ፈልግ

ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ዋዜማ ዕለት የጸሎት ሥነ ሥርዓት ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ዋዜማ ዕለት የጸሎት ሥነ ሥርዓት 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን ለማለት ተዘጋጅታችኋል”?

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓናማ 34ኛውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል፣ በመቶ ሽህዎች  ከሚቆጠሩ፣ ከአምስቱም አህጉራት ከመጡት ወጣቶች ጋር በማክበር ላይ መሆናቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በፓናማ ቆይታቸው ለተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ በፓናማ እና በላቲን አሜርካ አገሮች የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያ ብጹዓን ጳጳሳትና መንፈሳዊ ተቋማት መሪዎች ሰፊ መልዕክት  ሲያስተላልፉ ቆይተዋል። ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ዋዜማ ዕለት በሆነው ቅዳሜ ጥር 18 ቀን 2011 በመቶ ሺህ ዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ያደረጉትን ንግግር ትርጉም እንደሚከተለው ቀርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወጣቶች እንደ ምን ዋላችሁ!

ስለ “ሕይወት ዛፍ” የቀረበውን ትዕይንት ተመልክተናል። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠን ሕይወት፣ የፍቅር ታሪክ ያለበት መሆኑንና ከእኛ ሕይወት ጋር የተዛመደ እና በሕወታችን ውስጥ ሥር የሰደደ መሆኑን እንገነዘባለን። የምሕረት ሕይወት ታዲያ ዳመና ላይ ከፍ ብሎ የሚገኝ፣ ወደ መሬትም እንዲወርድ የምንጠብቀው ሕይወት አይደለም። በስልኮቻችን እንደምንጭነው ፕሮግራም አይደለም። እግዚአብሔር የሚሰጠን ምሕረት ከግል የሕይወት ታሪካችን ጋር የተገናኘ መሆን አለበት። የምሕረት ሕይወት በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን መካከል እንዲሁም በማንኛውም ሥፍራ ሆነን የምናሳየው የሕይወታችን አካሄድ የሚያስገኘው ውጤት ነው። ይህን የምሕረት ሕይወት እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንዲገባ ሲያደርግ እኛም ከእርሱ ተቀብለን ወደ ሌሎች ሕይወት ውስጥ እንዲገባ እናደርገዋልን። ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔር የእኛን የሕይወት አካሄድ በመቀበል፣ እኛም እርሱን እንድንቀበል ይፈልጋል።

እግዚአብሔርም ከሁሉ አስቀድሞ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያቀረበላት ጥያቄ የፍቅሩ ተካፋይ እንድትሆን የሚል ነው። በናዝሬት ከተማ ውስጥ የማርያምን ማህበራዊ ሕይወት ስንመልከተው በነዋሪዎች መካከል የምትታወቅ ሴት አልነበረችም። እርሷም ብትሆን በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ራሷን ከፍ የምታደርግ እና እውቅናን የምትፈልግ አልነበረችም። ነገር ግን በኋላ ማርያም በዘመናት ታሪክ ውስጥ እጅግ የምትታወቅ ሆና ተግኝታለች።

ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ለእግዚአብሔር በተናገረቻቸው ጥቂት ቃላት፣ ለጥሪው በሰጠችው አዎንታዊ መልሷ፣ ሁሉን ነገር ወደ መልካም ለመለውጥ ሃይል ባለው በእግዚአብሔር ፍቅር በመተማመኗ ምክንያት  በእግዚአብሔር የተመረጠችና በዓለም ሕዝቦች መካከልም ስሟ ከፍ ብሎ ተገኝቷል።

ለመልአኩ ገብርኤል በገለጸችላቸው አዎንታዊ መልሶቿ እና እንደ ቃልህ ይሁን በማለት የተናገረችው ስናስብ ሁል ጊዜ እንገረማለን። ይህን የተናገረችው በጥርጣሬ ተሞልታ እሞክረዋለሁ ወይም አየዋለሁ በሚል ሃሳብ ሳይሆን በድፍረት ተሞልታ፣ እንቅፋት ቢገጥማትም ለሚደርስባት ችግር በሙሉ ሃላፊነትን በመውሰድ፣ የገባችውን ቃል ኪዳን እስከ መጨረሻው ጠብቃ ለማቆየት ባላት ጽኑ አቋሟ ተነሳስታ ነበር። ይህ ውሳኔዋ ቀላል ባይሆንም ነገር ግን ወደ ፊት ከሚጠብቃት እና ከምታገኘው ታላቅ ዋጋ ስታወዳድረው አይሆንም ወይም አልችለውም የሚል መልስ እንድትሰጥ የሚያደርጋት አልነበረም። ነገሮች እንደሚወሳሰቡባት ግልጽ ቢሆንም ፍርሃት እንዲይዛት እና እንድትጠራጠር የሚያደርጋት አልነበረም። ለእግዚአብሔር ያሳየችው የእሽታ መልስ ከሚያጋጣሟት ውጣ ውረዶች እጅግ የበለጠ መሆኑን ከልብ ተገንዝባለች።

እኛም ዛሬ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእግዚአብሔር የሰጠችው የአዎንታ መልስ በእያንዳንዱ ትውልድ መካከል ምን ያህል ተሰራጭቶ እንደገባ እንመለከታለን። በርካታ ወጣቶች እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ቃል በመግባት ለወደ ፊት ሕይወታቸው ሃላፊነትን እንደወሰዱ ይታያል። ለዚህም ምስክር የሆኑትን ኤሪካንና ሮጄሊዮን ላመሰግናቸው እወዳለሁ። ምክንያቱም በጎደሎ ጤንነት የምትወለድ ልጃቸው ኢነስን ለመቀበል መወሰናችው የሚያስመሰግን ነው። ይህን ውሳኔ ከማድረጋችው በፊት በአእምሮአችው የሚመላለሱ አንዳንድ ጥያቄዎች አልታጡም ይሆናል። በማንም አእምሮ ሊመጣ የሚችልና ሁላችንም የምንረዳው ሃቅ ነው። አስገራሚው ነገር ግን ልጃቸው ስትወለድ፣ ሙሉ ፍቅርን በማሳየት ለማሳደግ መወሰናቸው ነው። ልጃቸው ከመወለዷ በፊት፣ ሁሉንም እንደ አመጣጡ እንወስደዋለን በማለት ያደረጋችሁ ቆራጥ ውሳኔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካደረገችው ውሳኔ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ለእግዚአብሔር የአዎንታ መልሽ መስጠት ማለት በሕይወት መካከል የሚያጋጥም ማንኛውም ነገር እንደ ፈቃዱ መሆኑን አምኖ ለመቀበል መዘጋጀትን ያመለክታል። ይህን ለማድረግ የኤሪካ እና የሮጄሊዮ ሙሉ ፍቅር የታየበት ቆራጥ ውሳኔ በቂ ምሳሌ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን በምንልበት ጊዜ ሌሎች በርካታ ነገሮችን ማስታወስ እንችላለን። ለምሳሌ የተወለድንበት አገር ደሃ ይሁን ሃብታም፣ ወላጆቻችን አቅመ ደካሞች ይሁኑ ብርቱዎች፣ ጓደኞቻችንም እንደዚሁ፣ ሁሉንም እንደ ሁኔታው መቀበል ማለት ነው። ሕይወትንም እንደ ሁኔታው መቀበል ማለት የተስተካከለ ሕይወትን ማግኘት ማለት ሳይሆን ምንም ይሁን ምን ከእውነተኛ ፍቅር አይበልጥም ማለታችን ነው። የሰው ልጅ ሕመምተኛ ወይም አካለ ጎደሎ ቢሆን ለዚያ ሰው ፍቅርን ማሳየት አያስፈልግም ማለት አይደነለም። የማናውቀው የባዕድ ሰው ቢሆን፣ ወንጀለኛ ሰው ቢሆን፣ ወደ ወሕኒ የተጣለ ቢሆን፣ ለእነዚህ በሙሉ ፍቅርን መግለጽ ያስፈልጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለምጻሙን፣ ዕዓይነ ስውሩን፣ ሽባውን፣ ፈሪሳዊውን እና ኃጢአተኛውን፣ እንዲሰቀል የተፈረደበትንም ሌባ፣ ሌላው ቀርቶ እርሱን በመስቀል ላይ የቸነከሩትንም ሳይቀር ተቀብሎአቸዋል።

ይህን ያደረገበት ምክንያት ለምን ይመስላችኋል? ምክንያቱም ፍቅር የተቸረለት በሙሉ ድነትን ስለሚያገኝ ነው። ፍቅር የተቸረለት ሁሉ ይለወጣልና። የእግዚአብሔር ፍቅር ደግሞ ከችግሮቻችን ከድክመቶቻችን እና ከጉድለቶቻችን ይበልጣል። እግዚአብሔር ድክመቶቻችንን እና ስህተቶቻችንን እየተመለከተ ፍቅሩን ሊገልጽልን ወዷል። አባካኙን ልጅ አቅፎታል፣ ጴጥሮስን ከክህደቱ በኋላ ተቀብሎታል፣ ዘወትር በሐጢአት ብንወድቅም አንስቶን እና አስታጥቆን በእግራችን እንድንቆም ያደርገናል። ወድቀን እንድንቀር፣ ከውድቀታችን እንድንነሳ ለሚያደርጉን ሰዎች ፈቃደኞች አለመሆን በራሱ ትልቅ ውድቀት ነው።

የእግዚአብሔርን ፍቅር ለይቶ ማወቅ ከባድ ቢሆንም ድክመታችንን፣ ውድቀታንን፣ ስህተታችንን ሁሉ እየተመለከተ ይቅር የሚል፣ እውነተኛ ፍቅሩን የሚገልጽ አባት መኖራችን ከስጦታዎች ሁሉ በላይ ስጦታ  ነው። ስለዚህ የመጀመሪያው እርምጃ ፍርሃትን አስወግደን ማንኛውንም ሕይወት በምስጋና ተቀብሎ ማስተናገድ ነው።

አልፍሬዶ የሕይወት ታሪኩን ነግሮናል፣ ለሰጠሄንም ምስክርነት አመሰግነዋለሁ። በሕንጻ ሥራ ድርጅት ውስጥ ስሰራ ነበር፣ ነገር ግን ሥራው ሲጠናቀቅ ሥራ ፈታሁ፣ ነገሮች በሙሉ በቅጽበት ተቀየሩብኝ ብሎ በነገረን ታሪክ ልቤ ተነክቷል። ያለ ትምህርት፣ ያለ ንግድ፣ ያለ ሥራ ያልከንን በመውሰድ፣ ሕይወታችንን ያለ ትርጉም ሊያስቀሩ የሚችሉ አራት ነገሮችን መመልከት እፈልጋለሁ። በእርግጥ በሕይወታችን ውስጥ አንድ አስተማማኝ ነገር ከሌለ ማደግ መበልጸግ አስቸጋሪ ነው። ደጋፊ ከሌለን በቀላሉ ተንሸራትተን እነውድቃለን። እኛ የዕድሜ ባለ ጸጋ የሆንን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን አንድ ነገር አለ። እናንተም ብትሆኑ እኛን ልትጠይቁን የሚገባ አንድ ጥያቄ አለ። ይህም እንደ ሰው እንድታድጉ ምን መሠረት ጥለንላችኋል? ምንስ አድርገንላችኋል? ምንም ዓይነት የሥራ፣ የትምህርት እና ሌሎችንም ማሕበራዊ እድሎችን ሳናመቻችላችው ቀርተን ነገር ግን ወጣቶች እንዲህ ናቸው በማለት መተቸት በጣም ቀላል ነው። እንደሚታወቀው አንድ ሰው የወደ ፊት ሕይወቱን ለማስተካከል በትምህርት ራሱን ማዘጋጀት እጅግ አስፈላጊ ነው። ያለ ሥራ ስለ ወደ ፊት ሕይወት ማለም አስቸጋሪ ነው። ያለ ቤተሰብ እና ያለ ማሕበረሰብ ስለ ወደ ፊት ማሕበራዊ ሕይወት ማለም ፈጽሞ አይቻልም። ስለ ወደ ፊት ሕይወት ማለም ማለት ለምን እኖራለሁ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብቻ ሳይሆን እኔስ ማን ነኝ? የሚለውንም ጥያቄ ለመመለስ ያግዛል። ይህ ብቻ ሳይሆን የማልመውንና የምመኘውን ሕይወት ለመኖር የሚያግዘኝ ማነው? የሚለውንም ጥያቄ ለመመለስ ያግዛል። አልፍሬዶ እነዚህን ነገሮች አስመልክቶ፣ ያለ ሥራ፣ ያለ ትምህርት፣ ያለ ቤተሰብ እና ያለ ማሕበረሰብ ስንቀር ባዶነት እንደሚሰማን ገልጾልናል። ለአመጽ ወይስ ለፍቅር እንደምንኖር ለይተን ማወቅ ያዳግተናልና።

ከአንድ ወጣት የቀረበልኝ ጥያቄ እንዲህ የሚል ነበር። ለምንድር ነው ብዙ ወጣቶች ዛሬ ስለ እግዚአብሔር መኖር ወይም አለመኖር ደንታ የሌላቸው? ወይም በእርሱ ለማመን የሚቸገሩት? የሕይወታቸውንም ትርጉም ያጡት? የሚል ነበር። እኔም መልሼ፣ እናንተስ ምን ታስባላችሁ? አልኳቸው። ከእነርሱ የተሰጠኝ መልስ የሚገርም ነበር። “ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት በሕይወት የሚኖሩት ለራሳቸው ብቻ እንጂ ለሌሎች መሆኑን ስላልተገነዘቡት ቀስ በቀስ ማንነታቸው ተሸርሽሮ በመጥፋቱ ነው” አሉ። ይህ ነው የዘመናችን ባሕል፣ ለሌሎች ያለን ፍቅር እና ግንዛቤ በጠፋበት ዘመን ላይ እንገኛለን። 

ሁሉም ባይሆን በርካታ ሰዎች በማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ እንዲሳተፉ ጥያቄ ስለማይቀርብላቸው፣ ለሌሎች ሊያበረክቱ የሚችሉት ነገር የለኝም ስለሚሉ ወይም ቢኖራቸውም በጣም ጥቂት ነው ብለው ያስባሉ። በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ይህን የመሰለ ከሆነ የእግዚአብሔርን መኖር እንዴት ሊረዱ እና ሊያውቁ ይችላሉ?

የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ! ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተን እንደሚወዳችሁ ካመናችሁ እናንተም የእርሱ ፍቅር ተካፋዮች መሆናችሁን አትዘንጉ፣ በፍቅሩ በመታገዝ ብዙ አስደናቂ ነገሮችን ለማከናወን መዘጋጀታችሁንም መርሳት የለባችሁም።

ኢየሱስ ክርስቶስን ፊት ለፊት በምታገኙበት ጊዜ እኔንም በጸሎታችሁ አስታውሱኝ። በጸሎታችሁ በመታገዝ እኔም እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ድፍረት ይኖረኛል”።                 

27 January 2019, 17:56