ፈልግ

ለክርስቲያኖች ሕብረት የተደረገ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ለክርስቲያኖች ሕብረት የተደረገ የጸሎት ሥነ ሥርዓት 

ለክርስቲያኖች ሕብረት የታሰበ የጸሎት ሳምንት ተጀመረ።

የክርስቲያኖች አንድነት ምርጫ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዋና ዓላማውም ለእውነተኛ ፍትህ ብለን የምናደርገው የጋራ ጥረት ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ጥር 10 ቀን 2011 ዓ. ም. ለክርስቲያኖች ሕብረት የታሰበ የጸሎት ሳምንት፣ በሮም ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ ማስጀመራቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ከሰዓት በኋላ፣ በ11 ሰዓት ተኩል ላይ ባስጀመሩት የክርስቲያኖች ሕብረት የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሳሰቡት ለክርስቲያኖች አንድነት ጸሎት በሚቀርብበት ጊዜ እውነተኞችና ትክክለኞች መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

በዘንድሮ የጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ. ም. ለ52ኛ ጊዜ ለሚካሄድ የክርስቲያኖች ሕብረት ተብሎ የሚቀርብ የጸሎት ዝግጅት በዋናነት ያቀረቡት በኢንዶኔዢያ የሚገኙ ክርስቲያኖች መሆናቸው ታውቋል። 265 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ኢንዶኔዢያ፣ 86 ከመቶ የእስልምና እምነት ተከታይ መሆኑ ሲነገር 10 ከመቶ ደግሞ ክርስቲያኖችና ባሕላዊ እምነት ተከታዮች መሆናቸው ታውቋል። በቫቲካን የክርስቲያኖችን ሕብረት አስተባባሪና ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ያስነበበው ጽሑፍ እንዳብራራው በኢንዶኔዢያ ውስጥ የተስፋፋው የሙስና ወንጀል የፖለቲካ ሥርዓትንና የውጭ ግንኙነትን እጅግ እንዳዳከመው፣ ይህም ተመልሶ ለአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ የሚሰጠውን ትኩረት በጣም ዝቅተኛ እንዲሆን ከማድረጉ በላይ፣ ፍትሐዊ ሥርዓትን የማስፈን እና ሕግን የማስከበር ተግባርን እንዲዳከም ማድረጉን ገልጿል። ብዙን ጊዜ ፍትህን ለማምጣት፣ ደሃና አቅመ ደካማ የሆኑትን የማህበረሰብ ክፍል ለማገዝ አደራ የተሰጣቸው ባለስልጣናት ግዴታቸውን በትክክል አለመወጣታቸው፣ በደሃ እና በሃብታም መካከል ያለውን ልዩነት ከፍ እንዳደረገው፣ ኢንዶኔዢያ በተፈጥሮ ሃብት የከበረች ብትሆንም ሕዝቦቿ ለድህነት ሕይወት ተዳርጎ እንደሚኖሩ፣ የክርስቲያኖችን አንድነት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስረድቷል።

በእርግጥ ትክክለኛ መሆን ያስፈልጋል፣

“አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ በአገርህ ደጅ ሁሉ በየነገዶችህ ፈራጆችንና አለቆችን ሹም፤ ለሕዝቡም ቅን ፍርድ ይፍረዱ። ፍርድን አታጣምም፤ ፊት አይተህም አታድላ፤ ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል። በሕይወት ትኖር ዘንድ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም የሚሰጥህን ምድር ትወርስ ዘንድ እውነተኛውን ፍርድ ተከተል” የሚለውን ከ(ኦሪት ዘዳግም 16: 18-20)ላይ በመጥቀስ የኢንዶኔዢያ ክርስቲያኖች የኑሮአቸውን ሁኔታ ዞር ብለው እንዲመለከቱት፣ የሚገኙበትንም የኑሮ ደርጃ ተረድተው የጋራ ትኩረትን በመስጠት፣ በአገሪቱ ለሚታየው ኢፍትሃዊ ሥርዓት የጋራ መፍትሄን ለማፈላለግ ይረዳል ብለዋል። የኢንዶኔዢያ ክርስቲያኖች ሕብረት በማከልም፣ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ስንገኝ፣ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን የሚፈጸምብንን በደልና የፍትህ መዛባት ማጤን ያስፈልጋል ብለዋል። የኢንዶኔዢያ ክርስቲያኖች በጋራ ሆነው ባወጡት የጸሎት ሃሳብ እንደገለጹት፣ ለአገራችን፣ ለሕዝባችን መልካም እንዲመጣ ማድረግ የሚቻለው የኢየሱስ ክርስቶስን ጸሎት በማዳመጥ ነው በማለት በ(ዮሐ. 17,21) ላይ “እኔም የምለምነው ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፣ እንዲሁም አባት ሆይ አንተ በእኔ እንዳለህ እኔም ባንተ እንዳለሁ እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው፣ አንተ እንደላክሄኝም ዓለም እንዲያምን ነው” የሚለውን በመጥቀስ በክርስቲያኖች መካከል ያለውን ሕብረት በተግባር መመስከር እንደሚያስፈልግ አስረድተው በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን አንድነት አማካይነት በአገሪቱ ሕዝቦች ላይ የሚፈጸመውን የፍትህ መጓደል መዋጋት እንችላለን ብለዋል።

ለጸሎት ተጠርተናል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው ረቡዕ ዕለት ሳምንታዊውን የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት እንዳስገነዘቡት፣ የመላው ዓለም ክርስቲያኖች የአንድ ቤተሰብ ልጆች እንዲሆኑ የጋራ ጸሎት ለማቅረብ ተጠርተናል ብለው ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ(ዮሐ. 17:21) “እኔም የምለምነው ሁሉም አንድ እንዲሆኑ” ያለውን በመጥቀስ መናገራቸው ይታወሳል። የክርስቲያኖች አንድነት ምርጫ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዋና ዓላማውም ለእውነተኛ ፍትህ ብለን የምናደርገው የጋራ ጥረት እንዲያድግ፣ በማሕበረሰቡ ውስጥ ለተጎሳቆሉት፣ ለደሄዩት፣ ለደከሙት እና ለተጨቆኑ ፍትህ እንዲወርድላቸው ተገቢውን መልስ ለማግኘት እንደሆነ አስረድተዋል።                           

19 January 2019, 17:04