ፈልግ

የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት  

34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል በይፋ መጀመሩ ተነገረ።

የፓናማው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ፣ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ባሰሙት ንግግር መስዋዕተ ቅዳሴውን የተካፈሉ በርካታ ወጣቶችን አመስግነው፣ የፓናማ ከታማ የዓለም ወጣቶችን የምታስተናግድ የወጣቶች መዲና ሆናለች ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፓናማ በሚከበረው 34ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ከዓለም ዙሪያ የመጡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መካፈላቸውን ከሥፍራው የተላከልን ዘገባ አስታውቋል። መስዋዕተ ቅዳሴውን የመሩት የፓናማ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ ኡሎአ መሆናቸው ታውቋል። በፓናማ በሚከበረውን 34ኛውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ ለመገኘት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቫቲካን ከተማ መነሳታቸው ታውቋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወጣቶች፣

የፓናማው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ፣ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ባሰሙት ንግግር መስዋዕተ ቅዳሴውን የተካፈሉ በርካታ ወጣቶችን አመስግነው፣ የፓናማ ከታማ የዓለም ወጣቶችን የምታስተናግድ የወጣቶች መዲና ሆናለች ካሉ በኋላ በትላልቅ ድናጋዮችና ክርስታሎች በተገነባች በፓናማ ከተማ ውስጥ፣ የተለያዩ ቀለማት ያሏቸውን የየአገራት ባንዲራ የያዙ ወጣቶች “እኛ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወጣቶች ነን” እያሉ በሚያሰሙት መዝሙር ወጣቶች ብቸኝነት ሊሰማ አይገባም ብለዋል። በከተማይቱ ውስጥ ወደሚገኙት ቁምስናዎች በመሄድ ወጣቶቹ በሕብረት ሆነው የመቁጠሪያ ጸሎታቸውን ማቅረባቸውንና በሌሎችም መንፈሳዊ ፕሮግራሞች መካፈላቸውን ከከተማው የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።

ወጣቶች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች ናቸው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በፓናማ ለከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል መሪ ቃል እንዲሆን በማለት “እነሆኝ የጌታ ባርያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” በማለት፣ የበዓሉ ተካፋይ ወጣቶች ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ እንዲያቀርቡ በጠየቁት መሠረት፣ በዓሉ የሚከበርበት ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ፓናማ የመጡት የዓለም ወጣቶች በእጃቸው መቁጠሪያን ይዘው ጸሎት ሲያደርሱ መታየታቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጿል። 

ፍቅር በወጣቶች ሕይወት በገሃድ እንዲገለጥ ማድረግ ቀላል ባይሆንም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እገዛ ፍሬያማ ሊሆን ይቻላል። ይህ ጥቅስ ለእያንዳንዱ የበዓሉ ተሳታፊ ወጣት በተሰጠው የመቁጠሪያ ስጦታ ውስጥ የተጠቀስ ሲሆን፣ የፓናማው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ፣ ወጣቶች በፍርሃት መያዝ የለባቸውም፣ ተስፋቸውና ምኞታቸው በመንፈስ ቅዱስ ሃይል እውን ይሆናል፣ ፍቅር በወጣቶች ሕይወት እንዲገለጥ ማድረግ ቀላል ባይሆንም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እገዛ ፍሬያማ ሊሆን ይቻላል። በማለት ለውጣቶች ያስተላለፉትን መልዕክት፣ በመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ለወጣቶች ባሰሙት ስብከታቸው ገልጸዋል።

የፓናማ ገጽታ፣

34ኛውን ዙር ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ለማስተናገድና በድምቀት ለማክበር አቅሟ የፈቀዳትን ሁሉ ስታደርግ የቆየች የመካከለኛው ላቲን አሜርካ አገር ፓናማ፣ የተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች እንዳልተለዩዋት ከቦታው የሚሰራጩ ዘገባዎች አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ያለባትን ማሕበራዊ ችግር፣ ዓለም አቀፉ የወጣቶች በዓል በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ የሚያስችላትን መንገድና ዕድል ሊከፍትላት ይችላል የሚል ተስፋ በስፋት እንዳለ ተነግሯል። በተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች የተጠቃውን ሕዝብ በተመለከተ፣ በዋና ከተማዋ ፓናማ ዙሪያ፣ ፓኮራ በተባለ አካባቢ የሚገኙትን እጅግ የደሄዩ ቤተሰቦችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አርብ ዕለት እንደሚጎበኟቸውና በአካባቢው በሚገኘው ማረሚያ ቤት ውስጥ ከሚገኙት ወጣቶች ጋር አብረው እንደሚጸልዩ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር አመልክቷል።

በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙ የከተማ ዳርቻ ነዋሪዎች፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓናማ በሚከበረው 34ኛ ዓለም አቀፍ በዓል ላይ የሚያስተላልፉት መልዕክት ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን ማሕበረ ሰብ የሚያስታውስ ወይ የሚያካትት እንደሚሆን ይጠበቃል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በበላይነት ከተገኙባቸው የመጨረሻዎቹ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓላት በስተቀር ባለፉት በዓላት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተገኙበት፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ የተደረገ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት እንዳልተካሄደ ሲታወቅ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙትን፣ ከእነዚህም መካከል የኤይድስ ሕመምተኞችን፣ በተለያዩ በሽታዎች የሚሰቃዩትንና የተረሱትን፣ ትኩረትን የተነፈጉ የጦርነት ሰለባ የሆኑትን በሙሉ በመጎብኘት የተስፋ መልዕክታቸውን እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይፈጸም ዘንድ “እነሆኝ የጌታ ባርያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” እንዳለች ሁሉ የፓናማም ወጣቶች ለእግዚአብሔር ፈቃድ አዎንታዊ ምላሽን ሊሰጡ ይገባል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእግዚ አብሄር ፈቃድ ቅድሚያን መስጠቷ የናዝሬት ከተማን የዓለም ማዕከል እንዳደረጋት ሁሉ ትንሿ የላቲን አሜርካ አገር ፓናማም፣ ለእግዚአብሔር በምትሰጠው አዎንታዊ ምላሽ የተባረከች ልትሆን ይገባታል።                 

23 January 2019, 14:51