ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ኢየሱስን ለመቀበል ያስችለን ዘንድ ልባችንን መክፈት ይኖርብናል”

ዛሬ የሚጀመረው የስብከተ ገና ሳምንት ስርዓተ አምልኮ ለገና በዓል የምያዘጋጃን ወቅት ሲሆን ኢየሱስን ለመቀበል ልባችንን መክፈት እንችል ዘንድ ይጋብዘናል።

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በትላንትናው እለት ማለት በኅዳር 03/2011 ዓ.ም የመጀመርያው የስብከተ ገና ሣምንት መጀመሩ ይታወቃል። በዚህ የስብከተ ገና ወቅት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን ከመበሩ ከአራት ሳምንታት በፊት ለዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን የሚሆን መንፈሳዊ ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት ሲሆን በእነዚህ ሳምንታት ምዕመኑ በጸሎት፣ በአስተንትኖ፣ በኖቪና እና በመሳሰሉ መንገዶች መንፈሳዊ ዝግጅቶችን በማድረግ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ቀን ለማክበር የሚዘጋጁበት ወቅት ነው።

ከላይ ለመጥቀስ እንደ ተሞከረው የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በኅዳር 23/2011 ዓ.ም የስብከተ ገና ሳምንት መጀመሩን ቀደም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን በዚህም መሰረት ይህ የስብከተ ገና የመጀርያ ሳምንት በተጀመረበት ወቅት በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ባሰሙት ስብከት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “ኢየሱስን ለመቀበል ያስችለን ዘንድ ልባችንን መክፈት ይኖርብናል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 23/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ የሚጀመረው የስብከተ ገና ሳምንት ስርዓተ አምልኮ ለገና በዓል የምያዘጋጃን ወቅት ሲሆን ኢየሱስን ለመቀበል ልባችንን መክፈት እንችል ዘንድ ይጋብዘናል። በስብከተ ገና ወቅት እየተጠባበቅን የምንገኘው ጌታ የተወለደበትን ቀን ብቻ አይደለም፡ ነገር ግን በተጨማሪም ክርስቶስ ዳግመኛ በክብር የሚመጣበትን ቀን በጉጉት ነቅተን እንድንጠባበቅ ጭምር ይጋብዘናል- እርሱ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ተመልሶ በሚመጣበት ወቅት ከእሱ ጋር ለመገናኘት ያስችለን ዘንድ የሚረዱንን ተገቢ የሆኑ ምርጫዎችን በማድረግ በብርታት በእርሱ ፊት እንቆም ዘንድ የሚረዱንን ተግባሮች በመፈጸም ተዘጋጅተን የምንጠብቅበት ወቅት ነው። የገናን በዓል ስናስታውስ፣ ክርስቶስ በክብር የሚመጣበትን ቀን በምንጠባበቅበት ወቅት፣ እኛም ከእርሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ ለመገናኘት በመዘጋጀት፣ ክርስቶስ በሚጠራን ወቅት ለእርሱ ጥሪ ምልስ ለመስጠት የምንዘጋጅበት ወቅት ነው። በእነዚህ አራት ሳምንታት ውስጥ ከተገለለና ከተለመደ የሕይወት ጎዳና እንድንወጣ እና በአዲስ ጎዳና ላይ ተስፋ በማድረግ እንድንራመድ ጥሪ የሚያደርጉልን ሳምንታት ሲሆኑ በተጨማሪም የወደፊቱን ተስፋ በማለምለም የወደፊቱ ኑሮዋችንን በአዲስ መልክ ለመኖር የምናልምበት እና በዚህ መልክ እንድንኖር ጥሪ የሚያቀርብልን ወቅት ነው። በዚህ እለተ ሰንበት (ኅዳር 23/2011 ዓ.ም) የተነበበል ቅዱስ ወንጌል (ሉቃ 21፡25-28, 34-36) በዚህ አቅጣጫ በትክክል እንድንሄድ ጥሪ በማድረግ በራስ ወዳድ መንፈስ የመኖር አባዜን በመተው፣ የአኗኗራችንን ዘይቤ መገምገም እንደ ሚገባን ያስጠነቅቀናል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት በጣም ወሳኝ የሆኑ ቃላት ናቸው፡ እንዲህም ይላል፡ ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር፣ በመባከን እና ስለዓለማዊ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ። ስለዚህ ከሚመጣው ክፉ ነገር ሁሉ ለማምለጥ ኃይል እንድታገኙ እና በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ” (ሉቃ. 21፡ 34,36) በማለት ያስጠነቅቀናል።

ከዛሬ ቀን ጀምሮ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን የገና በዓለ እስከ ምናከብርበት ቀን ድረስ ያሉትን የስብከተ ገና ሳምንታት መኖር የሚገባን ተግቶ በመጠበቅ እና በጸሎት ሊሆን የገባል። ተግቶ መጠበቅ እና መጸለይ!! ውስጣዊ የሆነ እንቅልፍ የሚከሰተው ኑሮዋችንን ራሳችንን ብቻ ባማከለ መልኩ በምንኖርበት ወቅት እና በሕይወት ውስጥ በምያጋጥሙን ችግሮች፣ ደስታዎች፣ ሕመሞች ውስጥ ራሳችንን በራሳችን ቆልፈን ስንቀምጥ ነው። እናም ይሄ ያደክመናል፣ ይህ ስልቹዎች እንድንሆን ያደርገናል፣ ይህ ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርገናል። የዛሬ ቅዱስ ወንጌሉ የሚናገረው ይህንኑ ነው፣ ደንዝዘን እና ሰንፈን እንዳንቀመጥ ይጠይቀናል። ይህ የስብከተ ገና ወቅት ከራሳችን ውጭ በመሄድ ሌሎችን እንድንመለከት፣ እራሳችንን እና ልባችንን በማስፋት፣ ለሕዝቦች እና ለወንድሞቻችን  ፍላጎት ልባችንን በመክፈት  በአዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ያላቸውን ምኞት እውን ለማድረግ እንድንሠራ ይጋብዘናል። ይህም በረሃብ፣ በፍትሕ መዛባትና በጦርነት የተሠቃዩ የብዙ ሕዝቦች ፍላጎት እና ምኞት ነው፡ የድሆች፣ የደካማዎች  እና የተተው ወይም የተረሱ ሰዎች ምኞት ነው። ይህ የስብከተ ገና ወቅት ህይወታችንን እንዴት እና ለማን መክፈት እንዳለብን በማሰብ ግልጽ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንድንችል ልባችንን ለመክፈት እድሉን ይፈጥርልናል።

በዚህ በስብከተ ገና ወቅት ጌታን በመልካም ሁኔታ ላይ በመሆን ለመጠባበቅ ከሚያስችሉን ባሕሪያት መላከል በሁለተኛ ደረጅ የሚጠቀሰው ደግሞ ጸሎት ነው። ይህ ሁሉ መሆን በሚጀምርበት ጊዜ ደኅንነታችሁ ቀርቦአልና ቀና ብላችሁ ወደ ላይ ተመልከቱ” (ሉቃ 21፡28) በማለት የሉቃስ ወንጌል ያሳስበናል። ይህም የምያመልክተው አስተሳሰባችንን እና ልባችንን በኢየሱስ ላይ በማድረግ ነቀተን እንድንጸልይ ነው። አንድ ነገር ወይም አንድን ሰው የምንጠብቀው ተነስተን በመቆም ነው። እኛም በዚሁ መልክ ኢየሱስን በምንጠባበቅበት ወቅት በጸሎት መንፈስ በመሆን እርሱን መጠበቅ ይኖርብናል፣ ይህም ተግባር በቀጥታ ተግቶ ከመጠበቅ ጋር ይያያዛል። ኢየሱስን ለመጠበቅ፣ ራሳችንን በራሳችን ሳንዘጋ ሌሎችን ነቅተን ለመጠበቅ እንችል ዘንድ እና በትጋት ለመቆም ያስችለን ዘንድ መጸለይ ያስፈልጋል። ነገር ግን እኛ የገናን በዓለ ለማክበር እንዲሁ የፍጆታ ቁሳቁሶችን ብቻ በመግዛት የተጠመድን ከሆነ፣ ይህንን ነገር ወይም ያንን ነገር ለማድረግ፣ ይህንን ብገዛ ወይም ያንን ብገዛ እያልን ዓለማዊ የሆነ በዓል ለማክበር በምንሞክርበት ወቅት በዚህ አኳኋን እያለን ኢየሱስ በሚመጣበት ወቅት እኛን አልፎ ይሄዳል፣ እኛም እርሱን ልናገኘው አንችልም። እኛ ግን ኢየሱስን ለመጠበቅ እንፈልጋለን፣ በጸሎት መንፈስ በትዕግስት ልንጠብቀው እንፈልጋለን፣ ይህም በቀጥታ ተግቶ ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው።

ይሁን እንጂ የጸሎታችን እጣ ፈንታ ምንድነው? ይህንን ከሁሉም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ወስጥ የተጠቀሱት የነቢያት ድምጾች ያሳያሉ። በዚህም ረገድ በዛሬው ጊዜ በግዞት ስለሞቱ ሰዎች እና ማንነታቸውን ለማጥፋት ለሚያስቡ ሰዎች የሚናግረው ነቢዩ ኤርምያስ ነው። እኛም ክርስቲያኖች የእግዚኣብሔር ሕዝብ አንዱ አካል በመሆናችን የተነሳ ማንነታችንን እንድናጣ ከሚያደርገን ዓለማዊ ተግባራት "የአረማዊነት" ባህሪይ በመተው የክርስትና እምነት መለያችንን በመልበስ በዚህ የኑሮ ዘይቤ መኖር ይኖርብናል። ስለዚህ በነቢዩ ኤርሚያስ በኩል የታወጀው የእግዚአብሔር ቃል ያስፈልገናል እንዲህም ይላል እነሆ የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።  በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቍጥቋጥ አበቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል” (ት.ኤር. 33፡14-15)። ይህ የሚበቅለው ቁጥቋጦ ኢየሱስ ራሱ ነው፣ የምንጠባበቀው እና የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ወደ ኢየሱስ እንድንቀርብ የምታደርገን፣ በጸሎት እና በትዕግስት የመጠባበቅ ተምሳሌት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠንን ተስፋ መጠባበቅ የምንችልበትን ኃይል እንድትሰጠን፣ በታሪክ ሂደት ውስጥ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ታማኝ በመሆን እና ምንም እንኳን የሰው ልጆች በስህተቶች ተሞልተው የሚኖሩ ቢሆንም ቅሉ፣ ነገር ግን የእርሱን መለኮታዊ ምሕረት በትዕግስት መጠባበቅ እንችል ዘንድ አማላጅነቷን መማጸን ያስፈልጋል።

 

02 December 2018, 16:31