ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራነችስኮስ ““ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ይቅርታ ማድረግ እንደ ሚገባን ያስተምረናል!”

የጎርጎስሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ዘንድ ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት የገና በዓል በደማቅ ሁኔታ በትላንትናው እለት ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከተከበረበት የገና በዓል በመቀጠል ባያለው እለት የቤተ ክርስቲያን የመጀመርያው ሰማዕት የሆነው የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓል እንደ ሚከበር ይታወቃል። ይህ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ሰማዕት በመባል የሚታወቀው የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓል በታኅሳስ 17/2010 ዓ.ም. በቫቲካን ተከብሮ ማለፉ ተገልጹዋል። በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይህንን የቅዱስ እስጢፋኖስን በዓል ለማክበር ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች ባሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ገለጹት “ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ይቅርታን ማድረግ እንደ ሚገባን ያስተምረናል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በታኅሳስ 17/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን የቅዱስ እስጢፋኖስን ዓመታዊ በዓል አስመልክተው ያሰሙትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
የገና በዓል ደስታ አሁንም ልባችንን እያጥለቀለቀ ይገኛል፣ ለእኛ ሲል የተወለደው የክርስቶስ ድንቅ አዋጅ አሁንም ቀጥሉዋል፣ ለዓለምም ሰላም ያመጣል። በዚህ የደስታ መንፈስ ውስጥ ወይም ድባብ ውስጥ ሆነን የመጀመሪያ ሰማዕት እና ዲያቆን የነበረውን የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል እናከብራልን። የቅዱስ እስጢፋኖስን የመታሰቢያ በዓል ከኢየሱስ የልደት በዓል ወቅት ጋር በተያያዘ መልኩ ማክበር እንግዳ ነገር ሊመስል ይችላል፣ ምክንያቱም በኢየሱስ መወለድ የተነሳ በቤተልሔም በነበረው ደስታ እና ቤተ ክርስቲያን በተወለደችበት ማግስት በቤተ ክርስቲያን ላይ በተቃጣው ስደት ምክንያት የመጀመርያው ሰማዕት በነበረው በእስጢፋኖስ መካከል የሚቃረን ነገር ያለ ስለሚመስል ነው። በተጨባጭ ግን እንዲህ አይደለም፣ ምክንያቱም ሕፃኑ ኢየሱስ ሰው የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣ እሱም በመስቀል ላይ በመሞት ሰዎችን ያድናል። አሁን በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ መተኛቱን በማሰላሰል ላይ እንገኛለን፣ ከእዚያም ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ደግሞ አሁኑም በአዲስ መልክ በጨርቅ ተጠቅልሎ በመቃብር ውስጥ ስያስቀምጡት እናያለን። 

መለኮታዊ የሆነውን ጌታ ፈለግ በመከተል ሰማዕትነትን የተቀበለው የመጀመሪያው ሰው ቅዱስ እስጢፋኖስ ነበር፣ ኢየሱስ ሕይወቱን ለእግዚኣብሔር በአደራ በመስጠት ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠና አሳዳጆቹን ይቅር በማለት እንደ ሞተ ሁሉ ቅዱስ እስጢፋኖስም እንዲሁ አድርጉዋል። እስጢፋኖስን በድንጋይ ይወግሩት በነበረበት ወቅት እርሱ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል” (የሐዋ. ሥራ 7፡59) ብሎ ተናገረ። እነዚህ ቃላት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ከተናገራቸው ቃላት ጋር በጣም ተመሳሳይ ናቸው፡ ኢየሱስም በመስቀል ላይ ሳለ “አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ በአደራ ሰጣለሁ” (ሉቃ 23፡46) ብሎ ከተናገረው የኢየሱስ ቃላት ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። የኢየሱስን አካሄድ በታማኝነት የተከተለው የእስጢፋኖስ ባህሪ እያንዳንዳችን በሕይወታችን የሚከሰቱትን አዎናታዊ እና አሉታዊ የሆኑ ነገሮችን በእምነት በእግዚኣብሔር እጅ ውስጥ በአደራ ማስቀመጥ እንደ ሚገባን እና ጽኑ ሆነን መኖር እንዳለብን የሚጋብዘን ጥሪ ነው። እኛ የመኖር ሕልውና አስደሳች በሆኑ ሁኔታዎች ብቻ የተሞላ ሳይሆን፣ ነገር ግን አንዳንዴ በመከራ እና በመጥፎ ስሜት የተሞላ ሊሆንም ይችላል። ነገር ግን በእግዚአብሄር መታመን አስቸጋሪ ወቅቶችን ለመቀበል እና በእምነት ለማደግ፣ እንዲሁም ከወንድሞቻችን ጋር አዲስ ግንኙነቶችን መመስረት እንችል ዘንድ ዕድሉን ያመቻችልናል። ይህም ማለት ደግሞ በእግዚኣብሔር እቅፍ ውስጥ ራሳችንን በማስገባት እርሱ በመልካም ነገሮች የተሞላ ባለጸጋ አባት መሆኑን እና ለልጆቹ የምያስብ አባት መሆኑን ማወቅ ማለት ነው።
በመቀጠል እስጢፋኖስ የኢየሱስን ባህሪ የተላበሰበት ሁለተኛው አጋጣሚ የተክሰተው ደግሞ በመስቀል ላይ ነበር፣ ይህም ይቅርታ ማድረግ የሚለውን አመለካከት ያሳያል። እስጢፋኖስ መከራ ስያደርሱበት የነበሩትን አሳዳጆቹን አልረገመም፣ ወይም አልተሳደበም፣ ነገር ግን በተቃራኒው “ተንበርክኮ፣ ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ በመጮኸ ለእነሱ ጸለዬ” (የሐዋ. 7፡60)። እኛም ከእርሱ ሕይወት በመማር ሁል ጊዜ ይቅር ባይ እንድንሆን ተጠርተናል፣ ይቅርታ ማድረጉ ልብን ይከፍታል፣ ካለን የማጋራት መንፈስን ያመነጫል፣ ሰላምን እና መረጋጋትን ይሰጠናል። የመጀመርያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት እና በሥራ ቦታ በቁምስና እና በተለያየ ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ጥልቀት ያለው ግንኙነት መጀመር እንችል ዘንድ መንገዱን ያሳየናል። የይቅርታ እና የምህረት አመክንዮ ሁሌም ቢሆን የአሸናፊነት እና የተስፋ አድማስን ይከፍታል። ነገር ግን የይቅር ባይነትን መንፈስ ለማሳደግ በጸሎት መኮትኮት ያጠይቃል፣ ይህም ዓይናችን በኢየሱስ ላይ እንድያተኩር ያደርገናል። እስጢፋኖስ ገዳዮቹን ይቅር ማለት ችሎ ነበር፣ ምክንያቱም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ በማየቱ የተነሳ ነበር (የሐዋ.7፡55)። እርሱ ካደረገው ጸሎት ውስጥ ሰማዕትነትን ለመቀበል የሚያስችል ጥንካሬ አገኘ። ፍራቻዎቻችንን፣ ድክመቶቻችንን፣ ስህተቶቻችንን ለማስወገድ እና ለመፈወስ ያስችልን ዘንድ ጥንካሬን እና ብርታትን ይሰጠን ዘንድ መንፈስ ቅዱስን አጥብቀን መማጸን እና ለእርሱ መጸለይ አለብን።
ይህንንም ጸጋ ማግኘት እንችል ዘንድ እንዲረዱን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን እና የቅዱስ እስጢፋኖስን አማላጅነት እንማጸናለን፡ የእነርሱ ጸሎት በተለይም በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ በምንሆንበት ወቅት ለእግዚአብሔር ራሳችንን በአደራ እንድንሰጥ ያግዘናል፣ በተጨማሪም እኛም ይቅር ማለት የምንችል ወንዶች እና ሴቶች እንድንሆን ያበረታናል።
 

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 December 2018, 16:12