ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በአምላክ ማመን ከመለያየት ይልቅ ኅብረትን ይፈጥራል” አሉ!

“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል በቅርቡ የተባበሩት የአረብ ኤምሬትስ አገር በሆነችው በአቡዳቢ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የሐይማኖት መሪዎች ስብሰባ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ ስብሰባ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ተሳታፊ እንደ ሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን እርሳቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ በስድስት አመታት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው 27ኛ የሆነውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ አቡዳቢ እንደ ሚጓዙ ለቅዱስነታቸው ከወጣው የጉዞ መርዐግብር ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በዚሁ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል በአቡዳቢ በሚካሄደው የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ስብስባ ላይ ለመካፈል ከመሄዳቸው በፊት እንደ ተለመደው ቅዱስነታቸው ማነኛውንም ሐዋሪያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው በፊት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አስመልክተው የቪዲዮ መልእክት እንደ ሚያስተላልፉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም መሰረት በዛሬው እለት ማለትም በጥር 23/2011 ዓ.ም በሚቀጥለው እሁድ ጥር 26/2011 ዓ.ም በአቡዳቢ የሚያደርጉትን 27ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት አስመልክተው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “በእግዚኣብሔር ያለን እምነት ኅበረት እንዲኖረን ያደርጋል እንጂ አይከፋፍለንም” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅርቡ በአቡዳቢ የሚያደርጉትን 27ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት አስመልክተው በቪዲዮ ያስተላለፉትን መልእክት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል ተከታተሉን።

አሳላም አሌኩም /ሰላም ለእናንተ ይሁን!

አብሮ በሰላም የመኖር እና የሰብዓዊ ወንድማማችነት ተምሳሌት የሆነችውን፣ የተለያዩ ስልጣኔዎችና ባህሎች መገናኛ የሆነችውን፣ ብዙዎች አስተማማኝ የሆነ የሥራ እንድል የሚያገኙባት እና በነጻነት የሚኖሩባት፣ ለሕብረ ብሔራዊነት ስብጥር ከፍተኛ የሆነ ክብር የምትሰጠውን አገራችሁን ከጥቂት ቀናት በኋላ ለመጎብኘት በመምጣቴ ደስታ ይሰማኛል።

የወደፊቱን በዓይነ ሕሊናው እየተመለከተ ዛሬን የሚኖር ሕዝብ ለመገናኘት ወደ እዚያው ለመሄደ በመዘጋጀቴ ደስታ ይሰማኛል። የተባበሩት አረብ ሄምሬትስ አገር መሥራች የነበሩት ሼክ ዛይድ ጥለውልን ካለፉ "የተከበሩ ትዝታዎች" መካከል “እውነተኛ ሀብት የሚገለጸው ቁሳዊ በሆኑ ሐብቶች አማካይነት ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን የአገሪቱ እውነተኛ ሃብት የሚገኘው የአገራቸውን መጪ ጊዜ በሚገነቡ ሕዝቦች አማካይነት ነው […] ሰዎች እውነተኛ ሃብቶች ናቸው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

"ሰብዐዊው ወንድማማችነት" በሚል መሪ ሐሳብ በሚካሄደው የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ስብሰባ እንድሳተፍ የጋበዙኝን ክቡር ሼክ መሀመድ ቢን ዘይይድ ቢን ሱልጣን አል ናሃይንን ከልብ አመሰግናለሁ። በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ውስጥ ላሉት ሌሎች ባለሥልጣናት ለጋስ እና እንግዳ ተቀባይ በመሆናቸው፣ ይህ ስብሰባ ይሳካ ዘንድ በወንድማማችነት መንፈስ የተሞላ ከፍተኛ አስተዋጾ በማድረጋቸው የተሰማኝን ደስታ በመግለጽ ምስጋናዬን አቀረባለሁ።

ጓደኛዬ የሆኑት የአል-ዓዛሃር ታላቁ ኢማም የሆኑት ዶ/ር አህመድ አል-ታይብን እና ይህ ስብሰባ እውን ይሆን ዘንድ በመተባበር ያዘጋጁትን፣ ይህ ተግባራቸው፣ ፈቃደኝነታቸው፣ ብርታታቸው በአንዱ በእግዚኣብሔር ላይ ያለን እምነት፣ ልዩነታችንን እንድናጠብ እንደ ሚያደርግ፣ የጠላትነት እና የጥላቻ መንፈስን በማራቅ ኅብረት መፍጠር እንደ ምንችል ያሳየ ማረጋገጫ ነው።

በዚህ አጋጣሚ የእናንተ ተወዳጅ የሆነችው አገራችሁ የተለያየ ሐይማኖት ተከታዮች የሆንን እኛ ሁላችን ወንድማማቾች መሆናችንን በማረጋገጥ በሃይማኖት ተቋማት መካከል ግንኙነት እንዲፈጠር በማድረግ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲከፈት በማድረጋችሁ የተነሳ እና እኔም በዚህ የተነሳ ለዚህ ታሪካዊ ጉብኝት የሚሆን መልእክት ማስተላለፍ በመቻሌና ጌታ ይህንን አጋጣሚ ስለሰጠኝ በጣም ደስ ብሎኛል።

በደስታ እናንተን ለመገናኘት እያሰብኩኝ ሰላምታዬን እያቀረብኩኝ የእናንተ የብልጽግና እና የሰላም መሬት፣ ፀሐያማና ተስማሚ የሆነ መሬት፣  አብሮ የመኖር ተምሳሌት እና የግንኙነት ባሕል ላለው አገራችሁ ሰላምን እመኛለሁ።

በቅርቡ እስከምንገናኝ ሰላም ቆዩን፣ ለእኔ ጸልዩልኝ!

31 January 2019, 14:15