ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፓናማ ከዓለም ወጣቶች ጋር የመስቀል መንገድ ጸሎት አስተንትኖ አደረጉ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የምህረት አባት የሆንክ አምላክ ሆይ፣ በፓናማ የባሕር ዳርቻ ሆነን ዓለም አቀፍ በዓላቸውን ለማክበር ከመላው ዓለም ከመጡት ወጣቶች ጋር በሕብረት፣ ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያህል እንደሚወደንና ለሕይወታችንም እንደሚጨነቅልን የገለጸበትን የመስቀል መንገድ ሕማማት በማስታወስ ላይ እንገኛለን። 

ኢየሱስ ክርስቶስ የተጓዘበት መንገድ የስቃይ እና የብቸኝነት መገድ መሆኑ ዛሬ በዘመናችንም መታየቱን አላቋረጠም። የእርሱ የስቃይ ጉዞ ዛሬ በዘመናችን የሚደገመው በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለማስወገድ ካለመፈለግ የተነሳ በመሆኑ ነው።     

ጌታ ሆይ! እኛም ልጆችህ በዚህ ግድ የለሽነታችን በሐጢአት ውስጥ ወድቀናል፣ የተሳሳተ መንገድ መከተላችንም አስተዋይ ቢስ አድርጎናል። በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ስቃይ በመመልከት የአንተን ስቃይ መረዳት አቅቶናል። ስቃዮቻቸውን ላለማየት ፊታችንን አዙረናል፣ ችግሮቻቸውን ላለመስማት ጆሮአችንን ደፍነናል፣ ስለ ፍትህ ላለመናገር አፋችንን ዘግተናል። 

በመሆኑም ሁል ጊዜ በፈተና እንወድቃለን፣ በደስታ ጊዜ አብሮ መሆን፣ ከምናውቃቸው ጋር ሆነን አብሮ መደሰትና ጓደኝነትን ማሳደግ ይቀለናል።

በሌላ ወገን ተንኮልና ወንጀል መፈጸም፣ ሰዎችን ማስፈራራት የየዕለት ተግባራችን ሆኗል።

ጌታ ሆይ አንተ ግን በመስቀል ላይ ሆነህ ያሳየሄን አካሄድ፣ ከሚሰቃዩት ጋር ሆነህ ስቃያቸውን መካፈልን፣ ከተረሱት ጋር መሆንን ነው።

ጌታ ሆይ አንተ ግን፣ እኛ ንቀናቸው፣  የሚገባቸውን ፍቅር እና ምስጋና የነፈግናቸውን በሙሉ ወደ ራስህ ዘንድ እንዲቀርቡ አድርገሃቸዋል።

ጌታ ሆይ አንተ ግን፣ በመስቀልህ የእያንዳንዱን ወጣት ማንኛውንም ዓይነት ስቃይ በመሸከም ወደ ትንሳኤ እንዲለወጥ ማድረግን መርጠሃል።

አባት ሆይ! የልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ ዛሬም ቢሆን እየተደገመ፣ በጽንስ ደረጃ ላይ ያሉ ሕይወት ወደዚህች ዓለም እንዳይመጡ፣ ከተውለዱ በኋላም መብታቸውን እንዲያጡ በማድረግ፣ ካደጉ በኋላም ቤተሰብ የመመስረት መብታቸውን፣ የትምህርት እና የመልካም አስተዳደግ መብታቸውን፣ የመዝናኛንና ስለ ወደፊት ሕይወት ማለምንና ሌሎች በርካታ መብታቸውን ተነፍገው ይገኛሉ።

ለሴቶች ሊሰጥ የሚገባ እንክብካቤ ጎሏል፣ ተጨቁኗል፣ ለብቸኝነት ሕይወት ተዳርገዋል፣ ክብራቸውን ተነጠቀዋል። በትምህርት ማጣት፣ ሥራን ካለመያዝ ተስፋቸው በመጨለሙ በዚህ የተነሳ ሐዘናቸው ከፊታቸው ይነበባል።

አባት ሆይ ብዙ ወጣት ጓደኞቻችን፣ አንተን እናገለግላለን የሚሉትም ሳይቀሩ፣ ሕይወታቸው በጭቆና እና በወንጀል ወጥመድ ውስጥ ወድቋል።

አባት ሆይ! የልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ ዛሬም ቢሆን ቀጥሎ፣ በአደናዛዥ ዕጽ ተጠቃሚዎች፣ የአልኮል መጠጦችን በሚያዘወትሩት፣ በሴተኛ አዳሪነት ተግባር ላይ በተሰማሩት፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በተሰማሩት ሰዎች በኩል የበርካታ ወጣቶችና ቤተሰቦች ሕይወት ለሞት እየተዳረገ ይገኛል። እነዚህ ተግባራት የዛሬን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የወደ ፊት ሕይወታቸውንም አደጋ ላይ ጥሎባቸዋል። ልሶችህን ገፍፈውህ ዕጣ እንደተጣጣሉ እና እንደተከፋፈሉ ሁሉ የበርካታ ወጣቶችና ቤተሰቦች ሰብዓዊ ክብር ተወስዶባቸዋል።

አባት ሆይ! የልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ ዛሬም ቢሆን ቀጥሎ፣ በጎጂ አመል በተጠመዱ፣ አደንዛዥ ዕጽ በማዘዋወር ሕይወታቸውን ለማስተካከል፣ ለማቀድና ለማለም አቅምን ባጡ በርካታ ወጣቶች ዘንድ በገሃድ እየታየ ይገኛል።

የበርካታ ወጣቶችም ሕይወት፣ ከማሕበረሰቡ ሊደረግላቸውን የሚገባውን እገዛ በመነፈጋቸው፣ ከማሕበረሰቡ በመገለላቸው ምክንያት ለሃዘን በመዳረግ የችግሮች ሰለባ እና ተጠያቂም ሆነዋል።

አረጋዊያንም ያለ ረዳትና ጧሪ፣ ብቻቸው ቀርተው ተስፋ እንዲቆርጡ ማድረግ ቀጥሏል። ሌሎችም መሬታቸውን እንዲሰድባቸው ተደርጓል፣ ባሕላቸውንም እንዲረሱት ተደርጓል። ለማሕበረሰቡ የሚያበረክቱት ባሕላዊ እሴቶቻቸው እንዲረስ ተደርጓል።

አባት ሆይ! የልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ ዛሬም ቢሆን ቀጥሎ፣ ምድራችን በመርዛማ አየር በመበከሉ የተነሳ ዛፎችዋ ደርቀዋል፣ ውሃዎችዋም ቆሽሸዋል በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች ሰዎች ለመጠጥ የሚሆን ንጹሕ ውሃ እጦት እየተሰቃየ ይገኛል። በምድራችን የሕዝቦች ዋይታና ስቃይ ተበራክቶ ይገኛል።

አዎ አባት ሆይ፣ ዓለማችን በምትገኝበት አስቸጋሪ አጋጣሚዎች በሙሉ፣ ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ የስቃይ መስቀሉን ተሸክሞ በመጓዝ ላይ ይገኛል።

ታዲያ ጌታ ሆይ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

የኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ፣ ስደት፣ መፈናቀል በቀጠለበት በዚህ ዘመን፣ በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የሚደርሱትን የሞት፣ የስደት፣ የረሃብ እና የበሽታ ስቃይ እየተመለከትን እንዳልተመለከተ መሆን አለብን?

የምሕረት አባት ሆይ፣ በድሕነት ከሚሰቃዩት ጋር፣ ረዳት አጥተው ከሚጨነቁት ጋር፣ ከተረሱትም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር የልጅህን የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ በእውነት እየተጋራን እንገኛለን?

ቄረናዊው ስምዖን የልጅህን ከባድ መስቀል ተሸክሞ እንዳገዘው ሁሉ፣ እኛም የሰላም መሳሪያ በመሆን፣ የፍቅርና የወንድማማችነት ድልድይ በመገንባት፣ የሰዎችን የመከራና የስቃይ መስቀል ሸክም እንጋራቸዋለን?

እንደ እመ ቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምስቀል ሥር እንገኛለን? ብርቱ የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንመልከት። እንደ እርሷ ተስፋን ሳንቆርጥ፣ ጥርጣሬን አስወግደን፣ በጽኑ መንፈስ እመስቀል ሥር እንቁም። ጌታ ሆይ፣ ቅድስት ድንግል ማርያም የልጇንና የልጅህንም ስቃይ በመካፈል፣ በዓይኖችዋም እያገዘችው፣ በልቧም ተከላክለዋለች። ስቃዮችንም ብትጋራ ከበደኝ ከበደኝ አላለችም። በስቃይ የመስቀል መንገድ ወቅት ልጇን የረዳች፣ የተንከባከበች፣ ያቀፈች ብርቱ እናት ናት። የተስፋም እናት ናት። እኛ ዛሬ የተለያዩ የስቃይ ሕይወትን በመኖር የኢየሱስ ክርስቶስ የመከራና ስቃይ መስቀልን ተሸክመው ለሚጓዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አለኝታነታችንን በተግባር የምንገልጽ የቤተክርስቲያን ልጆች መሆን እንፈልጋለን።

ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትዕግስትን በመማር፣ ልጆቻቸው ችግር ላይ በወደቁ ጊዜ ተስፋን ሳይቆርጡ የዘወትር እገዛቸውንና ድጋፋቸውን ለሚሰጡት እናቶች፣ አባቶችና አያቶች በሙሉ የበኩላችንን እገዛ ልናደርግ የተዘጋጀን መሆን አለብን።

ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ኑሮ ለጨለመባቸው፣ የሕይወት ውጣ ውረድ ላጋጠማቸውና ተስፋን ለቆረጡት በሙሉ ተስፋ መሆንን፣ ከወደቁበት ችግር ውስጥ እንዲወጡ ማድረግን፣ መጠለያ ለሌላቸው መልካም የመኖሪያን ሥፍራ ማዘጋጀትን፣ ካለን ማካፈልን እንማራለን።

ባሕላቸው ሲናቅ፣ ጭቆናና ግፍ ሲደርስባቸው አቤት እንዳይሉ ድምጻቸው ለሚታፈንባችው ድማጻቸው በመሆን፣ ሰላማዊ አየርን እንዲተነፍሱ በማድረግ ከሚደርስባቸው ጥቃት በሙሉ የሚተርፉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ጥበብና ብርታት ከቅድስት ድንግል ማርያም እንማራለን።

ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ መጠጊያ የሌላቸውን፣ ከቄየያቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉትን፣ ከቤተሰብ የተነጠሉትንና ከሥራ ገበታ የተፈናቀሉትን ተቀብለን የምናስተናግድበትን ብርታት እንማራለን።

ጌታ ሆይ እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ስር መቆምን አስተምረን። ዓይናችንንና ልባችንን ክፈትልን። ከፍርሃት፣ ከጥርጣሬ እና ከችንቀት ሰውረን። ለልጅህ ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ለእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ጥሪ እንዲሁም በልባቸው መንግሥትህን ለሚሹት ደቀ መዛሙርትህ በሙሉ አለሁ ማለት ራሳችንን በደስታ እና በፍቅር የምናቀርብበትን ብርታት ስጠን፣ አሜን።

                       

26 January 2019, 10:38