ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ምስጢረ ጥምቀትን በተቀበልንበት ወቅት የገባነው ቃል ማስታወስ ያስፈልጋል”።

“ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትን የጥምቀት በዓል በምናከብርበት ወቅት እኛም ምስጢረ ጥምቀት በተቀበልንበት ወቅት የገባነውን ቃል ኪዳን በማስተውስ በተግባር ላይ ማዋል ይገባናል”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በእለቱ በሚነበቡት የእግዚኣብሔር ቃላት ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ለመከታተል በርካታ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እንደ ሚሰበሰቡ ይታወቃል። በዚህም መሰረት የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በትላንትናው እለት ማለትም በጥር 05/2011 ዓ.ም በተከበረው እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት የጥምቀት በዓል በተከበረበት ወቅት ይህንን በዓል ከግምት ባስገባ መልኩ፣ በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌላ ላይ መስረቱን ባደርገው አስተንትኖ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትን የጥምቀት በዓል በምናከብርበት ወቅት እኛም ምስጢረ ጥምቀት በተቀበልንበት ወቅት የገባነውን ቃል ኪዳን በማስተውስ በተግባር ላይ ማዋል ይገባናል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በትላንትናው እለት ማለትም በጥር 05/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮ አደባባይ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
ዛሬ በምናከብረው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ቀደም ሲል ጀምረነው የነበረው የገና በዓል ስርዓተ አምልኮ ይጠናቀቃል። የዛሬው እለት ስርዓተ አምልኮ በቅርብ ጊዜ ባከበርነው የገና በዓል ወቅት የተወለደውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ምልኣት ባለው መልኩ እንድናውቀው ይጋብዘናል፣ ለዚህም ነው እንግዲህ የዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 3፡15-16,21-2) ሁለት አንኳር የሆኑ አስፈላጊ ነገሮችን የሚያብራራልን በዚሁ ምክንያት ነው፣ ከእነዚህ አንኳር ጉዳዮች መካከል በቅድሚያ የምናገኘው ኢየሱስ ከሕዝቡ ጋር የነበረውን ግንኙነት የሚያሳይ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ኢየሱስ ከአባቱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ያሳያል።
በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በመጥምቁ ዮሐንስ አማካይነት መጠመቁን በሚያሳይ ታሪክ ውስጥ የህዝቡን ሚና እንመለከታለን። ኢየሱስ በሕዝቡ መካከል ነበረ። ይህ ደግሞ የዚህ ታሪክ የጀርባ ዳራ ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን የክስተቱ አስፈላጊ ክፍል ነው። ኢየሱስ ወደ ውሃ ውስጥ ከመግባቱ/ከመጥለቁ በፊት በሕዝቡ ውስጥ "ገብቶ/ጠልቆ" ይገኝ ነበር፣ በዚህም ተግባሩ የሰው ልጆችን ስብዕና ሙሉ በሙሉ ይወስዳል፣ ከኃጢአት በስተቀር ሁሉንም ነገር ይጋራል። በመለኮታዊ ጸጋ፣ በጸጋና በምህረት በመሞላት፣ የአለምን ኃጢኣት ለማስወገድ የእኛን ስጋ ለብሶ ሰው የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ፣ መከራዎቻችንን እና ሰብአዊ ሁኔታዎቻችንን ለመካፈል መጣ። ዛሬም ቢሆን የኢየሱስን መገለጽ እያከበርን እንገኛለን፣ ምክንያቱ ኢየሱስ በመጥምቁ ዮሐንስ ለመጠመቅ በሄደበት ወቅት፣ በተመሳሳይ መልኩ በኋጢኣታቸው ተጸጽተው ለመጠመቅ በሄዱ ሰዎች መካከል መገኘቱ በራሱ የእርሱን ተልዕኮ አመክንዮ እና ሁኔታ ያሳያል።
መጥምቁ ዮሐንስ ይሰጠው የነበረውን እና መንፈሳዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለውን የንስሐ ጥምቀት ለማድረግ የሚጠባበቁ ሰዎችን በመቀላቀሉ የተነሳ ኢየሱስ በተጨማሪም ውስጣዊ እድሳት ለመሻት ያለውን ጥልቅ ፍላጎት ያሳያል። “መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ በርግብ አምሳል ይወርዳል” (ሉቃስ 2፡22)፣ ይህም በሕይወታቸው ውስጥ ክርስቶስን የሚቀበሉትን ሁሉ የሚያካትት አዲስ ፍጥረት መሆን ማለት ሲሆን ከኢየሱስ ጋር ሕይወት መጀመራቸውን የሚያሳይ አዲስ ምልክት ነው። እያንዳንዳችንም በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት ከክርስቶስ ጋር በአዲስ መልክ ተወልደናል፣ ለእኛም ቢሆን “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” (ሉቃስ 2፡22) የሚለው ቃል ለእኛም ተሰቶናል። ምስጢረ ጥምቀትን በተቀበልንበት በጥምቀታችን ቀን ሁላችንም አብ ለእኛ ያለውን ፍቅር በልባችን መቀበላችን የሚያስታውሰን ሲሆን ይህም በጸሎት እና በበጎ ተግባራት መደገፍ ያለበት ስጦታ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ወንጌላዊው ሉቃስ በዛሬው እለት ቃሉ አንኳር የሆነ አስፈላጊ ነገር ያብራራልናል፣ ኢየሱስ በህዝቡ መካከል ነበረ፣ ከዚያም በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ገብቶ ከተጠመቀ በኋላ፣ ኢየሱስ ራሱን በጸሎት ስሜት ውስጥ ያስገባል ይህም ማለት ከአብ ጋር አንድነትን ይፈጥራል። ኢየሱስ ተልዕኮውን በይፋ የጀመረው ጥምቀትን ከተቀበለ በኋላ ነው፣ ከእግዚኣብሔር ዘንድ ወደ አለም ተልዕኮ መምጣቱን እና የእግዚኣብሔርን መልካምነት እና ለእርሱ ያለውን ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ ለማሳየት በአብ የተሰጠውን ተልዕኮው ጀመረ። ይህ ተልዕኮ የሚከናወነው በአብ እና በመንፈስ ቅዱስ ቋሚ እና ፍጹምነት ባለው ኅበረት አማካይነት ነው። የቤተክርስቲያን እና የእያንዳንዳችን ተልዕኮ ሳይቀር ታማኝና ፍሬያማ ሊሆን የሚችለው ኢየሱስ "ተሳታፊ” ሲሆን ብቻ ነው። ክርስቲያናዊ ምስክርነት ለመስጠትና ሐዋሪያዊ ተግባሮችን ለማከናውን ቀጣይነት ባለው መልኩ ጸሎት ያስፈልጋል፣ ይህም እንደ ሰዎች እቅድ ሳይሆን፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር እቅድ እና ስልትን መሰረት በማድረግ ግልጽ የሆነ የወንጌል እና የሐዋሪያዊ ተግባሮችን መደገፍ ማለት ነው።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ የጌታ ጥምቀት በዓል እኛ ምስጢረ ጥምቀትን በተቀበልንበት ወቅት የተጠቀምናቸውን ቃላቶች በአድናቆት በመግለጽ እና እምነታችንን በማደስ በእየለቱ ከዚህ ጋር የሚመጣጠን ሕይወት እንድንኖር እድሉን ይሰጠናል። እንደዚሁም ብዙ ጊዜ እንደነገርኳችሁ ምስጢረ ጥምቀት የተቀበላችሁበትን ቀን ማወቅ በጣም ጠቃሚ የሆነ ነገር ነው። አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡ “ከእናንተ ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበለበትን ቀን የሚያውቅ ሰው አለ ወይ?”። እርግጠኛ ነኝ አንዳንዶቻችሁ ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበላችሁበትን ቀን አታውቁትም። ከእናንተ መካከል ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበለበትን ቀን የማያውቅ ሰው ካለ ወደ ቤታችሁ ስትመለሱ፣ ወላጆቻችሁን፣ የእድሜ ባለጸጋ የሆኑ አያቶቻችሁን፣ አጎቶቻችሁን፣ የክርስትና አባት/እናትቶቻችሁን፣ . . .ወዘተርፈ “በምን ቀን ነው ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበልኩት?” በማለት ጠይቁዋቸው። ከዚያን በኋላ ደግሞ ይህንን ቀን በፍጹም መርሳት አይኖርባችሁም፣ ይህንን ቀን በልባችሁ በመያዝ በእየአመቱ ማክበር ይጠበቅባችኋል።
መልካም በመሆናችን የተነሳ ሳይሆን ወደር በሌለው የአባቱ መልካምነት የተነሳ ኢየሱስ ለሁላችንም ምሕረት ያደርግልናል። የምሕረት እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አብነታችን እና መሪያችን ትሁን።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

14 January 2019, 14:27