ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የመጪውን ጊዜ ተስፋችንን በድፍረት ለመገንባት ያለፈውን ጊዜ ማስታወስ ያስፈልጋል

ከጥር 14-19/2011 ዓ.ም “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ” (ሉቃ 1፡38) በሚል መሪ ቃል 34ኛው ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን በፓናማ እንደ ሚከበር ይታወቃል። በዚህ በፓናማ በሚካሄደው 34ኛው ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደ ሚገኙ መዘገባችን ይታወሳል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከዚህ በፓናማ ከሚካሄደው 34ኛው ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን በፊት ከጥር 09-13/2011 ዓ.ም ድረስ በፓናማ በሚገኘው በዳዊት ሀገረ ስብከት ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቀደምት ነዋሪዎች ዘር ተተኪ የሆኑ ወጣቶች ቀን ይሆን ዘንድ የቪዲዮ መልእክት ማስተላለፋቸውን ለመረዳት ተችሉዋል፣ ይህንን የቅዱስነታቸውን የቪዲዮ መልእክት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አስናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

ወድ ወጣቶች ከዚህ ቀደም እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2016 ዓ.ም በፖላንድ ዋና ከተማ በካርኮቪያ በተካሄደው ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን ማጠቃለያ ላይ በዚያ ለተገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስጪ ወጣቶች “የመጪውን ጊዜ ተስፋችንን በድፍረት ለመገንባት ያለፈውን ጊዜ ታሪክ ማስታወስ ይገባል” በማለት ተናግሬ ነበር። ይህም በዚህ ዓመት ከጥር 09-13/2011 ዓ.ም ድረስ በፓናማ በሚገኘው በዳዊት ሀገረ ስብከት ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቀደምት ነዋሪዎች ዘር ተተኪ የሆኑ ወጣቶች ቀን ይሆን ዘንድ የመረጥኩት መርሕ ሐሳብ ነው።
በተለይም ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለማቀፍ ደረጃ የቀደምት ነዋሪዎች ዘር ተተኪ የሆኑ ወጣቶች ዓለማቀፍ ቀን በማዘጋጀታችሁ የተነሳ የተሰማኝ ደስታ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ። ይህ በፓናማ በሚገኙ የብጽዕን ጳጳሳት ጉባሄ ተነሳሽነት የተዘጋጀ እና ለቀደምት ነዋሪዎች ዘር ተተኪ ሰዎች እየተደረገ የሚገኘውን ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚያሳይ ነው።
የተከበራችሁ ወጣቶች፦ የተለያዩ ሀገራት ተወላጅ የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀደምት ነዋሪዎች ዘር ተተኪ ወጣቶች ይህንን ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን በምታከብሩበት ወቅት የቀደምት ነዋሪዎች ዘር ተተኪ ወጣቶች በመሆናችሁ የተነሳ ከቀድሞዎቹ በርካታ የበለጸጉ ባህላዊ እሴቶቻችሁ በመነሳት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላችውን እምነት ማንጸባረቅ እንደ ሚኖርባችሁ ላሳስባችሁ እወዳለሁ። ቀደም ሲል በነበሩት ጊዜያት ለወጣቶች ለተላለፉት መልእክቶች ምላሽ እንዲድትሰጡ፣ እድሉንም እንድትጠቀሙ፣ የቀደምት ነዋሪዎች ዘር ተተኪ ወጣቶች በመሆናችሁ የተነሳ ለዚህ ለሕዝባቸው ታሪክ አድናቆት እንዲሰማችሁና በዙሪያችሁ ከቧችሁ የሚገኙትን ተግዳሮቶች በብርታት እንድትጋፈጡ፣ የተሻለ ዓለም ለመግንባት በተስፋ ተሞልታችሁ ወደ ፊት ትጓዙ ዘንድ ላሳስባችሁ እፈልጋለሁ።
ወደ ቀደምት ነዋሪዎች ዘር ባሕል ልውሰዳችሁ። ስር መሰረታችሁን በጥንቃቄ ጠብቁ፣ ምክንያቱም ስር መሰረታችሁ እንድታድጉ፣ እንድትበለጽጉ እና ፍሬያማ እንድትሆኑ ኃይል ይሰጣችኋል። በሌላ በኩል ደግሞ የቀደምት ነዋሪዎች ዘር ተተኪ የሆኑ ሰዎች የቤተ ክርስቲያናችሁን ሁኔታ በተለይም ደግሞ አሁን በሚከበረው ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ የእናንተን ቤተ ክርስቲያን ገጽታ በማንጸባረቅ የጋራ መኖሪያ ቤታችንን እንዴት መንከባከብ እና መጠበቅ እንደ ሚገባ በማሳየት፣ በተጨማሪም ይበልጥ ፍትሐዊ እና እጅግ ሰብዓዊ የሆነ አለም ለመገንባት ጥረት ይደረግ ዘንድ ግንዛቤ እንዲሰጥ ማድረግ ያስፈልጋል።
ውድ ወጣቶች ባህሎቻችሁን ተንከባከቡ። ሥር መሰረታችሁን ተንከባከቡ! በዚያም ሳታበቁ ከሥር መሰረታችሁ በመነሳት ማደግ፣ ማበብ እና ፍሬ ማፍራት ይኖርባችኋል። አንድ ገጣሚ የሆነ ሰው “አንድ ዛፍ ያፈራው ፍሬ ሁሉ የተገኘው ከመሬት ውስጥ ከሚያገኘው ነገሮች ነው” በማለት ይናገር ነበር። ሥር መሰረታችሁን ጠብቁ! በተጨማሪም ሥር መሰረቶቻችን የመጪውን ጊዜ ይወስናሉ። የወደፊቱን ነገር ይተነቢያሉ። ይህ ደግሞ እናንተን ዛሬ የሚገጥማች ተግዳሮት ነው።
በፓናማ እናንተን ለመገናኘት በመዘጋጀቴ ያስደስተኛል። ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደ ምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ፣ ሐዋርያዊ ቡራኬዬ ይድረሳችሁ።
እግዚኣብሔር ይባርካችሁ!

 

18 January 2019, 16:26