ፈልግ

ወጣቶች በዓለም አቀፍ በዓላቸው ላይ ሆነው ወጣቶች በዓለም አቀፍ በዓላቸው ላይ ሆነው  

በፓናማ የዓለም ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተስፋንና ብርታትን እንደሚያገኙ ገለጹ።

በፓናማ ከሚካሄደው ዓለም አቀፍ በዓል የሚጠብቁት ነገር፣ ከዚህ በፊት በተደረጉት ዓለም አቀፍ በዓላት እንደሆነው ሁሉ፣ ተስፋንና ብርታትን ለማግኘት እንደሆነ ገልጸው፣ ወደ ፓናማ እንዲመጡ ያደረጓቸውም፣ የደስታ ጳጳስ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ ለ34ኛ ጊዜ በፓናማ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ ለመገኘት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ወደ መካከለኛዋ የላቲን አሜርካ አገር ወደ ሆነችው ወደ ፓናማ መጓዛቸው ታውቋል። ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል በሚከበርበት በፓናማ ከ160 ሺህ በላይ ነጋዲያን ወጣቶች ከ156 አገሮች የመጡ ሲሆን ከእነርሱም ጋር 480 ብጹዓን ጳጳሳት መገኘታቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ወስጥ ከተለያዩ መንግሥታዊና የቤተክርስቲያን ተቋማት ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ፣ ቀጥለውም ከጥር 14 ቀን ጀምረው በፓናማ ከተማ ከሚገኙትን የዓለም ወጣቶች ጋር እንደሚገኛኙ ታውቋል።

ወጣቶች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ፓናማ ሲደርሱ ከተማዋ የሕብረት መዝሙሮች የተስተጋቡባት፣ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቀች፣ የላቲን አሜርካ ሕዝብ መለያ በሆነው የደስታና የፈገግታ ስሜት የተዋጠች መሆኗ ታውቋል። “ፓናማ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልባዊ ሰላምታዋን ታቀርባለች” ባሉት መልዕክታቸው ይህንንም ለመግለጽ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተለያዩ ባሕላዊ ውዝዋዜዎችና ዘፈኖች ለቅዱስነታቸው ቀርበውላቸዋል።

ፓናማ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በደስታ ተቀብላለች፣

ለ34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶችን በዓል ለማክበር ወደ ፓናማ የመጡትን፣ በብዙ ሺህ ዎች የሚቆጠሩትን ወጣቶችን በማስተናገድ ላይ የምትገኝ ፓናማ፣ የከተማዋ መንገዶች በእንግዶችና በመኪኖች መጨናነቁ ታውቋል። ወጣቶች የሚሰበሰቡባቸው የተለያዩ ስፍራዎች መዘጋጀታቸው የታወቀ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የወጣቶችን ዓለም አቀፍ በዓል ንግግር በማድረግ የከፈቱበት ሳንታ ማርያ ላ አንቲጓ የተባለ ሰፊ የባሕር ዳር የመሰብሰቢያ ስፍራ እንደሚገኝ ታውቋል። ይህ ታዋቂ ስፍራ ወጣቶች ደስታቸውን የሚገልጹበት፣ ተስፋቸውንም የሚያደርጉበት ስፍራ እንደሆነ የታወቀ ሲሆን በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች ቁጥር ከከተማዋ ስፋት ጋር ሲወዳደር ምናልባትም እጅግ በልጦ እንደተገኘ ለማወቅ ተችሏል። በፓናማ ከተማ ለወጣቶች መሰብሰቢያ እንዲሆን ተብሎ ከተዘጋጁት ስፍራዎች መካከል ሌላው ኦማር ፓርክ የሚል ስም የተሰጠው ሜዳ ሲሆን ይህ ስፍራ የወጣቶች ፓርክ የሚል ስም የተሰጠው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በዚህ ፓርክ ውስጥ ከ200 በላይ በታራሚ ወጣቶች የተዘጋጁ የኑዛዜ ቦታዎች መኖራቸው ታውቋል።

የፈረንሳይ ወጣቶች መልካም አቀባበል እንደተደረገላቸው ተናገሩ፣

ወደ ፓናማ የመጡበት ምክንያት ከሌሎች ወጣቶች ጋር ለመገናኘት፣ በእምነት ጉዞም ብቸኝነት እንዳይሰማን ስለማንፈልግ ነው ያሉት በፈረንሳይ የሊዮን ከተማ ወጣቶች በበኩላቸው እንደገለጹት ወደ ፓናማ ሲደርሱ የተደረገላቸው አቀባበል አስደሳች እንደሆነ ገልጸው ወደ ፓናማ የመጡበት ዋናው ምክንያት የመላዋ ቤተክርስቲያን አካል በመሆን የዛሬና የነገ ትውልድ መሆናቸውን ለመግለጽ እንደሆነ ተናግረዋል። አንዳንድ ጊዜ እምነታችንን ለመደበቅ ይቃጣናል ብለው ዛሬ በዚህ ስፍራ ተገኝተን በነጻነትና በደስታ፣ ባንተዋወቅም እንኳን ተመሳሳይ ምኞት ካላቸው የዓለም ወጣቶች ጋር ሆነው እምነታቸውን ለመግለጽ መምጣታቸውን አስረድተው ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት የተካሄዱት ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ለእምነታቸው መዳበር ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳደረጉላቸው ገልጸው በፓናማ የሚካፈሉት የወጣቶች በዓልም የበለጠ ለማደግ እንደሚረዳቸው አስረድተዋል። ወደ ፓናማ ሲደርሱ የተደረገላቸው አቀባበል እንዳስደሰታቸው የተናገሩት በፈረንሳይ የሊዮን ከተማ ወጣቶች በማከልም በበዓሉ ላይ የተገኙት ወጣቶች ከተለያዩት አገሮች የመጡ ቢሆንም በመካከላችን አንድ የሚያደርገን መንፈስ እንዳለ ግልጽ ነው ብለዋል።

በፓናማ ከሚካሄደው ዓለም አቀፍ በዓል የሚጠብቁት ነገር፣ ከዚህ በፊት በተደረጉት ዓለም አቀፍ በዓላት ወቅት እንዳደረጉት ሁሉ፣ ተስፋንና ብርታትን እንደሆነ ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደዚህ ስፍራ እንድንመጣ ያደረጉን የደስታ ጳጳስ ናቸው ብለው፣ የቤተክርስቲያን ተስፋ የሚያደርጋቸውን መልዕክት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመቀበል ትልቅ ጉጉት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በአይሁዶች እና በካቶሊኮች መካከል መተማመን አለ፣

በፓናማ በመካሄድ ላይ ባለው 34ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ የተገኙት 50 የአይሁድ እምነት ተከታዮች መኖራቸው የተረጋገጠ ሲሆን በፓናማ ከተማ ለሚገኝ ምኩራብ አለቃ የሆኑት መምሕር ጉስታቮ ክራሰሊንክ እንደገለጹት በፓናማ ከምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር ያላቸው ግንኙነት የሚያበረታታ እንደሆነ ገልጸው ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም የእምነት ተቋማት ጋር ያላቸው መልካም እንደሆነ ተናገረዋል። ፓናማ ትንሽ አገር ናት፣ ሕዝቦቿ በሙሉ እርስ በርስ እንተዋወቃለን፣ በተለይም በአይሁድና በካቶሊክ እምነቶች መካከል የበለጥ ትውውቅ አለን። ይህም የሆነበት ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ወዲህ መልካም የውይይት መድረክ ስለተፈጠረ ነው፣ ከ15 እና ከ20 ዓመታት ወዲህ በየጊዜው እየተገናኘን የምንወያይበት፣ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነታችንን የምናሳድግበት ዕድል ስለተገኘና መተማመንን ስለፈጠረ ወጣቶቻችንም በዓለም አቀፉ የወጣቶች በዓል ላይ እንዲገኙ ወስነናል ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጉብኝት በወጣቶች መካከል የሞራል መታደስን ያስገኛል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለውጣቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት ባሁኑ ወቅት በወጣቶች ዘንድ በጉጉት እየተጠበቀ መሆኑ ሲነገር፣ በተለይም በፓናማ ወጣቶች መካከል የሞራል መታደስን ያስገኛል ተብሏል። በበርካታ ሰዎች አስተያየትም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ለፓናማ ሕዝብ በሙሉ፣ ለክርስቲያና ክርስቲያን ላልሆኑት፣ ምንም እምነት ለሌላቸውም ተስፋን የሚሰጥ፣ ሃገሪቱ የምትጠይቀውን አስቸኳይ የለውጥ ጥያቄን ለመመለስ ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።  

24 January 2019, 16:22