ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓኮራ ማረሚያ ቤት ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓኮራ ማረሚያ ቤት ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፓናማ፣ ፓኮራ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን አጽናንተዋል።

ወንድሞቼና እህቶቼ! እናንተ የአንድ ቤተሰብ አባል ናችሁ እንጂ የተለያችሁ አይደላችሁም። ለማሕበረሰቡም ልታበረክቱ የምትችሉት በርካታ ስጦታ አላችሁ። በዚህ ችሎታችሁ ማህበረሰቡ ካልታገዘ እጅግ ይጎዳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓናማ በተዘጋጀው 34ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ተገኝተው በመቶ ሽህዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች ጋር መገናኘታቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በፓናማ ቆይታቸው ከተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት ሰፋ ያለ መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። ከእነዚህም መካከል በፓናማ፣ ፓኮራ በተባለ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ ወጣቶች ንግግር አድርገዋል። የንግግራቸው ትርጉም እንደሚከተለው ቀርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል” (ሉቃ. 15,2)። በዚህ የወንጌል ጥቅስ የኢየሱስ ክርስቶስ ተግባር ምን እንደሚመስል ስንረዳ በሌላ ወገን ደግሞ፣ በፈሪሳዊያን፣ በቀራጮች እና በሙሴ የሕግ መምህራን ዘንድ ማጉረምረምንና ቁጣን ያነሳሳ መሆኑን እንረዳለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን በማድረጉ ምክንያት ውርደትን እንዲከናነብና ከሕዝቡ መካከል እንዲገለል ለማድረግ፣ የሙሴ የሕግ መምህራንና ፈሪሳዊያን ጥረት አድርገዋል። እነርሱ ሊያጠቁት የተነሱበት የኢየሱስ ተግባር  ከሕዝቡ ዕለታዊ ኑሮ ጋር የተያያዘ፣ ሕዝቡም የሚፈልገው ስለነበር ምንም ችግር አልፈጠረበትም። እኛ ሁላችን ሐጢአተኞች ስለሆንን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ራሱ እንደሚቀበለን ሊሰማን ይገባል። ነገር ግን ከእኛ መካከል ሐጢአተኛ መሆኑ የማይቀበል፣ ያ ሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚቀበለው ትልቅ ስጦታ እንዲቀርበት ማድረጉን ሊያውቅ ይገባል።

ኢየሱስ በተለያዩ ምክንያቶች ከሕዝቡ ጋር ጥላቻ ያደረባቸውን፣ የገዛ ሕዝባቸውን የሚበዘብዙትን የሚጨቁኑትን ለመቃወም ወደ ኋላ አላለም። ኢየሱስ ክርስቶስ የተለያዩ ጥፋቶችን በመፈጸማቸው ምክንያት በሕዝብ ዘንድ ጥሩ ስም የሌላቸውንና ተቀባይነት ያጡትን ሰዎች ተቀብሎ አስተናግዶአቸዋል። ይህን የሚያደርገው ከዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ በሐጢአቱ ተጸጽቶ በሚመለስ በአንዱ፣ በሰማይ ታላቅ ደስታ እንደሚሆን ስለሚያውቅ ነው (ሉቃ. 15.7)።

ኢየሱስ ከወንጀለኞች ጋር፣ በክፉ ሥራቸው ምክንያት ከማሕበረሰቡ የተወገዙትን ወደ ራሱ ማቅረቡ በአንዳንዶች ዘንድ ቁጣን እንደሚቀሰቅስ፣ ማንነቱንም እንደሚጎዳ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ብዙን ጊዜ እንደሚመክረን፣ ዓይናችንን ወደ ላይ አቅንተን፣ ሕይወታችንን ወደሚቀይር፣ ታሪካችንን ወደሚለውጥ፣ ወደ ሰማዩ አባት እንድንመለከት ይነግረናል። እያንዳንዳችን ይህን ማድረግ የምንችልበት አጋጣሚ አለን። ስለዚህ ማንም ቢሆን የልቤን የማወያየው የለኝም ሊል አይችልም። የልባችሁን መስኮት ክፍት አድርጉት። ፍቅር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ታገኙታላችሁ። ሁለት ተቃራኒ ምርጫዎች ወይም መንገዶች አሉ። አንደኛው ኢየሱስ ክርስቶስ መከተል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሙሴ ሕግ መምህራን መከተል ናቸው። ዋጋ ቢስ ከሆኑት መንገዶች መካከል ጥቂቶቹ ማጉረምረም፣ ሐሜት ማውራት እና ራስን ትክክለኛ አድርጎ መቁጠርና ስለ ሌሎች ክፉ መናገር ናቸው። ሌላው ወደ ለውጥ እና ወደ አዲስ ሕይወት የሚመራን ኢየሱስ የሄደበት መንገድ ነው።

የማጉረምረምን እና የሐሜትን መንገድ መከተል፣

ማጉረምረም እና ሐሜት ማውራት በዘመናችንም በብዙዎች ዘንድ የሚንጸባረቅ ልማድ ነው። ብዙ ሰዎች ኢየሱስ የሄደበትን መንገድ መራመድ አልፈለጉም። ይህን የሚገልጹት ዘወትር በማጉረምረም፣ ወደ አደባባይ ወጥተው በጩሄት የተቃውሞ ሲያሰሙ በመደመጣቸው ነው። በዚህ ብቻ ሳያበቁ የኢየሱስን እና የእርሱ ተከታይ የሆኑ ሰዎች ስም በማጥፋትም ጭምር ነው። በሕዝቡ ዘንድ ወደ ተጠሉት ዘንድ ቀርበው ከስህተታቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ መንገድ ማሳየትን ፈጽሞ አይፈልጉም። ምክንያቱም የተሳሳቱ በመሆናቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ለዘለዓለም የተወገዙ አድርገው ስለሚቆጥሩ ነው። የእግዚአብሔር ርህራሔ እና ፍቅር እንደሚያስልጋቸው አይገነዘቡም። ይህ ደግሞ በሰዎች ያለፈው ሕይወት ብቻ ሳይሆን በወደ ፊቱ ሕይወታቸውም መጥፎ አሻራን ጥሎ ያልፋል። የሰዎችን ደካማ ጎን ብቻ በማንሳት እና በማስታወስ የተበላሸ ስም እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። ሐሜተኞች የሚያደርጉት ይህን ነው። መልካም እና ክፉ በሚሏቸው፣ ትክክለኛና ሐጢአተኛ በሚሏቸው ሰዎች መካከል ልዩነትን ይፈጥራሉ። የዘመናችን ባሕል ከሰዎች ማንነት ጋር የሚመሳሰል ስም መስጠት ሆኗል። ይህም ማለት ክፉ የሰራ እንደሆነ ክፉ ስም መስጠት፣ መልካም የሰራ እንደሆነ መልካም ስም መስጠት ነው። ይህን በማድረግ የሰዎችን ስም በማጥፋት ወደ ውርደት በመክተት ከማሕበረሰብ እንዲገለሉ ያደርጋሉ። ኢየሱስ የሄደበት መንገድ ይህ አለመሆኑ ተገንዝበን ይህን ባሕል መቃወም ያስፈልጋል።

በሕዝቦች መካከል የተገነባው የማይታይ የልዩነት ግድግዳ እንደ ትክክለኛ አካሄድ ተቆጥሮ፣ ችግሮችን  በቀላሉ ማስወገድ የሚቻለው ማንነታቸውን በመለየት ነው ብለው እንዲያስቡ አድርጎአቸዋል።  በአንድ ማሕበረሰብ መካከል ሐሜትና ማጉረምረም የተስፋፋ ከሆነ ክፍፍልን ማስከተሉ አይቀርም። አስገራሚው ነገር፣ ኢየሱስን መከተል የማይፈልጉ ሰዎች በመካከላቸው መለያየትንና መገለልን ፈጥረው፣ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ እንደተናገርው “ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ ይሻላል” (ዮሐ. 11.50) እንዳለው፣ ኢየሱስን ከማሕበረሰብ መካከል ተነጥሎ እንዲቀር እንዳደረጉት ሁሉ በዘመናችንም በተለይ በአቅመ ደካሞች፣ በደሆችና  እና መከታ በሌላቸው ሰዎች ላይ የሚደረገውን ማግለል መዋጋት ያስፈልጋል። ከሁሉ በፊት የማሕበራዊ ችግሮች ገፈት ቀማሾች እነዚህ የተገለሉ ሰዎች  ናቸው። ማሕበራዊ ለውጦችን እና አዳዲስ የልማት መንገዶችን ከማመቻቸት ይልቅ በሐሜትና በማጉረምረም ብቻ ጊዜው የሚያባክን ሕብረተሰብን ያሳዝናል።

የለውጥ መንገድ፣

ቅዱስ ወንጌል የሚያስቀምጥልን የለውጥ መንገድ እግዚአብሔር ካቀደልን መንገድ የተለየ አይደለም። የእግዚአብሔር ዕቅድ እናንተን ወደራሱ በመጥራት የበለጠ እንድትቀርቡት በማለት እጆቹን ዘርግቶ ይጠብቃችኋል። ወደ እርሱ የሚያደርሰውን መንገድ ባታውቁት እንኳን እርሱ ያሳያችኋል። ከእግዚአብሔር ዕቅድ የተለየ ሁሉ ሰዎችን ከሰዎች የሚለያይ ነው። በሉቃ. 15. 11-13 ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር ልጆቹ በሙሉ ወደ እርሱ ተመልሰው እንዲመጡ ይፈልጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ምሕረት በግልጽ እንዲታይ አድርጓል። የኢየሱስ ፍቅር ራስን ከወቀሳ፣ ጥቅመ ቢስ አድርጎ ከመቁጠር ነጻ ማድረግን እንጂ ለሐሜት እና ለማጉረምረም ጊዜ የለውም። የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የልጁ የኢየሱስ ፍቅር ወደ ፈውስ፣ ወደ ምሕረት፣ ራስን ወደ መለወጥ እና ወደ ይቅርታ የምትደርሱበትን መንገድ የሚያሳይ ፍቅር ነው። ከሐጢአተኞች ጋር አብሮ በመብላቱ በሰዎች መካከል ያለውን የልዩነት እና የመከፋፈል አስተሳሰብን አስወግዶታል። ይህን ያደረገው ሕግን በማርቀቅ አይደለም። በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት የሻረው ልዩነት ሳያደርግ ከሁሉም ጋር አብሮ በመዋሉ ነው።    

ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን ሐሜት እና ሐዘን ወደ ደስታ ይለውጠዋል። ከእኔ ጋር ተደሰቱ በማለት ይጋብዘናል። ወንድሞቼና እህቶቼ! እናንተ የአንድ ቤተሰብ አባል ናችሁ እንጂ የተለያችሁ አይደላችሁም። ለማሕበረሰቡም ልታበረክቱ የምትችሉት በርካታ ስጦታ አላችሁ። በዚህ ችሎታችሁ ማህበረሰቡ ካልታገዘ እጅግ ይጎዳል። ከእግዚአብሔር የተሰጠን የአንድነት መንገድ ልዩነቶችን በማስወገድ ሰዎችን ወደ ምሕርት መንገድ የሚጋብዝ ነው። በመሆኑም የደስታን ሕይወት እንድንኖር የተዘጋጀልንን መንገድ እንድንጓዝ ያስፈልጋል፣ አመሰግናለሁ።                             

28 January 2019, 15:11