ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አድልዎ እና ፍርሃት ተወግዶ እውነተኛ ፍቅርን ማሳየት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓናማ ከተማ በሚገኘው፣ የመልካም ሳምራዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተገኝተው የኤይድስ ሕሙማንን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የአድልዎን እና የፍርሃት መንፈስ በማስወገድ ችግር ውስጥ ለወደቁት እውነተኛ ፍቅርን ማሳየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በፓናማ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የመልካም ሳምራዊ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ውስጥ፣ በተላላፊ የኤይድስ በሽታን ጨምሮ በተለያዩ በሽታዎች የሚሰቃዩትን በርካታ ወጣቶች እና አዛውንት የጎበኙት ቅዱስነታቸው ለታመሙት እና ለተቸገሩት እርዳታን ማድረግ የእግዚአብሔር ምሕረት የሚገለጥበት አንዱ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። በፓናማ ከተማ በሚገኝ የመልካም ሳምራዊ ማዕከል በኩል የሚሰጥ አገልግሎት ቤተክርስቲያን ድሆችን፣ ሕሙማንን፣ የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቂዎችን፣ ያለ ተንከባካቢ የቀሩትን፣ ከማሕበረሰቡ የተገለሉትን ሁሉ ተቀብላ የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት እንድታበረክት ከእግዚአብሔር የተሰጣት ተልዕኮ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ይህን የመሰለ አገልግሎት ከዚህ በፊት በተደረጉት ሌሎች ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ጎልቶ ባይታይም፣ ቤተክርስቲያን አገልግሎቷን በምታበረክትበት ጊዜ የሚሰማት ደስታ ቀጣይነት አለው ብለዋል። በፓናማ ከተማ የመልካም ሳምራዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ዶሚንጎ ኤስኮባር፣ በማዕከሉ ውስጥ እርዳታን በማግኘት ላይ በሚገኙ ተረጂዎች ስም ሆነው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ላደረጉት አመስግነው በጉብኝታቸውም እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እንዳዳመጠ ገልጸዋል። በስፍራው ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ የአገልግሎት መስጫ ማዕከልን ጨምሮ ከሌሎችም ማዕከላት የመጡት፣ በቁጥር 60 የሚሆኑ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ለቅዱስነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

አዲስ ሕይወት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በበኩላቸው በአገልግሎት መስጫ ማዕከሉ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በማዕከላቱ ውስጥ እርዳታ ከሚደረግላቸው ወጣቶች ጋር የተገናኙበት አጋጣሚ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ተስፋ የታደሰበት እንደሆነ ገልጸው፣ አጋጣሚውን ላመቻቹት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ሕይወት መኖር የሚቻለው፣  ለምናውቃቸው ወይም ለምንወዳቸው መልካምን በማድረግ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ በችግር ላይ የወደቁትን ለመመልከት የሚያስችለንን ዓይን እና ሕሊናን ከመንፈስ ቅዱስ ስናገኝ ነው ብለዋል።

ከማዕከሉ ተረጂዎች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ወደዚህ ማዕከል በገባ ጊዜ እንደገና መወለዱን በመሰከረበት ጊዚ ልባቸው እንደተነካ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ማዕከሉ አዲስ ሕይወት የሚገኝበት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑንም ገልጸዋል። አንዳንድ ወጣቶች ቁስላቸው ሲፈወስ፣ ተስፋቸው ሲለመልም፣ በእምነታቸውም ሲበረቱ በማየት የእምነታቸውን ጥንካሬ ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል። በዚህ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ አዲስ የሚወለዱት እና አዲስ ሕይወትን የሚያገኙት ተረጂ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ቤተክርስቲያን በቸርነት አገልግሎቶቿ እንደምታድግ፣ እምነትም በቀጣይነት እንደሚታደስ እና እንደሚያድግ አስረድተዋል።                   

ለባለእንጀራ በሚደረግ ቸርነት አማካይነት ብርታትን ማግኘት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ፓናማ ስላደረጉትን ጉዞ ዓላማ በማስመልከት ባሰሙት ንግግር ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት የምንችለው በባልንጀሮቻችን በኩል እንደሆነ ገልጸው ለተቸገሩት፣ ለታመሙት እና  ለደሄዩት የዕርዳታ እጆቻችንን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። እገዛ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በየዕለቱ እንደሚያጋጥሙን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ለራስ ቅድሚያን ከመስጠት ይልቅ ለተቸገሩትም በመጨነቅ፣ ሕይወታቸውን በሚገባ ተመልክተን በማሕበራዊ ሕይወት ቦታ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። 

የሰዎችን ስቃይ ችላ ማለት ተገቢ አይደለም፣

ጥቃት ደርሶበት በሞት አፋፍ ላይ ለሚገኝ ሰው እርዳታ ካለተደረገለት፣ ጥቃትን ያደረሰው ወንጀለኛው ብቻ ሳይሆን፣ ለዚያ ለተጎዳው ሰው እርዳታ ማድረግን ያልፈለጉት በሙሉ ጥቃት የፈጸሙ ናቸው ብለዋል። በመሆኑም በችግር ላይ ለወደቀ ሰው በቸልተኝነት ትኩረትን አለመስጠት ራስን እንደመግደል ይቆጠራል ያሉት ቅዱስነታቸው ቸልተኝነት የተላላፊ ቫይረስ ያህል ሰውን ያቆስላል፣ ይገድላልም ብለዋል።

በፓናማ ከተማ የሚገኝ የመልካም ሳምራዊ ማዕከል ለተቸገሩት የሚያበረክተ እርዳታ መልካም ምሳሌ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው በምንም ዓይነት ሁኔታ ላይ ቢገኙ የተቸገረን አይቶ ማገዝ ወይም መርዳት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፣ በዓለማችን ውስጥ በርካታ ሰዎች ምንም ዓይነት ዕርዳታ ሳያገኙ በችግር ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ለተቸገሩርት ዕርዳታን መለገስ የነጻነት ጎዳናን እንድንከተል እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም እንድንችል ያደርገናል ብለዋል።

የቤተክርስቲያን የእናትነት መልክ፣

ቤተክርስቲያን በዓለም ዙሪያ የምታበረክተው የዕርዳታ አገልግሎት በገሃድ እንዲታይባት ባታደርግም ነገር ግን እውነተኛ የእግዚአብሔር ምሕርት እና ርህራሄ የሚገለጥበት፣ የትንሳኤው መልካም ዜና የሚበሰርበት  ምልክት እንደ ሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በሕብረት በመሆን የቤተሰብነትን መንፈስ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ ይህን ሊያደናቅፉ የሚችሉ የተለያዩ ችግሮችን በማሸነፍ፣ ጥቂት ቢሆንም በዕለታዊ ሕይወታችን መካከል መልካም ማድረግን መለማመድ ያስፈልጋል ብለዋል።

የእመቤታችን ማርያም እገዛን እንጠይቅ፣

የርህራሄ እናት የሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ርህራሄን እንድታስተምረን፣ ለባልንጀሮቻችን ፍቅርን የምንገልጽበት ልብ፣ የሚያስፈልጋቸውን ዕርዳታ ለማድረግ የምንችልበትን ልብ እንድተትሰጠን እንለምን ብለው ይህም በጋራ የተጠራንበት ተልዕኮ መሆኑን አስረድተዋል።                      

             

29 January 2019, 16:47