸሎት እንደሚያሳልፍ፣ ሐዋርያቱንም ለጸሎት እንደሚጋብዛቸው አስታውሰው ከዚሁ ሐዋርያው ማርቆስ ከጻፈው በምዕ. 10. 43 ላይ “ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን” የሚለውን በማከል በኢየሱስ ክርስቶስ የአገልግሎት ዘመንም ቢሆን በቅናት የተነሳሱት የማሕበረሰብ ክፍሎች ለቀዳሚነት ስፍራ በመሮጥ እንቅፋቶችን ከማስቀመጥ እንዳልተቆጠቡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል።   

ተግቶ በመጠበቅ በጥበብና እና በማስተዋል መከታተል ይስፈልጋል፣

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የምንወስዳቸው ውሳኔዎች፣ አማራጮች፣ ተግባሮችና ዓላማዎች በሙሉ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚረዱ መፍትሄዎችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ለማግኘት ተግቶ መጠበቅ፣ በጥበብና በማስተዋል መከታተል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በርካታ ጠቃሚ፣ መልካም፣ አስፈላጊና ትክክለኛ የሆኑ ሃሳቦች ቢመነጩም ነገር ግን የቅዱስ ወንጌል መዓዛ ላይኖራቸው ስለሚችል፣ ፈዋሽ መድሐኒት ከበሽታው የከፋ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

በስልጣን ጥማት፣ በሕሊና ውድቀት እና በጾታዊ ጥቃት የቆሰለች የሰሜን አሜርካ ቤተክርስቲያን፣

በመጨረሻዎቹ ዓመታት ውስጥ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ የውደቀች የሰሜን አሜርካ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ውድቀቷም በምዕመናን ዘንድ ባላት አመኔታ ላይ ጉዳትን እንዳስከተለ በመልዕክታቸው ገልጸው፣ በቤተክርቲያኒቱ አገልጋዮች መካከል የሕሊና ጥፋትን እንዳስከተለ፣ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በትክክል አለመወጣታቸውን ግልጽ እንዳደረገና ጉዳቱ በደረሰባቸው ቤተሰቦች ስቃይን እንደዚሁም በመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ በደልን እንዳስከተለ ገልጸዋል።              ከሁሉም በላይ የተፈጸመውን በደል መሰወር ቤተክርስቲያን የደረሰባትን ውድቀት የከፋ እንዲሆን አድርጎታል ያሉት ቅዱስነታቸው የተፈጸሙት ሃጢአቶችና ወንጀሎች በክርስቲያን ማሕበረሰብ፣ በማሕበራዊና ባሕላዊ ተቋማት መካከል ጠባሳን ከመተው በተጨማሪ በምዕመናኑ ልብ ውስጥ ከባድ ቁስልን እንደፈጠረ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በምልዕክታቸው ተናግረዋል።   

አመኔታን ማጣት የሚወገደው ድርጅታዊ ሃሳቦችን በማቅረብ ብቻ አይደለም፣

በመሆኑ ይህን ከመሰለ ጉዳት ለመውጣት አዲስ መንገድ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው አመኔታን ማጣት የሚወገደው የተለያዩ አዳዲስ ድርጅታዊ መዋቅሮችን በመዘርጋት፣ ወይም ምክር ቤቶችን በማቋቋም፣ ወይም ውሳኔዎችን በማተላለፍ እንዳልሆነ ገልጸው፣ አንዳንድ ውሳኔዎችን ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም በቂ እንዳልሆኑና ወደ ድርጅታዊ ችግሮች ውስጥ በማስገባት ወደ ሌላ ችግር ውስጥ እንዳይከት ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

ለወንጌል ተልዕኮ ያለን ግንዛቤ መታደስ ያስፈልጋል፣

አመኔታን ማጣት ለማስቀረት በመካከላችን ያለውን የግንኙነት ደረጃ በሚገባ መመልከት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ መላክም ግንኙነት ያለውን ሕብረተሰብን ለመገንባት ግልጽ መንገዶችን በመከተል፣ የእያንዳንዱን ሰው ግላዊ መብትን ማክበር እንደሚያስፈልግ አሳስበው ይህም ውጤታማ የሚሆነው አዳዲስ ድርጅታዊ ሃሳቦችን በማፍለቅ ብቻ ሳይሆን እውነተኛ የአስተሳሰብ ለወጦችን በማምጣት፣ የጸሎት ሕይወትን በመለማመድ፣ የተጣለብንን የአገልግሎት ተልዕኮአችንን በሚገባ መልኩ በማከናወንና የቤተክርስቲያን ሐብትን በአግባቡ በመጠቀም፣ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በመካከላቸውና ከዓለምም ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማስተካከል እንደሆነ አስረድተዋል። የቤተክርስቲያን ተሃድሶ የሚመጣው የወንጌል ተልዕኮ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲያድግ፣ ሐዋርያዊ አገልግሎትም በቀዳሚነት ቅዱስ ወንጌልን መሠረቱ ሲያደርግ እንደሆነ አስረድተው ይህ ካልሆነ ግን ራስን የመጠበቅ እና የመከላከል ጥረት ብቻ በመሆን ከንቱ ልፋት ይሆናል ብለዋል።

አመኔታ ማግኘት የአንድነት ፍሬ ነው፣

በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ለሚገኝ የሰሜን አሜርካ ሕዝብ፣ ቤተክርስቲያንን የሚያስተዳድሩ ብቻ ሳይሆን አስተዋይ የቤተክርስቲያን እረኞች እንደሚያስፈልጉ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰዎች አስተያየት ላይ ውይይት ይደረግባቸዋል ነገር ግን  በዘመኑ ሁኔታ ላይ ጥበብ በተመላበት መንገድ ማስተዋል እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ምዕመናኑ አሁን ባለበት ሁኔታ ከሁሉ አስቀድሞ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አማካይነት ስልጣንን ለመያዝ የሚያስችል ሕዝባዊ መረጋጋት ሳይሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ያለንበትን ሁኔታ በቤተሰባዊ አሠራር በማስተዋል ለመገምገም የሚያግዝ፣ በጥበብ ልናገለግላቸው በአደራ የተሰጡን ምዕመናን ያለእረኛ ተበታትነው እንዳይቀሩ የሚያደርግ የሕብረት መንፈስን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

በምዕመናኖቻችን ዘንድ ያለን እምነት ከራሳችን ማንነት ወይም በመልካም ነገሮቻችን ወይም በሚሰጠን ክብር ወይም በችሎታችን ሳይሆን የሠራነውን ኃጢአት በመገንዘብ፣ መለወጥ እንደሚያስፈልግ በመናገር እንደሆነ አስረድተው፣ የምንመሰክረው ስለራሳችን ሳይሆን ለአገልግሎት የጠራንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሆነ፣ አስጨናቂና ጨለማ በሆነብን ጊዜ እግዚአብሔር መንገድ እንደሚሆነን፣ እምነታችን በተዳከመበት ጊዜ፣ ተስፋም በቆረጥን ጊዜም ቢሆን በአንድነታችን ጸንተን ስንገኝ የሚመጣ ውጤት እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

በምዕመናን መካከል መተማመ ሊኖር የሚችለው ግልጽነት፣ ትህትናን እና ቸርነትን ያካተተ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሲኖር ነው በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው ለብጹዓን ጳጳሳት በላኩት መልዕክታቸው ለእግዚአብሔር ሕዝብ ለማበርክት የተጠራንበትን ሐዋርያዊ አገልግሎታችንን በድክመታችን እና በስህተታችን የተነሳ ሳናበርክት መቅረት አንችልም ብለዋል። በርካታ ሰብኦዊ ስህተቶች አሉብኝ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ የእርሱን ፍቅርና ርኅራሄ ለመመስከር እኔንም እናንተንም ይጠቀምበናል በማለት የተናገረችውን የቅድስት ማዘር ተሬዛን ንግግር በመጥቀስ ተናግረዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ዲናርዶ መልዕክት ልከዋል።

የሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የጋልቨስቶንና ዩስተን ሊቀ ጳጳስና የሆኑት ካርዲናል ዳንኤል ዲናርዶ በበኩላቸው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በላኩት መልዕክታቸው በሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት መካከል ያለው ሕብረት እንዲያድግ ወደ አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የበለጥ እንድንቀርብ ቅዱስነታቸው በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው ጠይቀዋል። ብጹዕ ካርዲናል ዲናርዶ በማከልም ብጹዓን ጳጳሳቱ በዚህ ሕብረት በመጠናከር የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጋራ ለማለፍ የሚያስችለንን ጥበብ ከእግዚ አብሔር ዘንድ ማግኘት እንችላለን ብለዋል። የሰሜን አሜርካ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ያደረሰባትን ሕመምና የሚታያትን ብሩሕ ተስፋ ተሸክማ ትጓዛለች ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ዲናርዶ የወደፊት ተስፋችንም የሚገኘው ከሌላ ከማንም ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ነው ብለዋል። የሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳስትም በበኩላቸው ቅዱስነታቸውን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው፣ በሐዋርያዊ አገልግሎታቸውም አብሯቸው እንደሆኑና በማከናወን ላይ ባሉት የጸሎትና የሱባኤ ወቅትም ለመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አንድነት በጸሎት እንደሚተባበሩ አረጋግጠውላቸዋል።

ወደ አዲስ ምዕራፍ የመሸጋገሪያ መንገድ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ውስጥ በደልን የመፈጸም ባሕልን፣ ተዓማኒነትን ማጉደልንም ማስወገድ የሚቻለው በጥበብና በማስተዋል ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መንገድን ማግኘት እንደሚያስፈልግ አሳስበው ይህን ማድረግ የሚቻለው አዳዲድስ መመሪያዎችን በማውጣት ወይም ኮሚቴዎችን በመሰየም ሳይሆን በዘመናት ሁሉ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር እንደሆነ፣ ብጹዓን ጳጳሳት ምዕመናንን እንዲያስተምሩ አሳስበው ቀዳሚ ሥራ መሆን ያለበትም በዚህ መነፈስ በመነሳሳት በምዕመናን መካከል ያለውን ሕብረት ማጠናከር እንደሆነ አስረድተዋል። የቤተክርስቲያን ተሐድሶ ከሁሉ አስቀድሞ ሐጢአተኛነትን በመገንዘብ፣ ምህረትን በመለመን  ከጊዜ ወደ ጊዜ ራስን መለወጥን ይጠይቃል ብለዋል።

05 January 2019, 12:15