ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓናማ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮችን ሲያመሰግኑ  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓናማ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮችን ሲያመሰግኑ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በፓናማ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩትን ወጣቶች በሙሉ አመሰገኑ።

የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ወጣቶች እምነታቸውን በተግባር እንደገለጹ፣ ከጸሎት የሚገኘውን ብርታት በተግባር የተመለከቱ መሆናቸውን፣ በዚህም ደስታን ማግኘታቸውን ገልጸው ይህ የሆነበት አንዱ መንገድ በሕብረት መንፈስ አብረው በመሥራታቸው ነው ብለዋል። ሌሎችም በርካታ ወጣቶች በእነዚህ ቀናት ውስጥ በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር ስለተከናወኑት ነግሮች ሊያውቁ ይገባል ብለው የተከናወኑ ሥራዎችን በሙሉ እግዚአብሔር ይባርክ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በመካከለኛዋ የላቲን አሜርካ አገር በሆነችው በፓናማ በተዘጋጀው 34ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ተገኝተው የበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸውን ሲያበርክቱ የሰነበቱትን ወጣቶች አመስግነዋል። ቅዱስነታቸው ለውጣቶቹ ባቀረቡት የምስጋና ንግግራቸው በኩል ከወጣቶቹ መካከል ምስክርነታቸውን የሰጡ ወጣቶችንም አመስግነዋቸዋል። ሰዎች በሕብረት ሆነው ሌሎችን ለመርዳት በሚነሱበት ጊዜ በመካከላቸው ሊመጣ የሚችለውን ወዳጅነት አስታውሰው በሕብረት በሚሆኑበት ጊዜ እምነትም ብርታትን ሊያገኝ እንደሚችል አስረድተዋል። የእምነት ብርታትን ከማግኘት በተጨማሪ ደስታም እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ወጣቶቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በሚያበረክቱበት ጊዜ በልባቸው የሚሰማውን ደስታ አስታውሰው ይህን ተልዕኮ እንዲያበረክቱ ያደረጋቸውም ሌላ ሳይሆን ለሌሎችን ለመርዳት ካላቸው የሕይወት ልምድ በመነሳሳት ነው ብለው የበጎ አገልግሎታቸውን ባበረከቱበት ወቅት አንዳንድ ድክመቶች ሊታዩ እንደሚችሉ ገልጸው፣ ድክመቶች መኖራቸውን መረዳት የቻሉትም ራሳቸውን ለአገልግሎት በማሰማራት በመሆኑ ገልጸዋል።  በድክመት ምክንያት አገልግሎታቸውን ካለማበርከት ወደ ኋላ አለማለታቸው ለአገልግሎት መጠራችውን ከልብ በመገንዘባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ድክመቶቻችንና ሌሎችም እንቅፋቶች ከተልዕኮአችን ወደ ኋላ ሊሉን ቢሞክሩም፣ እግዚአብሔር ደግሞ ድክመቶቻችንን ሳይቆጥርብን ከአቅማችን በላይ በሆኑ የአገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተን ውጤታማ የምንሆንበትን አቅምና ጉልበት እንደሚሰጥ አስረድተው በፍቅሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እንድናድግ ያግዛል ብለዋል።

በ34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ዕርዳትን ሲያበረክቱ የሰነበቱት የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች፣ የብርጭቆ ውሃን ከማቅረብ አንስቶ የተለያዩ ዕርዳታን ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶቹ ከዚያም በላይ አገልግሎታቸው የሰመረ እንዲሆን ሰፊ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ዝግጅታቸውንም በጸሎት በመታገዝ በደስታ ማከናወናቸውን አስታውሰዋል። በቤተክርስቲያን ለምናበረክተው አገልግሎት አቅምን ለማግኘት በጸሎት ስንጠይቅ ሃይል እንደሚገኝ የገለጹት ቅዱስነታቸው ከሁሉም በላይ ሃይል የሚሆን እግዚአብሔር እንደሆነ አስረድተዋል።

የግል ሥራዎችን ማከናወን ሲችሉ ነገር ግን በዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸውን ያበረከቱት ወጣቶች፣ ለበዓሉ ተካፋይ ወጣቶች ካደሉት የዳቦ እና የውሃ አቅርቦት በተጨማሪ ተስፋንም ጭምር እንዳካፈሉ ገልጸዋል። ወደ ፓናማ የበጎ አገልግሎት ተግባር ለማከናወን በማለት ከተለያዩ በርካታ አገሮች የመጡት ወጣቶች፣ ሌሎችን ለማገልገል ራስን ነጻ ሲያደርጉ እግዚአብሔርም እንደሚባርካቸው የተናገሩት ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር ይህን ለማድረግ የሚችል የቸርነትና የፍቅር አምላክ ነው ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ወጣቶች እምነታቸውን በተግባር እንደገለጹ፣ ከጸሎት የሚገኘውን ብርታት በተግባር የተመለከቱ መሆናቸውን፣ በዚህም ደስታን ማግኘታቸውን ገልጸው ይህ የሆነበት አንዱ መንገድ በሕብረት መንፈስ አብረው በመሥራታቸው ነው ብለዋል። ሌሎችም በርካታ ወጣቶች በእነዚህ ቀናት ውስጥ በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር ስለተከናወኑት ነግሮች ሊያውቁ ይገባል ብለው የተከናወኑ ሥራዎችን በሙሉ እግዚአብሔር ይባርክ ብለዋል። ቤተሰቦቻቸውንም እግዚአብሔር እንዲባርክ፣ በሥራዎች ሁሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እገዛ እንድትሆን በጸሎታቸው ጠይቀዋል።

በፖላንድ አገር፣ ክራኮቪያ ከተማ በተደረገው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ እንደተናገሩት ሁሉ በሚቀጥለው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ እርሳቸው እንደሚገኙ እርግጠኛ ባይሆኑም ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስ እንደሚገኝ እርግጠኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ወጣቶቹ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።                            

29 January 2019, 16:35