ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እግዚአብሔርን ማገልገል ማለት ቃሉን ማዳመጥ እና በተግባር ላይ ማዋል ነው”

ዛሬም ቢሆን እናታችን ማርያም ለእኛም ቢሆን “እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” ትለናለች።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰብሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ በሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ላይ ተመስርተው አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት በጥር 12/2011 ዓ.ም ቅዱስነታቸው ያደርጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከዮሐንስ (2፡1-11) በተጠቀሰው እና ኢየሱስ በቃና ዘገሊላ የመጀመሪያውን ተዐምራት ማድረጉን በሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን” እግዚአብሔርን ማገልገል ማለት ቃሉን ማዳመጥ እና በተግባር ላይ ማዋል ማለት ነው” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸሶኮስ በእለቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
ባለፈው ሳምንት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የጥምቀት በዓል ካከበርን በኋላ መደበኛ የሆነ የስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር መጀመራችን የሚታወስ ሲሆን በዚህም ወቅት ኢየሱስ በዓለም ውስጥ የሚያደርገውን እና አብ ወደ ዓለም ልኮት እንዲፈጽም ያዘዘውን ተልዕኮ የምንከተልበት ወቅት ነው። በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ዮሐንስ 2፡1-11) ኢየሱስ በይፋ ያከናወነውን የመጀመሪያውን ተዐምር እናገኛለን። ኢየሱስ ከፈጸማቸው ተዐምራት ውስጥ የመጀመሪያው የተፈጸመው በገሊላ ክፍለ አገር ቃና በምትባል መንደር ውስጥ በሰርግ ግብዣ የተፈጸመው ተዐምር ኢየሱስ የፈጸመው የመጀመርያ ተዐምር ነው።
በኢየሱስ ይፋዊ ሕይወት መጀመርያ ላይ የሰርግ ግብዣ መጠቀሱ እንዲሁ በድንገት የሆነ ነገር አይደለም፣ ምክንያቱም በእርሱ አማካይነት እግዚኣብሔር አብ ከሰብዓዊነታችን ጋር በመጋባቱ ነው። ይህም መልካም ዜና ሲሆን ነገር ግን እርሱን ወደ ሰርጉ ግብዣ የጠሩት ሰዎች ግን እርሱ ከእነርሱ ጋር በጠረጴዣ ዙሪያ የተቀመጠው እርሱ እውነተኛው ሙሽራ የሆነ የእግዚኣብሔር ልጅ መሆኑን ግን አሁንም አላስተዋሉም ነበር። እንዲያውም በቃና የተከሰተው ተዐምር መሰረቱን ያደረገው በዚሁ መለኮታዊ ሙሽራ በሆነውና ራሱን በይፋ በገለጸው በኢየሱስ ላይ ነው። ኢየሱስ ራሱን እንደ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሙሽራ አድርጎ ገልጧል፣ እሱም በነቢያት የተናገረውን፣ እርሱ ከእኛ ጋር ያለውን ጥልቅ የሆነ ግንኙነት በመግለጽ አዲስ የፍቅር ቃል ኪዳን ይመሰርታል።
በቃል ኪዳን አተያይ ውስጥ በዚህ ተዓምር ማዕከል ውስጥ የሚገኘው የወይን ጠጅ ተምሳሌት ትርጉም ሙሉ በሙሉ ተገልጹዋል። ግብዣው ሊጠናቀቅ ሲል የወይን ጠጅ ያልቅባቸዋል። በዚህን ጊዜ ማርያም ወደ ኢየሱስ ቀርባ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” (ዮሐ. 2፡3) ብላ ትነግረዋለች። ምክንያቱም ግብዣውን በውሃ መቀጠሉ መጥፎ የሆነ ነገር ስለነበር! ለእነዚያ ሰዎች ግብዣውን በውሃ መቀጠል ጥሩ መስሎ አልተሰማቸውም ነበር። ማርያም እናት በመሆኑ የተነሳ ይህንን ችግራቸውን ፈጥና ተረድታ ወደ ልጇ ዘንድ ሄደች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለይም የትንቢት መጽሐፍት ውስጥ የወይን ጠጅ መሲሃዊ የሆነ ግብዣን እንደ ሚያመልካት ተገልጹዋል (አሞጽ. 9፡13-14, ኢሳያስ 25፡6)። ውኃ ለኑሮ አስፈላጊ የሆነ መሰረታዊ ነገር ነው፣ ነገር ግን ወይን ጠጅ በአንድ ግብዣ ላይ በዓሉ በደስታ የተሞላ እንደ ሆነ ያሳያል። ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ የቀየረው “የመንጻት ስረዓት የሚፈጸምባቸውን የድንጋይ ጋኖች” ተጠቅሞ ነበር። ወደ ቤት ከመግባታቸው በፊት በውሃ የመንጻት ስርዓት ማድረግ የተለመደ ነገር ነበር። በዚህም ድርጊቱ ኢየሱስ አንድ ታላቅ የሆነ ትምህርት ያስተምረናል፣ እርሱም የሙሴን ህግ ወደ ወንጌል ሕግ ይቀይራል።
ከዚያም ማርያም እንመልከትን፦ ማርያም ለአገልጋዮቹ “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” ብላ የተናገራችው ቃላት የቃና ዘገሊላ ሰርግ ዘውድ ያመልክታሉ። ዛሬም ቢሆን እናታችን ማርያም ለእኛም ቢሆን “እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” ትለናለች። እነዚህ ቃላት እናታችን ለእኛ በውርስ የሰጠችን ቃላት ናቸው። በቃና ዘገሊላ ስርግ ግብዣ ላይ የነበሩ አገልጋዮች የማርያምን ቃል ሰምተው በተግባር ላይ አዋሉት። “ኢየሱስም ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም”። በዚህ በሰርግ ግብዣ ውስጥ አዲስ ቃል ኪዳን በእውነት የተደነገገ ሲሆን አዲሱ ተልእኮ ለጌታ አገልጋዮች ሁሉ ማለትም ለአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ እና “እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚለው ነው። እግዚአብሔርን ማገልገል ማለት ቃሉን ማዳመጥ እና በተግባር ላይ ማዋል ማለት ነው። ይህ የኢየሱስ እናት ቀላል እና ጠቃሚ ምክር ነው፣ ይህ የክርስትና ሕይወት መርሕ ነው።
አብዛኞቻችን በሕይወታችን ውስጥ በእርግጥ ሊያጋጥሙን ከሚችሉ ነገሮች ውስጥ አንድ ታሪክ ማንሳት እፈልጋለሁ። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን፣ እንዴት መፍትሄ እንደምንገኝ የማናውቃቸው ችግሮች ሲከሰቱ፣ ብዙ ጊዜ ጭንቀት እና ውጥረት ሲሰማን፣ ደስታ ሲጎለን፣ ወደ እናታችን ወደ ማርያም በመሄድ “የወይን ጠጅ እኮ የለኝም” እንበል። የወይን ጠጅ አልቆብኛል። ተመልከቺ የእኔን ሁኔታ፣ ልቤን ተመልከቺ፣ ንፍሴንም ተመልከቺ” ብለን ልንነግራት ይገባል። ለማርያም እንዲህ ብለን ችግራችንን በምንናገርበት ወቅት እርሱዋም ወደ ልጇ ዘንድ ሄዳ “ይህንን ተመልከት፣ ያንንም ተመልከት፣ የወይን ጠጅ የላቸውም” በማለት ትነገረዋላች። ከዚያም በኋላ ወደ እኛ ተመልሳ በመምጣት “እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” በማለት ትመልሳለች።
ለእያንዳንዳችን የድንጋይ ጋኖችን መሳብ ማለት ቃሉን በሕይወታችን ውስጥ ተቀብለን የእግዚአብሔርን ጸጋ በሕይወታችን ውስጥ መለማመድ እና በምስጢራት ሕይወታችንን መገንባት ማለት ነው። ስለዚህ እኛም የግብዣው ኋላፊ እንደ ተናግረው “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል” ብለን መናገር እንችላለን። ኢየሱስ ሁሌም ድንቅ የሆኑ ነገሮችን ያደርጋል። በዚህም የተነሳ እኛ ከማርያም ጋር መነጋገር ይኖርብናል፣ እርሷም የእኛን ችግሮች ሁሉ ወደ ልጇ ታቀርባለች።
ቅድስት የሆነች እመቤታችን ድንግል ማርያም “እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” ያለችሁን ቃል በመቀበል የኢየሱስን ጥሪ መከተል እንችል ዘንድ ትርዳን፣ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለኢየሱስ መክፈት እንችል ዘንድ ትርዳን፣ በሕይወታችን ውስጥ ኢየሱስ መኖሩ እየተሰማን መኖር እንችል ዘንድ እርሷ ትርዳን።

 

22 January 2019, 10:09