ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ  

መልካም ፖለቲካ ለሰላም

የላቀ ስብዕና ያለውና ኃላፊነቱን በሚገባ የሚረዳ ፖለቲከኛ የተባረከ ይሁን።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ጥር 1/2011 ዓ.ም ለተከበረው 52ኛው ዓለማቀፍ የሰላም ቀን የመረጡት መሪ ቃል “መልካም ፖለቲካ ለሰላም” የሚለው እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን “ማንኛውም ፖለቲካ ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብር እና የሚያስከብር፣ የዜጎችን ስብዕና የሚገነባ፣ ወጣቶችን የሚያበረታታ ከሆነ ፖለቲካ ለበጎ አድራጎት ተግባር እና ለሰላም ግንባታ አገልግሎት የሚውል ድንቅ መሳርያ ይሆናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካንዘ

“የፖለቲካ ኃላፊነት ለሁሉም ዜጎች፣ በተለይም ደግሞ ሕዝቡን ለመጠበቅ እና ለመምራት ስልጣን በተሰጣቸው ሰዎች ትክሻ ላይ እንደ ሆነ” የሚገልጸው መልእክቱ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የዓለማችን ማኅበረሰቦች ዘንድ በተከበረው የ2019 ዓ.ም አዲስ አመት መባቻ ላይ ለተከበረው ዓለማቀፍ የሰላም ቀን ይሆን ዘንድ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የተመረጠው መሪ ቃል “መልካም ፖለቲካ ለሰላም” የተሰኘው ሐረግ እንደ ሆነ ቀደም ሲል መግለጻችን ይታወሳል።

ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው የመተማመን መንፈስ በመገንባት ብቻ ነው
የዚህ “መልካም ፖለቲካ ለሰላም’ በሚል አርእስት የቀረበው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መልእክት ዋነኛው ተልዕኮ ሕገ-ወጥነትን በማስወገድ፣ የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች በማረጋገጥ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለያዩ ሚናዎችን የሚጫወቱ አካለት መካከል ውይይት እንዲደረግ በማበረታታት በአዲሱ ትውልድ እና በባሕል መካከል ያለውን ልዩነት በውይይት በመፍታት ሰላምን ማረጋገጥ” የሚል ተልዕኮ ያነገበ መልእክት እንደ ሆነ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በአንድ ማኅበርሰብ ውስጥ እርስ በእርስ የመተማመን መንፈስ የሌለ እንደ ሆነ ሰላምን ማረጋገጥ እጅግ ከባድ እንደ ሚሆን በሰፊው የሚያትት መልእክት ነው።
የከፍተኛ ፍቅር መገለጫ እና የልግስና ልምዶች አንዱ አካል የሆነው መልካም ፖለቲካ ለሕይወት እና ለዓለማችን እንዲሁም በጣም ወጣት እና ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች የመጪው ጊዜ ፍላጎቶቻቸውን በሚገባ ለሟሟላት ከፍተኛ የሆነ ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ እንደ ሆነ፣ በዚህም የተነሳ ማነኛውም ዜጋ ሰላምን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት መካፈል ይኖርበታል የሚል እንድምታ ያዘለ መልእክት ነው።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በጥር 01/2019 ዓ.ም በተከበረው 52ኛው ዓለማቀፍ የሰላም ቀን ይሆን ዘንድ “መልካም ፖለቲካ ለሰላም” በሚል አርእስት በኅዳር 30/2011 ዓ.ም ይፋ ያደረጉትን መልእክት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

መልካም ፖለቲካ ለሰላም

1. “ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን!”
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን ለመንፈሳዊ ተልዕኮ በላከበት ወቅት “ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፣ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። በዚያም ሰላም ወዳድ ሰው ቢኖር ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለበለዚያ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል” (ሉቃ 10፡5-6) በማለት ልኩዋቸው ነበር። ሰላምን ማረጋገጥ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከተሰጣቸው ተልእኮዎች መካከል ቀዳሚው ነው። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በሚያሳዝን እና አሰቃቂ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሰላምን ለማግኘት ለሚፈልጉ ወንዶች እና ሴቶች ሁሉ ይህ ሰላም ይሰጣቸዋል። ኢየሱስ "ቤት" በማለት የተናገረው በሁሉም ስብዕና እና ታሪክ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሀገር እና አህጉር ነው። ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ማንንም ሳያገል እና ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይፈጠር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው እያንዳንዱ ግለሰብ ነው። በመቀጠል እግዚኣብሔር እንድንከባከበው እና እንድንጠብቀው የሰጠንን "የጋራ መኖርያ ቤታችን” የሆነውን ዓለማችንን ይመለከታል። በመሆኑም በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ላይ (በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ.ም አዲስ አመት) “ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን” በማለት ሰላምታዬን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።
2. መልካም ፖለቲካ የሚገጥሙት ተግዳሮቶች
ገጣሚው ቻርለስ ፒዬጊ (እ.አ.አ 1914 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ፈረንሳዊ ገጣሚ ነው) እንደገለጸው “ሰላም የተስፋ በዓል ነው”። ልክ በአንድ ድንጋያማ በሆነ ስፍራ ላይ ለመብቀል ወይም ለማበብ እንደ ሚፈልግ አበባ ዓይነት ነው። ፖለቲካ ሰብዐዊ ህብረተሰብና ተቋማትን መገንባት የሚያስችል ወሳኝ ዘዴ ነው፣ ነገር ግን የፖለቲካ ሕይወት ለህብረተሰብ አጠቃላይ አገልግሎት የማይውል ከሆነ በተቃራኒው የጭቆና፣ የማግለያ እና በተጨማሪም የጥፋት መንገድ ሊሆን ይችላል።
ኢየሱስ እንዲህ ይላል “የሁሉም የበላይ ሊሆን የሚፈልግ ሰው የሁሉም አገልጋይ ይሁን” (ማር. 9፡35) ይለናል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ “በሀገር ውስጥ፣ በክልል፣ በብሔራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ፖለቲካዊ አቋም መገንባት ማለት እያንዳንዱ ግለሰብ እውነታውን እንዲረዳና፣ ነጻነት ክብር ሊሰጠው የሚገባ እሴት መሆኑን በመረዳት ለእያንዳንዱ ግለሰብ፣ ለከተማው፣ ለሀገር እና በአጠቃላይ ለሰብዓዊ ፍጡር መልካም ተግባሮችን በጋራ እንዲሠራ መንገዱን መክፈት ማለት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
ስለዚህ ፖለቲካዊ የሆኑ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ የሚገኙ እና የፖለቲካ ሃላፊነታቸውን በሚገባ በመወጣት ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ከፍተኛ የሆነ ጥረት በማደረግ በሀገራቸው የሚኖሩ ስዎችን ለመጠበቅ እና ለአሁኑና ለሚመጣው የወደፊት ጊዜ መልካም ሁኔታዎችን ለመፍጠር የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉ የሚገፋፋ ነው። ፖለቲካ ለሰዎች መሠረታዊ ክብር መረጋገጥ የሚውል ከሆነ፣ ለነጻነት እና ሰብዓዊ የሆኑ መብቶችን ለማስከበር የሚተጋ ፖለቲካ ከሆነ የፓለቲካ ሕይወት የላቀ የፍቅር መገለጫ ሊሆን ይችላል።
3. ልግስና እና የሰው ልጅ መልካም ባሕሪዎች፡ ፖለቲካ ለሰብዐዊ መብት መከበር እና ሰላምን ለማረጋገጥ መሰረት ነው።
የቀድሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት በነዴክቶስ 16ኛ “እያንዳንዱ ክርስቲያን ከተሰጠው ማነኛውም ዓይነት የጥሪ አገልግሎት እና ተጽኖ ማሳደር በሚችልበት ፖለቲካዊ ስልጣን ጋር በሚመጣጠን መልኩ የበጎ አድራጎት ተግባሩን ማካሄድ ይገባዋል። በሰብዐዊ ርህራሄ በመታገዝ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስከበር የሚደረግ ማነኛውም ጥረት ከዓለማዊ እና ፖለቲካዊ አቋም በላይ ዋጋ ያለው ነገር ነው. . . የሰው ልጅ ማነኛውም ዓይነት ምድራዊ እንቅስቃሴ በልግስና ተግባራት ተነሳሽነት እና ድጋፍ ሲካሄድ የሰው ልጅ ታሪክ ግብ የሆነውን የእግዚኣብሔርን መንግሥት ከተማ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋል” ማለታቸው ይታወሳል። ይህ ማለት ሁሉም ፖለቲከኞች ለሰብዐዊ ቤተሰብ ጥቅም አብረው ለመስራት እና ማነኛውንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያራምዱት የሰው ልጆችን መልካም ምግባር ለመደገፍ ከፈለጉ እያንዳንዱ ፖለቲከኛ ከባህሉ ወይም ከሐይማኖቱ ጋር ሊስማሙ የሚችሉትን ፍትህ፣ እኩልነት፣ የመከባበር፣ የታማኝነት፣ የሐቀኝነት እቅዶችን በመቅረጽ ለማስፈጸም መትጋት ይኖርባቸዋል።
በዚህ ረገድ "የፖለቲከኞችን ባህሪ" በተመለከተ የተናገሩት ታማኝ የወንጌል አገልጋይ የነበሩ እና እ.አ.አ በ2002 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ቬታናማዊው ካርዲናል ፍራነቼስኮስ ዛቬየር ሙሄን ቫብ ቷዋን ፖለቲከኞችን በተመለከተ የተናገሩትን ማስታወስ ያስፈልጋል። እንዲህም ይሉ ነበር. . .

 የላቀ ስብዕና ያለውና ኃላፊነቱን በሚገባ የሚረዳ ፖለቲከኛ የተባረከ ይሁን።
 በግለሰብ ደረጃ ታማኝ የሆነ ፖለቲከኛ የተባረከ ይሁን።
 ለራሱ/ሷ የግል ጥቅም ሳይሆን ነገር ግን ለጋራ ጥቅም የሚሠራ ፖለቲከኛ የተባረከ ይሁን።
 ተለዋዋጭ ባሕሪ የሌለው ፖለቲከኛ የተባረከ ይሁን።
 ለአንድነትን የሚሠራ ፖለቲከኛ የተባረከ ይሁን።
 መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ለማምጣት የሚሠራ ፖለቲከኛ የተባረከ ይሁን።
 የማዳመጥ ክህሎት ያለው ፖለቲከኛ የተባረከ ይሁን።
 ምንም ዓይነት ፍርሃት ያልተጠናወተው ፖለቲከኝ የተባረከ ይሁን።


እያንዳንዱ ምርጫ እና ዳግም ምርጫ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ሕዝባዊ ሕይወት ቀደም ሲል ወደ ነበረው ፍትህን እና ሕግን የማረጋገጥ ግብ ለማነቃቃት እና ለመመለስ እድል ይሰጣል። እንድ እርግጠኛ የሆነ ነገር አለ፣ መልካም ፖለቲካ ለሰላም አስፈላጊ ነው። መሠረታዊ ሰብዐዊ መብቶችን የሚያከብር እና የሚያስከብር ነው፣ ይህም በተመሳሳይ የጋራ ግዴታዎችን፣ በአሁኑ እና በመጪው ትውልድ መካከል የመተማመን እና የአመስጋኝነት ባሕሪን በመፍጠር ትስስር እንዲኖር ያደርጋል።
4. የፖለቲካ መጥፎ ምግባሮች
ፖለቲካ መልካም የሚባሉ በጎ ባሕርያት ቢኖሩትም በሚያሳዝን መልኩ ደግሞ በግል ብቃት ማነስ ወይም በስርዓቱ ውስጥ ባሉ ድክመቶች የተነሳ ፖለቲካ መጥፎ የሚባሉ ምግባሮችም አለት። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ የሰነ-ምግባር ጉድለቶች እና ጥፋቶች በአጠቃላይ የፖለቲካ ህይወት ተአማኒነት ላይ እንዲሁም በተቋሙ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ባለስልጣኖች የሚያደርጉትን ውሳኔዎች እና የሚወስዱትን እርምጃዎች ይረብሻሉ። እነዚህ የስነ-ምግባር ጉድለቶች የአንድ እውነተኛ ዲሞክራሲን መልካምነት የሚያበላሹ እና በሕዝብ ሕይወት ላይ ውርደት የሚያስከትሉ፣ ማህበራዊ ስምምነትን የሚያፈርሱ ናቸው። በዚህም የተነሳ በተለያየ መልኩ የሚፈጸሙትን ብዝበዛዎች እመለከታለን፣ የመንግሥት ሀብቶች መሰወር፣ የግለሰቦች መበዝበዝ፣ ሰብዓዊ መብትን መነፈግ፣ የማሕበራዊ ሕጎች ጥሰት፣ የሐቀኝነት መንፈስ መጥፋት፣ የግል ጥቅምን ማሳደድ፣ ኃይልን በመጠቀም ስልጣንን ማረጋገጥ፣ ወይም ከአግባብ ውጪ ጥቅም ለማግኘት ኃይልን መጠቀም፣ ስልጣንን የሙጥኝ ይዞ አለቅም ማለትን ያስከትላሉ። በተጨማሪም ደግም የባዕድ ሀገር ሰዎችን መጥላት፣ ዘረኝነት፣ ለተፈጥሮ እና ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት አለመስጠት፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን ከልክ በላይ መበዝበዝ፣ ፈጣን የሆነ ትርፍ ለማጋበስ ብቻ መሥራት እና በግዞት ለተገደሉ ሰዎች ንቀት ማሳየት . . . ወዘተ የሚሉትንም ምግባረ ብልሹ ባሕሪያትን ማካተት እንችላለን።
5. ወጣቶችን የሚያሳትፍ እና በሌሎች ላይ እምነት የሚጥል ፖለቲካ መልካም የሆነ ፖለቲካ ነው !
የፖለቲካ ስልጣን በጣም ጥቂት የሚባሉ ግለሰቦችን ጥቅማጥቅሞች እና ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ ብቻ ሲተገበር፣ የወደፊቱ ጊዜ እክል ይገጥመዋል፣ ወጣቱ ትውልድ በራስ የመተማመን ስሜቱ እንዲቀንስ ያደርጋል፣ ወጣቶች ለመጪው ማኅበርሰብ ማበርከት የሚችሉትን መልካም የሆነ አስተዋጾ እንዲቀንስ ያደርጋል። ነገር ግን ፖለቲካ የወጣቶችን ችሎታ እና ምኞት በተግባር ማስቀጠል ከቻለ ሰላም በወጣቶች አስተሳሰብ እና በፊት ገጽታቸውም ላይ ሳይቀር እየጨመረ ይሄዳል። ይህ ደግሞ በተግባር ላይ ከዋለ “እኔ በእናንተ እተማመናለሁ፣ እናንተንም አምናችኋለሁ በዚህም ምክንያት የጋራ ጥቃማችንን ለማስጠበቅ አብረን መሥራት እንችላለን” የሚል የመተማመኛ ድምጽ ማግኘት ይችላሉ። ፖለቲካ ለእያንዳንዱ ግለሰብ ስጦታዎች እና ችሎታዎች እውቅና ሲሰጥ ለሰላም አገልግሎት ዋለ ማለት እንችላለን። “ከተዘረጋ እጅ የተሻለ ምን ሊኖር ይችላል?” እርሱም ለመስጠት እና ለመቀበል የተዘረጋውን የእግዚኣብሔር እጅ ይመስላል። እግዚኣብሔር ማንንም ለመግደል በፍጹም አይፈልግም፣ በሰዎች ላይ ችግሮችን ለመጫን አይፈልግም፣ ነገር ግን ለሰዎች እንክብካቤን፣ ለሕይወታቸውም ጥንቃቄን ያደርጋል። ልባችንን ከአእምሮዋችን ጋር አስተባብረን በመጠቀም የውይይት መድረኮችን መክፈት እንችላለን።
እያንዳንዱ ሰው የጋራ የሆነውን ቤታችንን ለመገንባት የራሱን ድንጋይ ልያስቀምጥ ይችላል። እውነተኛ የፖለቲካ ሕይወት በሕግ የተደገፈ እና በግለሰቦች መካከል ግልጽ እና ፍትሃዊ ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርግ ሲሆን በተቻለ መጠን በእውነት ላይ የተመሰረተ አዲስ ግንኙነት፣ አእምሮአዊ፣ ባህላዊ እና መንፈሳዊ ኃይል እንዲመጣ መተማመን እና መተሳሰብን መፍጠር ይመለከታል። እንዲህ ዓይነቱን መተማመኛ ማግኘት ፈጽሞ ቀላል አይደለም፣ ምክንያቱም ከሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት በጣም የተወሳሰበ ስለሆነ፣ በተለይም በእኛ ዘመን ውስጥ የምናውቃቸውን ሰዎች ሆነ ሌሎች የማናውቃቸውን ሰዎች አለማመን ወይም ስለግለሰባዊ ደኅንነታችን ስጋት ስለሚገባን በዚህ ሁኔታ መተማመንን መፍጠር አስቸጋሪ በመሆኑ የተነሳ ነው። የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ በፖለቲካ ደረጃ በሚፈጠረው ከፍተኛ የሆነ ብሔራዊ ስሜት (Nationalism) የተነሳ ዓለም አቀፋዊው የወንድማማችነት መንፈስ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸረሸረ መምጣቱ እና በተጨማሪም ይህ አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ በፖለቲካ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔት መታየቱ ያሳዝናል። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ማኅበረሰባችን ለሰብዐዊ ቤተሰብ በጎነት እና ደስታ በትጋት የሚሠሩ የእግዚአብሔር መልእክቶች እና እውነተኛ ምስክሮች የሆኑ “የሰላም መሳርያ” የሆኑ ሰዎች ያስፈልጓታል።
6. ፍርሃትን እና ጦርነትን የሚፈጥሩ እቅዶችን መቃወም
የመጀመርያው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ በእነዚህ ጦርነቶች ምክንያት የተገደሉትን ወጣቶች እና ተበታትነው የቀሩትን የሲቪል ማኅበረሰቦች በማሰብ አስከፊ የሆኑ ጦርነቶች ከሚነገረው በላይ የምያስከትሉትን አሰቃቂ ሁኔታዎች ትምህርት በመቅሰም በኃይል እና በፍርሃት መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ እንዳለብን ተምረናል። ሌሎችን ማስፈራራት ማለት ሰዎችን ዝቅ አድርጎ መመልከት እና ሰብዐዊ መብታቸውን መግፈፍ ማለት ነው። ለዚህም ነው ታዲያ ማስፈራራት እና የጦር መሳሪያዎችን ለመታጠቅ የሚደርገው ሩጫ ከሥነ ምግባር እና እውነተኛ ሰላም ከመፈለግ ጋር ተቃራኒ ነው የምንለው በዚሁ ምክንያት ነው። ፍርሃትን ተጋላጭ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ መንዛት፣ ይህ ተጋላጭ ማኅበርሰብ ሰላምን ፍለጋ እንዲሰደድ ያደርገዋል። በስደት ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ እንደ ክፉ የሚቆጥር እና ተስፋቸውን የሚነጥቁ የፖለቲካ መልእክቶች በፍጹም ተቀባይነት የላቸውም። ይልቁንም ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው ለእያንዳንዱ ሰው ክብር ስንሰጥ ብቻ ነው፣ የእርሱ ወይም የእርሷ ስር መሰረት የትም ይሁን የት፣ ሕግን እና የጋራ ጥቅምን ማስከበር፣ ለእኛ በአደራ የተሰጠንን የተፈጥሮ ስነ-ምዕዳር መንከባከብ እና መልካም የሚባሉ ስነ-ምግባራዊ እሴቶችን የመንካባከብ ባህል ከባለፈው ትውልድ የወሰድነው ልምድ ነው።
በአሁኑ ወቅት በተለይም ደግሞ በጦርነት ቀጠናዎች ውስጥ የሚኖሩ ሕጻናት፣ የእነዚህን ሕጻናት ነፍስ ለመታደግ እና መብታችውን ለማስከበር በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ሰዎችን በተለየ ሁኔታ እናስባቸዋለን። ምንም እንኳን ሕጻናት በውትድርና ተግባር ውስጥ ባይሳተፉም ወይም በታጠቁ ቡድኖች ታግቶ የተያዙ ባይሆንም በዓለም ውስጥ ከሚገኙ ከስድስት ልጆች አንዱ በጦርነት ወይም ጦርነት በሚያስከትለው አሉታዊ ውጤቶች የተነሳ ተጽኖ ይደርስበታል። ሕጻናትን በሚንከባከቡ እና መብታቸውን ለማስከበር በሚተጉ ሰዎች የሚሰጠው ምስክርነት ለመጪው ትውልድ በጣም ውድ እና የከበረ ምስክርነት ነው።
7. ታላቅ የሰላም እቅድ
በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ የሰብዐዊ መብቶች ሕግ ከተደነገገ ሰባኛ አመቱን በምናከብርበት እና የመጀመርያው የዓለም ጦርነት የተጠናቀቀበትን 100ኛ አመት በመዘከር ላይ እንገኛለን። በእዚህ ረገድ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛን ግምገማ እንመልከት፦ “የሰው ልጅ ስለ መብቱ ያለው ግንዛቤ ግዴታውንም ጭምር እንዲገነዘብ ያስችለው ዘንድ ሊገፋፋው ይገባል። የመብቱ ባለቤት መሆኑ ደግሞ እዚህን መብቶች ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ማወቅን ያጠቃልላል፣ ምክንያቱም የአንድ ሰው ግላዊ ሰብዐዊ ክብር መገለጫ ናቸውና። እንዲሁም የመብቱ ባለቤት መሆን ለሌሎች ሰዎች መብት እውቅናና አክብሮት መስጠትን ይጨምራል” ማለታቸው ይታወሳል።
ሰላም ማለት የሰው ልጆች የጋራ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትና የሰው ልጆች እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉበት የትልቅ ፖለቲካ እቅድ ውጤት ነው። ነገር ግን በየጊዜው እንደገና በአዲስ መልክ መታደስ እንዳለበት ጥያቄ የሚያቀርብ ተግዳሮት ነው። ይህም የልብና የነፍስ ለውጥን ያካትታል፣ ይዘቱም ውስጣዊ እና ማህበረሰባዊ ነው፣ እንዲሁም ሦስት የማይነጣጠሉ ገጽታዎች አሉት፡

 ውስጣዊ የሆነ የግል ሰላም፦ ግትር የመሆን፣ መቆጣትና ትዕግስት የማጣት ባሕሪያትን በፍጹም አይቀበልም፣ ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ደ ሳላስ እንደ ሚለው "ለሌሎች ሰዎች ትንሽዬ የሆነች ጥፍጥናን ለመስጠት እንችል ዘንድ እኛ ራሳችን በቅድሚያ ትንሽዬ ጥፍጥና ሊኖረን ይገባል” ማለቱ ይታወሳል።
 ከሌሎች ጋር ያለን ሰላም፦ ከቤተሰብ አባላት፣ ከጓደኞች፣ ከሌላ ሀገር ሰዎች፣ ከድሆች እና በመከራ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች . . .ወዘተ እነዚህን ሰዎች ያለምንም ፍርሃት ለመገናኘት እና እነርሱ የሚናገሩትን ነገር ለማዳመጥ ዝግጁ መሆንን ያካትታል።
 ከፍጥረታት ሁሉ ጋር ሰላም መፍጠር፦ የእግዚአብሔርን ስጦታ ታላቅ መሆኑን በማየት እውቅና መስጠት፣ በዚህ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች፣ ዜጎች በሙሉ የመጭውን ጊዜ የመገንባት የጋራ ኃላፊነት እንዳለን ማወቅን ያካትታል።

ለሁሉም በተለይም ደግሞ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ትኩረት የሚሰጥ እና በጥልቀት የሚያስብ የሰላም ፖለቲካ የክርስቶስ እናት እና የሰላም ንግሥት የሆነችው ማርያም በመላው የሰው ልጅ ስም ካቀረበችው “እግዚኣብሔር ለሚፈሩት ሰዎች ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ ምሕረቱን ያደርጋል፣ በብርቱ ክንዱ ኃይሉን አሳይቶአል፣ ትዕቢተኞችንም ከነሐሳባቸው በትኖአቸዋል፣ ታላላቅ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዱዋቸዋል፣ ዝቅተኞችን ግን በክብር ከፍ አድርጎዋቸዋል። የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ያሳየውን ምሕረት በማስታወስ አገልጋዩን እስራኤልን ረድቶታል” (ሉቃስ 1፡50-55) በማለት ካቀረበችው የምስጋና መዝሙር የመነጨ ነው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ
ከቫቲካን
ኅዳር 29/2011 ዓ.ም

 

03 January 2019, 11:42